አዲስ አበባ፡– የህግ የበላይነትንና ፍትህን ለማስፈን የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች በውክልና የሰጠውን የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በማንሳት በአገሪቱ በሙሉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ማዋቀር እንደሚገባ ምሁራን ይገልጻሉ።
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 ንዑስ አንቀጽ 2 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የፌዴራል ከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችን በአገሪቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያደራጅ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሊወስን እንደሚችል ያስቀምጣል።
በዚህ ረገድ አንዳንድ የህግ ምሁራን ፍትህን ለማስፈን የመጀመሪያና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መቋቋም አለባቸው ይላሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ የስልጣን ውክልናውን ማስቀጠል ፍትህንና የህግ የበላይነትን እንደሚያሰፍን ያመላክታሉ።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል መስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በማፈናቀል አራት ሺህ 43 መዝገቦች ላይ ምርመራ ተደርጎ በሁለት ሺህ 276ቱ ላይ ዓቃቢ ህግ ክስ እንዲመሰርት ተልኳል።
ክስ የተመሰረተባቸው አራት መቶ 68ቱ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ አፈናቃዮች በህግ ጥላ ስር አልዋሉም። ለዚህም ዋናው ምክንያት አፈናቃዮችን ለማቅረብ በየደረጃው የሚገኝ የፖለቲካና የጸጥታ አመራር ቁርጠኛነትና አለመተባበር ነው ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በአገሪቱ የፍትህ አሰጣጥ ሂደት መጓደል አለ። የህግ የበላይነት ማስከበር ችግር ላይ እየወደቀ ነው። የክልል ፍርድ ቤቶችም በተሰጣቸው የፌዴራል የዳኝነት ውክልና ለዜጎች ገለልተኛ ሆነው ፍትህ እየሰጡ አይደለም ብለዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ጥጋቡ፤ የህግ የበላይነትና ፍትህን ለማስፈን የፌዴራል መንግሥት ያወጣቸው ህጎች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መዳኘት አለባቸው። ይህ ባለ መሆኑ ወንጀለኞች ክልሎችን እንደመጠጊያ እየተጠቀሙ ነው። ዜጎችም በገለልተኛነት ፍትህን ማግኘት አልቻሉም።
የህግ የበላይነትን ለማስከበርም አልተቻለም። ስለሆነም፤ የፌዴ ራል መንግሥት በውክልና ለክልሎች የሰጠውን ስልጣን በመመለስ ፍርድ ቤቶችን በክልሎች አደራጅቶ ፍትህን ለተጠማው ህዝብ መስጠት አለበት ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ዶክተር መሀሪ ረዳኢ፤ የረዳት ፕሮፌሰሩን ሃሳብ አይቀበሉም። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የፌዴራል መንግሥት ውክልናውን ከማንሳት ይልቅ ፍትህ ማጣት አገርን ያጠፋል በሚል ዕምነት ተቀራርቦ መስራት፤ የጋራ አመለካከት መፍጠር፤ በፍትህ ዘርፉ ያለውን ችግር አንጥሮ በማውጣት መፍትሄ መስጠት፤ መርህና ህግን መሰረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ያመላክታሉ።
የክልሎችን ውክልና አንስቶ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን በአገሪቱ ክልሎች ማደራጀት ልዩነት የለውም። በክልሎች ያሉ ዳኞች ችግር በፌዴራል አለ። ከብሄርም አንፃር ስልጣን የሚያገኙት ከክልሎች ስለሆነ ብሄርተኞች ናቸው።
ውክልና ቢነሳም በሚቋቋሙት ፍርድ ቤቶች የሚመደቡት ዳኞች የአካባቢውን ቋንቋ መቻል ስላለባቸው የዚያው አካባቢ ሰዎች ናቸው። ፍትህ ካጓደሉ ውክልናው ተነስቶም ቢሆን ያጓድላሉ። ሁሉም ተባብሮ ከመስራት ባለፈ ውክልናውን ማንሳት በፌዴራል እና በክልሎች መካከል አለመተማመን ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ የለውም ባይ ናቸው።
ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ለዶክተር መሀሪ አስተያየት ምላሽ አላቸው። እርሳቸው እንደ ሚሉት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአገሪቱ መደራጀታቸው ክልሎችን መጠጊያ የሚያደርጉ ወንጀለኞችን ትክክለኛ ፍርድ ይሰጣል።
ህጎቹ የፌዴራል ስለሆኑ የፌዴራል የዳኝነት አካሉ በህጉ መሰረት ፍትህ ይሰጣል። አስተዳዳሪውም ፌዴራል ስለሆነ ያለ ጫና ገለልተኛ ሆነው ይወስናሉ። ፍርድ ቤቶች ከክልል ባለስልጣናት ተጽዕኖ ነፃ ሆነው ለመስራት በፌዴራል መንግሥት ቢደራጁ የተሻለ ነው። 80 በመቶ የአገሪቱን በጀት የሚያስተዳድረው የፌዴራል መንግሥት ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍና ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የተሻለ ዕድል አለ።
የህግ ምሁር አቶ ሙልዩ ወለላው፤ አገሪቱ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥት ስልጣን ስር የሚወድቀውን የፍርድ ቤት ስልጣን የፌዴራል መንግሥት ፍርድ ቤቶችን በመላ አገሪቱ አዋቅሮ ቢመራ መልካም መሆኑን ያነሳሉ።
ሀሳባቸውን በምክንያት ሲያስደግፉም፤ በፌዴራል ስልጣን ስር የሚወድቁ የዳኝነት ሥራዎች በክልሎች የመፈጸም ችግር እየገጠማቸው ነው። አንፈጽምም ባይሉ እንኳን የማጓተት ሁኔታ ይታያል። በህገ መንግሥቱ የተቀመጠው የስልጣን ኃላፊነት አሁን ላይ እየተደበላለቀ ነው። የአገልግሎት አሰጣጥ መጓተትም በክልል ፍርድ ቤቶች ይታያል።
ከዚህም በላይ በአሁኑ ወቅት ክልሎች «በእኔ ክልል አትግባ» በሚሉበት ወቅት በፌዴራል ስልጣን ስር የሚወድቁ የዳኝነት ኃላፊነቶች በትክክል ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። በዚህም የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት እየተጓደለ ነው።
የፍርድ ቤቶችን አስተዳደራዊ ነፃነት ለመጠበቅ እና በፋይናንስ ጠንካራ ለማድረግ የፌዴራል መንግሥት በአገሪቱ ፍርድ ቤቶችን ቢያዋቅር የዳኝነት ስርዓቱ ውጤታማ ይሆናል። ነገር ግን፤ ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት ግምገማዊ ጥናት አድርጎ ችግሩን መፈተሽና መፍትሄ ማመላከት የተሻለ መሆኑንም አመላክተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚ ዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው «አዲስ ወግ» በተባለው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ደረጃዋ ዝቅተኛ ነው። እ.ኤ.አ በ2018 የዓለም አቀፉ ፍትህ ፎረም ባወጣው ሪፖርት ከዓለም ከ126 አገራት 118ኛ ስትሆን በአፍሪካ ከ30 አገራት 27ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በተመሳሳይ ወቅት የሰዎች ነፃነት ፎረም የተባለው ድርጅትም በአገሪቱ የህግ የበላይነት ከ162 የዓለም አገራት 150ኛ መሆኗን ማረጋገጡን አመላክተዋል። ይህ የፕሬዚዳንቷ መረጃ ኢትዮጵያ በህግ የበላይነትና ፍትህን በማስፈን ወደኋላ መቅረቷን ያመለክታል።
ፕሬዚዳንቷ፤ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተቋማት ሚና አላቸው። ዋናዎቹ ፍርድ ቤቶች ናቸው። ፍርድ ቤቶች ግን ደካማ ናቸው። የህግ የበላይነት እንዲከበር በፍትህ አካላት ተዕልኮና ሚና ላይ የጋራ መግባባት አልነበረም። ተቋማቱና መሪዎቹ ነፃ አልነበሩም። የተነሳሽነትና የሀብት ውስንነት አለባቸው። ፍርድ ቤቶች የተገልጋዩን ብዛት የሚመጥን አቅም የላቸውም። በአጠቃላይ ፍርድ ቤቶች መቀየር አለባቸው ይላሉ።
በምሳሌም ሲያመላክቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዓመት 15 ሺህ፤ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 20 ሺህ፤ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 140 ሺህ ጉዳዮች ለማስተናገድ ያቅዳሉ። ከእቅዱ በተቃራኒው ዳኞች ቀጠሮ አስይዘው ማስቻያ ስለሌላቸው ቀጠሮ ያስቀ ይራሉ። ማስቻያ በማጣታቸውም ዳኞች በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ፍርድ እንደሚሰጡ በማንሳት አንገብጋቢ ችግር መኖሩን ያስረ ዳሉ።
በአገሪቱ ያለው የፍትህ ስርዓት በብዙ ችግር ውስጥ እንደሆነ በሁሉም ደረጃ የሚታመን ሀቅ ነው። ችግሩም ከመዋቅር አንስቶ እስከ ግለሰብ ባለሙያ የሚደርስ ነው። ይህን ለመፍታትም በጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሮችን መለየት አስቻይ ሁኔታዎችን ማወቅና በጥናቱ ውጤት ላይ ተመስርቶ ፍርድ ቤቶችን በፌዴራል በማዋቀር ወይም በነበረው የውክልና አካሄድ ጠንካራ የፍትህ ስርዓት መዘርጋት ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ