ጭብጨባ የጠራት ብጽአት

 ጥሎባት ዘፈን ትወዳለች፤ የልቧን መሻት እንዳታጣጥም ቤታቸው ሙዚቃ የምትሰማበት ቴፕ ይሉት የለም። ‹‹ሳይደግስ አይጣላም›› ሆነና ጨርቆስ ከሚገኘው ቤታቸው ፊት ለፊት በ ‹‹ራህመቶ›› ሻይ ቤት ከጠዋት አንስቶ ሙዚቃ ይከፍታል። እሷም ነግቶ ሙዚቃ እስኪከፈትና መሽቶ እስኪዘጋ በጉጉት ትጠብቃለች። በሻይ ቤቱ ሸክላ ማጫወቻ የሚከፈቱትን ዘፈኖች አሳምራ ታውቃቸዋለችና ሁሌም አብራ ታዜማለች።

ብጽአት የዘፈን ፍቅር አድሮባታል። እናቷ ደግሞ ሙዚቃ የሚባል ነገር እንዲነሳ አይፈቅዱም። አጋጣሚ ሆኖ የመጀመሪያ ደረጃን የተማረችበት ፈለገ ዮርዳኖስና የሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት ከመደበኛ ትምህርት ሌላ የሙዚቃ ክበባት አልነበራቸውም።

በወቅቱ በየቀበሌው በግድ ይሰጥ የነበረውን ‹‹ንቃት›› የተሰኘ የወጣቶች የፖለቲካ ትምህርት ዕንቅልፍ እያዳፋት ትከታተል ነበር። በዚህ መሀል ከሌላ ክፍል የሚሰማው ተደጋጋሚ ጭብጨባ ያስገርማታል። በክፍለ ጊዜው እንድትነቃ ታስቦ የሚሰጣት የነማርክስና ሌኒን ትምህርት ጭራሽ እንቅልፍ ላይ እየጣላት ተቸገረች። ይህ ሲታወቅ ሁሌም አዳራሽና መጸዳጃ ቤት እንድታጸዳ ቅጣት ይበየንባት ጀመር።

አንድ ቀን በዕንቅልፍ ከምትፈተንበት የፖለቲካ ትምህርት ክፍል እንዳለች ከውጭ ስለሚሰማው ተደጋጋሚ ጭብጨባ ጠየቀች። ኪነቶች መሆናቸው ተነገራት። ብጽአት ስለ ኪነት አንዳች አታውቅም። ምንድነው? ስትል ጠየቀች። ምላሽ አላጣችም። ከፖለቲካ ትምህርቱ ውጭ የኪነት አባል መሆን እንደምትችል ተነገራት።

ብጽአት የኪነት ቡድኑን ከተቀላቀለች ፖለቲካውን መከታተል እንደማይጠበቅባት ተረዳች። ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› እንዲሉ በተማረከችበት ጭብጨባ ሰበብ በዕንቅልፍ ጥሎ የሚያስቀጣትን የፖለቲካ ትምህርት ተገላገለች። ፈጥናም የኪነት ቡድኑን ለመቀላቀል ወሰነች።

የኪነት አባል ከሆኑት የሰፈር ጓደኞቿ አብዲ ኡመር አንዱ ነበር። አብዲን እንዲያስገባትና ማጨብጨብ እንድትችል ለመነችው። በጨዋታ፣ በቀልድና ድብድብ ለምትታወቀው ብጽአት ምላሹ ጥሩ አልሆነም። ስለምትረብሽ እንደማይሆን ነገራት። ጸባይዋን ለማረም ቃል ገብታ የቀበሌያቸውን ኪነት ተቀላቀለች።

ይህ የጨዋታ አዋቂዋ ድምጻዊት ብጽአት ሥዩም የሙዚቃ አጀማመር ነው። ወቅቱ የአብዮት ጊዜ ነበር። በቀበሌያቸው ኪነት የሚዘመሩ ሀገርን የሚያወድሱ ዘፈኖችን በጭብጨባ ማጀብና መቀበል ተግታ ትለማመድ ያዘች።

በጭብጨባ የማጀብ ሥራዋን ወዳዋለች፤ ከዛ እንቅልፏን ከሚያመጣባት ንቃት የፖለቲካ ትምህርት አድኗታል። አሁን የሌኒና የማርክስ ታሪክና የፖለቲካ ውሳኔ የለም። ስለዚህ በማጨብጨብ ማጀቡንና መቀበሉን ትለማመዳለች። የቀበሌው የኪነት አባላት ዝግጅታቸውን ለቀበሌው ነዋሪ ሊያቀርቡ ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ሆኗል። የድግሱ ታዳሚ በስፍራው ተገኝቷል። ዋና ድምጻዊቷን በጭብጨባና በድምጽ የሚያጅቡ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። በድንገት ግን አንድ ጉዳይ ተሰማ። የዋናዋ ድምጻዊት እናት ድንገት መታመም ቡድኑን አጉድሎታል። ድምጻዊቷ ሁሉን ትታ ወደ ሆስፒታል ገስግሳለች።

የአስተባባሪውን መጨነቅ ያስተዋለችው ብጽአት ‹‹ምን ሆንክ?›› ስትል ጠየቀች። ‹‹ልጅቷ ቀረችብኝ ጉድ ሆንኩ›› አላት። ለዚህ ነው እንዴ እኔ እዘፍንልሃለሁ አለችው። የሰማውን አላመነም ‹‹ከመጣሽ ሳምንትሽ ነው። ዘፈኑን አታውቂውም›› ሲል ሞገታት። ምላሽዋ አልተቀየረም። ደጋግማ ‹‹አውቀዋለሁ›› ስትል አረጋገጠችለት።

ከዚህ ቀደም ለብቻዋ ስትዘፍን ሰምቷት አያውቅምና ወደጓሮ ወስዶ ‹‹እስቲ ዝፈኝልኝ›› አላት። ግጥምና ዜማውን ይዛው ኖሮ አሳምራ ተጫወተችው። በድምጿ ውበት የተማረከው አስተባባሪ እንደውም ልጅቷ ብትመጣም አንቺ ነሽ የምታቀርቢው አላት። በዚህ መልኩ የቀበሌው ኪነት ዋነኛ ድምጻዊት ሆነች።

በቀበሌ አንድ ተብሎ የጀመረ የብጽአት ድምጻዊነት ወደ ከፍተኛ ኪነት አደገ። የተለያዩ ዝግጅቶች ሲኖሩ አድማቂ ሆነች። በአካባቢው የካድሬ ሠርግ ሲኖር ያለብጽአት የማይታሰብ ሆነ። እንደተለመደው አንድ ቀን ሠርግ እንድታጅብ ተነገራት። እናቷ ለጉዳይ ከቤት ሊወጡ ሲሰናዱ ቤት እንድትጠብቅና ታናናሾቿን እንድትንከባከብ ያዟታል። ‹‹ሠርግ አለብኝ›› ብትልም ዛሬ አርፈሽ ቁጭ በይ ከቤት እንዳትወጪ ትእዛዛቸው ሆነ።

ብትጠበቅ ብጽአትን የበላ ጅብ አልጮህ አለ፤ እንደምንም ከቤት ወጥታ እናቴ ስለከለከለችኝ አልመጣም አለቻቸው። ምን ሲደረግ በአብዮት ጊዜ ይህ ይሞከራል። እናቷ ወደ ቀበሌ፣ እሷን ወደ ሠርጉ ወሰዱ። ብጽአት ሠርጉን፣ መልሱንና ቅልቅሉን ያለተቆጪ አጀበች። ከድግሱ መጠናቀቅ በኋላ በብጽአት ልመና ከእስር የተፈቱት እናት ልጃቸውን ለመከልከል አልሞከሩም። መዘዙን አይተዋልና ዝግጅት ባላት ጊዜ ለመላክ ፈቃጅ ሆኑ።

በየቦታው ተፈላጊነቷ የጨመረው ብጽአት የ17 ዓመት ወጣት ሳለች የልጅ እናት ሆነች። መጀመሪያውኑ ከእጅ ወደአፍ በሆነው ኑሮ ላይ የልጅ እናት መሆኗ ቤተሰቡን አስከፋ፤ እሷም ከኪነቱ ራቀች። ልጇ ሁለት ዓመት ሲሞላው ምን ሰርቼ ቤተሰቤን ልደግፍ? ልጄንስ ላሳድግ? ብላ ማሰብ ጀመረች። አንድ ጓደኛዋ አዝማሪ ቤት እንድትሰራ ሀሳብ አቀረበላት። ምንድነው አዝማሪ ቤት ስትል ጠየቀች ‹‹ቋራ›› ምግብ ቤት ይዟት ሄደ። ማታ የሚሰራ መሆኑን ስታውቅ እናቷ እንደማይፈቅዱ አውቃ ስጋት ገባት። እናት ሲሰሙ ምን ሲደረግ አሉ። እናቷ በማታ ቡና ቤት ለሚያስመሽ ሥራ ይሁንታ አልሰጡም። ሥራውን ሄድ መለስ እያለች ሞከረችው። ደሞዝ ባይኖረውም በሽልማት ደህና ገንዘብ ይገኝበታል። የእናቷ ቁጣ በረታ። ለትንሽ ጊዜ ከቤት ወጥታ ከሴት ጓደኛዋ ቤት መኖር ጀመረች።

በቋሚነት ቋራ ምግብ ቤት በአዝማሪነት መሥራት ጀመረች። ሆኖም እሷ የምታውቀው ዘፈንና የአብዮት መዝሙር ከአዝማሪ ቤት አልገጥም ቢላት ተቸገረች። እሷ የምታውቃቸውን ዘመናዊ ዘፋኞች እየጠራች ለባለ ማሲንቆ እንዲያጅባት ብትጠይቅ የማይሆን ሆነ።

የድምጿን ውበት የተመለከቱ በቤቱ የነበሩ የሙዚቃ ባለሙያ የባህል ዘፈን እንድታጠና መከሯት። ለማጥናት ዘፈኑን ማግኘት ያስፈልጋልና ግራ ገባት። ያኔ የመጣላት በኢትዮጵያ ሬዲዮ የዘፈን ፕሮግራም ያቀርብ የነበረው ጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ ነበር። ባታውቀውም እሱን ፍለጋ ቢሮው ድረስ ሄደች። ጀማሪ ዘፋኝ መሆኗን ነግራ ለጥናቷ የሚያግዙ ዘፈኖችን በቴፕ ቀድቶ እንዲሰጣት ጠየቀችው። ቴፕ ከሌለሽ በምን ትሰሚዋለሽ አላት። የጓደኞቿን ቤት ቴፕ ጠቆመችው። ‹‹ባለውለታዬ›› የምትለው ጋዜጠኛ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ከሪል በካሴት ቀድቶ ሰጣት።

የተለያዩ የባህል ዘፈኖችን ከመስማት ባለፈ ተለማመደች። አዝማሪ ቤት የሚፈልገውን ታዳሚውን በግጥም ማወደስ ከሌሎቹ እያየች በሂደት ተማረች። በሽልማት 80 ብር ያገኘች ቀን የያዘችው መንገድ ልክ መሆኑ ገባት። ሥራውን ደጋገመችው።

ብጽአት ሽልማቷን አጠራቀመች። 390 ብር በእጇ ቆጠረች። እሱን ይዛ እናቷ ቤት ገባች። እናቷ የብሩ ብዛት ቢገርማቸው የልጃቸውን የድምጽ ኃይል መረዳት ጀመሩ። ያኔ ወደ እናቷ ቤት ተመለሰች። ሙዚቃ ሰምታ የምትለማመድበት ቴፕ ቢኖራቸው ጥሩ ድምጻዊት እንደምትሆን አሳመነቻቸው ቴፑን ገዙላት።

ብጽአት ራስ ቲያትር ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ ልትቀጠር ሄደች። ፈታኞቹ ‹‹ዝፈኚ›› ሲሏት የመሀሙድን የፍቅር ወጥመድ ነው አቀነቀነች። ‹‹የሴት ዘፈን ቀይሪ›› ተባለች። ጭቅጭቁ ቀርቶ አሃሃሃ እያለች የመሀሙድን ደገመች። ‹‹ኧረ! የሴት›› አሏት። የጥላሁን ገሰሰ ምግብማ ሞልቷል … እኔን ያከሳኝ የፍቅር ርሃብ ነውን አዜመች። ‹‹ ኧረ! የሴት ሲሉ ዳግም ጮሁባት። እንባዋን እየዘረገፈች እኔ ይሄን ነው የማቀው አለች። ወዲያው ግን ‹‹ድንገት ሳላስበው፣

ውጥን ሳይኖረኝ፣

የሚያስለቅስ ፍቅር በድንገት ያዘኝ።

ብላ ከለቅሶዋ ተመለሰች። ወዲያው አንደኛ ወጥታ ማለፏን ሰማች። ደሞዙም የተወዛዋዥ መሆኑ ተነገራት። በአዝማሪ ቤት በሽልማት ለምትንበሻበሸው ብጽአት ደሞዝ የተባለው 90 ብር ከትራንስፖርትና ከአንዳንድ ወጪዎች አያልፍም። አላዋጣ ቢላት የአዝማሪ ቤት ሥራዋን ቀጠለች።

ከቋራ ቀጥሎ ባምቢስ ይገኝ የነበረው የወይዘሮ እልፍነሽ ቤት መሥራት ጀመረች። በቤቱ ያለ ደመወዝ በሽልማት ብቻ መሥራት ያዘች። ስፍራው ታዋቂ ሆነ። ‹‹የብጽአት ቤት የሚል ሥያሜም ተቸረው።›› ቀስ በቀስ ዝናዋ እየጨመረ በመሄዱ ብጽአት ቤት እንሂድ እያሉ የሚሰበሰቡበት የበርካቶች መቃጠሪያ ሆነ። በስፍራው ሳለች የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት ፍቃዱ ዋሪና፣ የዜማ ደራሲው አበበ መለሰ ተገኝተው ብቃቷን በአካል አረጋገጡ።

ባይዋት ቀን ‹‹ካሴት እንሰራልሻለንና ነገ ልምምድ ጀምሪ›› አሏት። በወቅቱ በሙዚቃ ቤቱ የሰለሞን ተካልኝን አልበም ጀምረው ነበርና አንድ ለብቻዋና ሁለት ዘፈኖችን ከሱ ጋር በቅብብል የሰሩበት የመጀመሪያ የጋራ አልበም ‹‹ፋጡማ›› በሚል ርዕስ ወጣ።

አልበሙ እንደወጣ ወዲያው አምላክ ተረዳ ሙዚቃ ቤት ሌላ አልበም የመሥራት እድል አመቻቸላት። ብጽአት ሥዩም ከፀሐይ እንዳለ፣ ወረታው ውበትና ከተማ መኮንን ጋር 4 ድምጻዊያን በአንድ ሲሉ በጋራ የሰሩት አልበም በገበያ ዋለ። ከሰለሞን ተካልኝ ጋር ካወጡት አልበም በጋራ የዘፈኑት አንድ ዘፈን ተቀርጾም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የመታየት እድል አገኘች። ዝናዋ፣ ተፈላጊነቷም ሆነ ብቃቷ ይበልጥ እየጨመረ ሄደ። ከዛ በኋላ የተለያዩ ቤቶች ስትሰራ ቆይታለች። በመጨረሻም የራሷን ትክክለኛ የብጽአት ቤት ከፍታ ታዳሚውን አዝናንታለች። በሷ ቤት ነበር የብጽአትና የአበበ ፈቃደ ጥምረት የተፈጠረው።

እሱ ማሲንቆውን እየተጫወተና በድምጹ እየቀለጸ፣ ከእሷ ጋር በአንድ እየተቀባበሉ በግሩም ሁኔታ ታዳሚን አዝናንተዋል። ብጽአት ‹‹የአዝማሪን ቤት ሥራ ከፍ ያደረግንበት፣ ብዙ ዓለም ያየንበት ወርቃማ ጊዜያችን›› የምትለው ጥምረት ነበራቸው። ብጽአትና አበበ በማሲንቆአቸው ታጅበው የባህል ምልክት ተደርገው እስኪቆጠሩ ድረስ ያልተጫወቱበት ቦታ የለም። ከአበበ ጋር የነበራቸው ጥምረት የሚገርም ቢሆንም በ1991 ዓ.ም በወጣው አልበሟ ውስጥ የሚገኘው ‹‹አደራ ልጄ›› የተሰኘው ሥራዋ ከሁሉም ልቆ መታወቂያዋ ሆኖ ነበር።

አልበም ለመሥራት ከግጥም ደራሲ ሙሉጌታ ተስፋዬ ጋር ዝግጅት እያደረጉ ያለበት ወቅት የበኩር ልጇን ወንድሟ ዘንድ አሜሪካ ሰዳ በናፍቆቱ እየተብሰለሰለች ነበር። በየወሩ ከፍተኛ ወጪዋም የስልክ ክፍያ ሆኗል። እቤት ስትገባ በወንድሟ የተናደዱትን እናቷን ለምን አትተይውም የሚል ምክር ትለግሳለች። ወልደሽ የለም ይተው እንደሆነ እናያለን አሉት። ልክ እኮ ናት እናቴ ስትል ለግጥም ደራሲው አያ ሙሌ ታሪኩን ነግራ ግጥም እንዲጽፍላት ትጠይቀዋለች። በወቅቱ ደራሲው ከሁለት ልጆቹ ጋር ተለያይቶ ናፍቆት ላይ ነበር። በተመሳሳይ የዜማውም ደራሲ ሙሉጌታ አፈወርቅ ባለቤቱ ልጆቹን ይዛ ተለይታው ነበርና ሦስት የልጅ ብሶተኞች በጋራ ‹‹አደራ ልጄ››ን ፈጠሩ። ዘፈኑ የልጅ ፍቅርንና የእናትን ውለታ ሳይረዱ ቆይቶ ልክ እናት ሲሆን መረዳትንና እናትን ለበደሉት ጥፋት ይቅርታ መጠየቅን ያነሳል።

ይሄን ዘፈን ከሌሎቹ ዘፈኖቿ በተለየ እናቷ በሕይወት እያሉም ሆነ ካረፉ ወዲህ በእንባ ታጅባ ለቅሶዋ ሲበረታ በመሀል አቋርጣ የምትዘፍነው ዘፈኗ ነው። ብጽአት የትዳር ሕይወቷም የሰመረና በርካቶች የሚቀኑበት ነው። ሆኖም ከትዳር አጋሯ ተዋናይና አዘጋጅ ተስፋዬ ገብረሃና ጋር የተገናኙት ‹‹ባመንኩት ተከዳሁ›› ብላ ባሰበችበትና ‹‹ሰውን ማመን በቃኝ›› ብላ ብቸኝነትን በመረጠችበት ወቅት ነበር። አንድ ቀን ብሔራዊ ትያትር ተወዳጁን ተዋናይ ተስፋዬን አይታ የተሰማትን ስሜት አልወደደችውም። እናም ለፈጣሪዋ ጸለየች ፈጣሪ አሁንም ሰው ወድጄ ልጎዳ ነው ምን በደልኩህ ስትል ተማረረች።

ትውውቁ ፈጣሪ ተካሽበት ሲል ያዘጋጀላት ሆነና ሰዎች አጥንተው አስጠንተው የሚገቡበት ግንኙነት ቢከሽፍም ከአንድ ቀን የቲያትርና የራት ግብዣ መልስ በጋራ ተጠቃለሉ። ‹‹ይቻላል›› የተሰኘው ዘፈን ለሱ የተሰራ መሆኑን ትናገራለች።

ወደደችው አሉኝ ብወደው፣

ያንን ሸጋ ጉብል ብፈቅደው፣

……….ይቻላል! ይቻላል! ማፍቀርም ይቻላል

እያለች መጀመሪያ የወደደችው እሷ መሆኑን በግልጽ ትናገራለች። ከእሱ ፍቅር ተስፋዬ የተሰኘች ሴት ልጅ ወልደው 27 ዓመታትን በትዳር ዘልቀዋል። ‹‹ይቻላል›› የተካተተበት ‹‹የባስረሳኝ›› አልበም መጠሪያ የሆነው ሙዚቃ አሰራሩ ይለያል።

‹‹ቴዲ አፖ›› እያለች አፍ ባልፈታ አንደበቷ በቴዲ አፍሮ አድናቆት የተሰቃየችው ልጃቸውን ሊያገኝ ድምጻዊው ከቤታቸው ይገኛል። ከመኖሪያዋ ባገኘው ፒያኖም ‹‹ባስረሳኝ›› ሲል የዜማ መያዣ ግጥም ይደርሳል። ይልማ ገብረአብ አሟልቶ ግጥም የደረሰለት ባስረሳኝ በ1997 ዓ.ም የወጣው አልበሟ መጠሪያና ተወዳጅ ሥራዋ ሆኗል።

ከሀገር የወጣችው እንደተለመደው ለኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሙዚቃዋን በአውስትራሊያ አቅርባ ለመመለስ ነበር። እዛው አውስትራሊያ እያለች ታመመች። የወሰዷት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች የመጀመሪያ ሕክምናዋን ወጪ ሸፈኑላት። ለቀጣዩ ግን ሕክምናሽ እንዲቀጥል ወረቀትሽን አስተካክይ የሚል ምክር ቸሯት። የጤና ነገር ነውና ‹‹እስቲ ልሞክረው›› ብላ ያመለከተችው ወረቀት በሦስት ሳምንት ተሰጣት። በስምንት ወሯ ቤተሰቦቿን ወሰደች።

በሰው ሀገር ኑሮ ተጀመረ። አዲስ አበባ ሬስቶራንትን ከፈቱ። ከባለቤቷ ጋር ምግብ አብሳይ፣ እቃ አጣቢ፣ አስተናጋጅ፣ ግዢ፣ አስተዳዳሪ ብቻ ሁሉንም ሆነው ሰርተዋል። ምግብ ቤቱን ስትጀምር ሀሳቧ ቀን ምግብ ቤት፣ ማታ ደግሞ ሙዚቃ የሚሰራበት ለማድረግ ነበር።

በአውስትራሊያ ያለው ታዳሚ ቁጥር አነስተኛ መሆን ሙዚቃ የመሥራቱን ሀሳብ አስጣለ። በዚህ ጊዜ ሁለቴ በአሜሪካ ሙዚቃ ከማቅረቧና ዓመት ከአውስትራሊያ ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ መድረክ ላይ ከመሥራቷ ውጭ ከሙዚቃ ተራርቃ ቆይታለች። አሁን ግን ከ15 ዓመታት የአውስትራሊያ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ከናፈቃት የሀገሯ አድማጭ ጋር ተገናኝታለች።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You