አዲስ አበባ:- የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ወደ መስመሮቹ በሚገቡ ባዕድ ነገሮች ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ባለስ ልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የፍሳሽ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬ ክተር አቶ ተስፋዓለም ባዩ ጉዳዩን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ወደሥራ የገባው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ፤ ወደመስመሮቹ በሚገቡ ቢንዚን፣ ናፍጣ፣ የሞተር ዘይት፣ ኬሚካል፣ ስብና ቅባቶች በተለይም ደግሞ የዝናብና የጎርፍ ውሃ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዓለም ማብራሪያ፤ በዚህ ዓመት በዘነበው የበልግ ዝናብ ወደፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያው የገባ ከፍተኛ ጎርፍ የቤት ውስጥ ፍሳሽ ቆሻሻን ብቻ ለማጣራት የተገነ ባውን ማጣሪያ ጣቢያና የፍሳሽ መስመሮች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
በመጪው ክረምት የሚመጣውን ዝናብና ጎርፍ ለመከላከል የፍሳሽ መስመርና ማንዋሎችን ከህገ ወጥ ቅጥያ መጠበቅ እንዲሁም ከጎርፍ ውሃና ከኢንዱስትሪ የሚወጣ ፍሳሽ
ከባለስልጣኑ የፍሳሽ መስመር ጋር እንዳይገናኝ በዘመቻ የመለየትና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ የመውሰድ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ተስፋዓለም አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለስልጣኑ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ «ሜምብሬን ባዮሬክተር» (Membren Bio Reactor) የተባለ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች በመገንባት ወደሥራ የገባ ቢሆ ንም፤ በሥራ ላይ ባሉ ጣቢያዎች እንደ ጆንያ፣ ላስቲክ፣ አጥንቶች፣ ዳይፐርና ሌሎች ደረቅ ቆሻሻዎች እየገቡ ጉዳት እያደረሱበት እንደሚገኝ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸ ዋል።
ህብረተሰቡ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ወጥቶ ባቸው የተገነቡ እነዚህ የፍሳሽ መሰረተ ልማቶችን ከአደጋና ብልሽት መጠበቅ አለበት ያሉት አቶ ተስፋዓለም፤ ከመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ቆሻሻ ውጪ ሌሎች ደረቅና ፍሳሽ ነገሮች ወደመስመር እንዳይገቡ ጥንቃቄና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተ ላልፈዋል፡፡
የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን፤ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ያህል የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
በድልነሳ ምንውየለት