ክረምቱ እና የፀጥታ ችግር እንዲሁም የዋጋ ንረቱ፣ ፆም እና ሌላ ሌላውም ተደማምሮ ገበያው ተቀዛቅዞ ሰንብቷል። በተለያዩ ምክንያቶች ከዕለት ወደ ዕለት እየተቀዛቀዘ ገበያው ሲረበሽበት የከረመው የማምሻ ግሮሰሪ ባለቤት እነተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማርያምን ሲያይ ፈገግ አለ። የግሮሰሪው ባለቤት አስተናጋጁን ይርጋን ጠርቶ ‹‹እነዚህ ጨለማ እና ዝናብ ሳይበግራቸው ደንበኝነታቸውን ሳያቋርጡ ለዘመናት የቀጠሉትን ተስተናጋጆች የዕለቱ ወጪያቸው በእኔ እንደሚሸፈን ንገራቸውና የበለጠ ዘና ይበሉ›› አለ።
አስተናጋጁ ይርጋ እንደታዘዘው ለእነተሰማ ሔዶ ነገረ። እነተሰማ በፈገግታ አመስግነው ተጨማሪ የሚጠጡትን አዘው ጨዋታቸውን ቀጠሉ። ይርጋ ከአካባቢያቸው ራቅ እንዳለ ገብረየስ ‹‹የሕዝብን ስህተት መንገር ተገቢ ነው። አስፈላጊ ሲሆን መውቀስም ያስፈልጋል። ሕዝብ አያጠፋም ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ሕዝብ የሰዎች ስብስብ ነው። አንዳንዴ የግለሰቦች የተሳሳተ ዕይታና ሃሳብ ሕዝብ ውስጥ ይሰርፃል፤ በዚህ ጊዜ ሕዝብ ይሳሳታል የሚል እምነት አለኝ። ለምሳሌ ግብር የመክፈልን ጉዳይ መጥቀስ ይቻላል።
ግብር የግድ መከፈል አለበት። ነገር ግን ብዙ ሰው ግብር መክፈል ተገቢ መሆኑን ተገንዝቦ አይከፍልም። ግብር መከፈል እንዳለበት ከሚያምነው እና በፈቃደኝነት በእውነት ላይ ተመስርቶ ከሚከፍለው ሰው ይልቅ፤ ጥናት ላይ መመስረት ቢያስፈልግም በደምሳሳው ከታየ ግብርን የሚያጭበረብረው ሰው ቁጥር ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ እኛ የምንጠቀምበት ይኸው ግሮሰሪ ውስጥ ለግብር ክፍያው አመቺ ይሆን ዘንድ የሂሳብ መመዝገቢያ ማሽን አለ። ነገር ግን ማሽኑን እየተጠቀሙበት አይደለም። እኛም ሂሳብ ስንከፍል ደረሰኝ አንጠይቅም። እነርሱም ስለለመዱን ደረሰኝ አይሰጡንም።
ደረሰኝ የሚሰጡት አዲስ ለሆነ እና ምናልባትም የገቢዎች ሠራተኛ ይሆናል ብለው ለሚገምቱት ሰው ነው። ይህ በአንድ ግሮሰሪ ውስጥ በተግባር አሁንም እያየነው ያለው ቢሆንም፤ ብዙ ነጋዴዎች በእውነት ላይ የተመረኮዘ ግብር አይከፍሉም። ያው ይህንን አስፍተን ስናየው ብዙኃኑ ነጋዴ ማህበረሰብ ተገቢውን ግብር ይከፍላል ለማለት ያዳግታል። ይህ አስተሳሰብ ሕዝቡ ውስጥ የሰረፀ ይመስለኛል። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሕዝብም ይሳሳታል ብሎ መናገር ይቻላል›› ሲል የጫወታውን ሜዳ ለዘውዴ እና ለተሰማ ለቀቀ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ ከግብር አንፃር ከተነሳን ችግሩ ሕዝቡ ላይ ሳይሆን ግብርን ሰብስቦ ሥራ ላይ በሚያውለው አካል ላይ ነው። ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የሚያነሳውን ጥያቄ በጥንቃቄ ማዳመጥ እና ምላሽ መስጠት ካልተቻለ፤ ሕዝብ ለምን ግብር ይከፍላል? ሕዝቡ መሠረታዊ ፍላጎቶች አሉት። ዋነኛዎቹ መንገድ፣ ጤና፣ ውሃ፣ ምግብ እና መጠለያ እያልን መዘርዘር እንችላለን። እነዚህን ማቅረብ ደግሞ የግብር ሰብሳቢው ግዴታ ነው። በዚህ በኩል ሰፊ ክፍተት አለ። ክፍተቱ ደግሞ ሰዎች ግብር እንዳይከፍሉ እንዲያስቡ ያስገድዳቸዋል። ይህ የሰዎች ሁሉ ባህሪ ነው። ማንኛውም ሰው ለሚሰጠው ማንኛውም ጉዳይ ምላሽ ይፈልጋል። ምላሽ ካላገኘ እርሱም በተቃራኒው ንፉግ ይሆናል። ›› ሲል ሰዎች ግብር ለማጭበርበር መነሻ ይሆናቸዋል ብሎ ያሰበውን ጉዳይ አስረዳ።
ገብረየስ ግን፤ ‹‹ግብር ማለት ሰዎችን መበዝበዝ ሕዝብን ማራቆት አይደለም። በእርግጥም ግብር በተዘዋዋሪ ከመንግስት በምንም መልኩ ለሚገኝ አገልግሎት የሚፈፀም ክፍያ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ግብር መክፈል ቀርቶ የግል ፍላጎትን ብቻ በማሰብ መንግስት እና ሕዝብን በማድኅየት ላይ የተሰማሩ ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ከሕዝብ የሚሰበሰበው ግብር በአግባቡ በሕዝብ አገልግሎት ላይ ከማዋል ይልቅ፤ የግል የተንደላቀቀ ሕይወትን መምሪያ የሚደያደርጉ ስለመኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ሕዝብ ይህንን ይጠላል። ነገር ግን በአደባባይ አይገልፀውም።
በሌላ በኩል ሕዝቡ የሚያደርገው ግብር አለመክፈል እና ማጭበርበር ላይ ያተኩራል። ስለዚህ በተለያየ መንገድ በተለይ ነጋዴው ግብር ይሠውራል። ያላወጣውን ወጪ እንዳወጣ አቅርቦ፤ ግብር እንዲቀነስለት ያደርጋል። ሕጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ እየቆረጠ ሽያጩ ዝቅተኛ እንደሆነ ያስመስላል። በዚህም መንገድ መክፈል ያለበትን ግብር ሳይከፍል ይቀራል። አንዳንዱ ግብር ሳይከፍል ወደ ሀብት ማማ ሽቅብ ይጋልባል። ይህ ሰው ምንም እክል ሳያጋጥመው እንደውም መንግሥት እና ሕዝብን እያጭበረበረ ከሁሉም በላይ ተከብሮ ዘመኑን ያሳልፋል።›› ብሎ በኢትዮጵያ ምድር ግብር ከመክፈል ይልቅ እንደውም ልዩ አክብሮት የሚሰጠው ግብር እያጭበረበረ ወደ ሀብት ማማ ለሚሮጥ ሰው እንደሆነ አስረዳ።
ተሰማ ግን ሃሰቡ ከዘውዴ እና ከገብረየስ በተቃራኒው የቆመ ነበር። ‹‹ሕዝብን በአንድ ላይ እንዳላዋቂ መቁጠር ተገቢ አይደለም። ሕዝብ ሳይሆን የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ግብር ላይ ያለው አቋም እናንተ እንደገለፃችሁት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ እንኳን ቢሆን በፍፁም ፍቃደኝነት ሁሉም ግብር እንዲከፍል ማስተማር ይገባል። ሕዝብም ሆነ ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ የውጪ ዜጋ እና የውጪ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ከሠሩ ግብር መክፈል አለባቸው። ግብር መክፈላቸው ግዴታቸው ነው።
ግብር ሲከፍሉ ደግሞ የቅርብ የኢትዮጵያ አጋር ሆኑ ማለት ነው። ነገር ግን በተለያየ መልኩ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ሲሰሩም ሆነ፤ ንግድ ሲከናወን በተገቢው መልኩ ግብር ያለመክፈል ሁኔታ ይስተዋላል። ይህንን ተገቢነት የጎደለው ድርገትን ማጋለጥ እና ድርጊቱን ፈፅመው የተገኙት ላይ እርምጃ የመውሰድ ክፍተት ሊያጋጥም ይችላል። እዚህ ላይ የመከራከር ፍላጎት የለኝም። ነገር ግን በምንም መልኩ የማልቀበለው። ‹ሕዝቡ በሙሉ ግብር ለመክፈል ከመነሳሳት ይልቅ ግብርን ማጭበርበር ላይ ትኩረት ይሠጣል።› የሚለው ሃሳብ በእኔ በኩል ፍፁም ተቀባይነት የጎደለው ነው።
በየትኛውም በኩል ክፍተት ይኖራል። ነገር ግን ክፍተቱ እንዳይኖር ከተፈለገ ሁሉም በየመስኩ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል። የአገር በጀት መሸፈንም ሆነ አገር ማደግ ያለባት በብድር እና በእርዳታ ሳይሆን በዋነኛነት ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር ነው። ሀገር ለማሳደግ ፒያኖ እንደመጫወት አይነት ንቅናቄ ያስፈልጋል። አስሩም ጣቶች መነቃነቅ አለባቸው፤ አስሩም ጣቶች በአንድ ጊዜ ከተጫኑ ዜማ አይወጣም። ያማረ ድምፅ፤ ያማረ ዜማና ቅላጼ እንዲወጣ አስሩም ጣቶች ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው መንቀሳቀስ አለባቸው። መንቀሳቀሳቸው ለሥራ እና ለዕድገት እንዲሆን ከተፈለገ ግብር መክፈል እና ማስከፈል ላይ ብቻ ሳይሆን የተሰበሰበው ግብርም በአግባቡ ሥራ ላይ እየዋለ መሆኑ መታየት አለበት።
ኅብረት፣ እንቅስቃሴ እና ሥራ ለእንቢተኝነት ወይም አንዱን በጠላትነት ለመፈረጅ መሆን የለበትም። በጠላትነት ለመፈረጅ ከሆነማ ኢትዮጵያን የማጥፋት አጀንዳ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ የጠላት ኃይሎች በምን ተለዩ? ፒያኖውን በደንብ ለመጫወት መማር አለባቸው ብለን የምናስባቸውን ወገኖች ማስተማር ይጠበቅብናል። ችግር ባለበት ሁሉ ጣታችንን በማንቀሳቀስ ችግር መፍታት፤ መፍትሔ ማምጣት እና አገር መለወጥ አለብን።
ነገር ግን ግብር በአግባቡ ካልተሰበሰበ መንግስት ሥራውን መሥራት አይችልም። ሥራ ካልተሠራ ደግሞ አገር አትቆምም። ስለዚህ የግብር ጉዳይ ተራ እና አልባሌ ነገር አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ እንደውም በልዩ ትኩረት መታየት ያለበት እና ባህል ሆኖ ሊቀጥል የሚገባው ጉዳይ ነው። ግብር አልከፍልም ብሎ መገዳደር ግን ልክ ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎት ያላቸውን የኢትዮጵያ ጠላቶችን አቋም እንደማራመድ ነው።›› ብሎ ግብር ያለመክፈል ጉዳይን ሀገር ከማፍረስ ፍላጎት ጋር አጣበቀው።
ዘውዴ ከት ብሎ ሳቀ። ‹‹አንተ ደግሞ አበዛኸው እንደው እያንዳንዱን ድርጊት ሀገር ከማፍረስ አጀንዳ ጋር ወስደህ ካጣበቅከው ሰዎች በምንም መልኩ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከለክል ከማስመሰሉም በላይ፤ አገር ማፍረስ እንደተራ ጉዳይ እንዲታይ ያደርጋል። መሠረታዊው ጉዳይ የጋራ ሕልም ነው። የጋራ ህልም እና ፍላጎትን እውን ለማድረግ ራስን መቻል ብቻ በቂ አይደለም፤ ሌሎች ወገኖቻችን ራሳቸውን እንዲችሉ እና መንገዱ ቀና እንዲሆን የሁሉም ትጋት ያስፈልጋል። ምንም እንኳ የራስን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ቢኖርም፤ ሌላውም እንዲሞላለት በጎነት ካልታከለ፤ በሌላ መስመር ክፋት ከጨመረ ደግ መዋል ከምኞት የዘለለ አይሆንም።
የተራበ በበዛበት ዓለም የጠገበ ተዝናንቶ አይኖርም። የጎደለበት በተበራከተበት ዘመን የሞላለት እንደፈለገ ቆሞ አይሔድም። ስለዚህ መፍትሔው በእርግጥም በዋናነት ግብር መክፈል ነው። ነገር ግን ደግሞ መዘንጋት የሌለበት ግብር ከመክፈል እኩል በተመጣጠነ መልኩ፤ ግብር ከፋዮችን ማበረታታት እና ግብር የማይከፍሉትን ወይም የሚያጭበረብሩትን ደግሞ እንደጠላት መቁጠር ሳይሆን በተገቢው መንገድ ማስተማር እና ወደ መስመር እንዲገቡ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚሁ ጋር ባልተለየ መልኩ ደግሞ የተሰበሰበው ግብር በአግባቡ ሕዝብን በተጨባጭ ለሚጠቅም ሥራ መዋል አለበት።
በሌላ በኩል ዋናው እና አንተም መካድ የሌለብህ ግብር ሰብሳቢው አካል ሃላፊነቱን ካልወሰደ ጉዳዩ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ እንደሚሆን አይነት ነው። ምክንያቱም ግብር ከፋዩ ግብር መክፈል እንዳለበት ቢያምንም የከፈለው ግብር በአግባቡ ሥራ ላይ ካልዋለ እና አጭበርባሪው የመንግሥት አካል ሲዘርፍ ካስተዋለ፤ አለመክፈልን እንደትክክለኛ ተግባር ሊወስደው ይችላል። መሰረታዊው ጉዳይ የሚሰበሰበው ግብር በአግባቡ ለሕዝብ በሚጠቅም ተግባር ላይ እንደሚውል ለአገር ጥቅም ካልዋለም መንግሥት ተጠያቂ እንደሚሆን አላፊነቱን መውሰድ ነው።›› አለ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹የእኔ ንግግር ቢያስቅም የአንተም አባባል ትንሽ ይከብዳል። ምክንያቱም መረጋገጥ የሚችል አይደለም። ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት መንግስት ነው ስትል መቼም ስለአንድ መሪ እየተናገርክ አይደለም። መንግስት ካልን በየተቋሙ መዋቅር ውስጥ ተሰግስጎ የሚሠራ አመራርንም ሆነ ባለሙያን የሚመለከት ነው። ግብር መክፈልን እያንዳንዱ በመንግሥት ተቋም ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ጋር አስተሳስረን እንየው ካልን ይቻላል። ነገር ግን ደግሞ አንድ ባለሙያ ወይም አመራር ስለዘረፈ ከግብር ጋር አስተሳስረን መንግስት ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት ካልን ከባድ ነው።›› በማለት ምላሽ ሰጠ።
ገብረየስ ደግሞ፤ ‹‹መሠረቱ ይኸው ነው። በእርግጥ ማንኛውም በሕግ ከተፈቀደለት ሰው ወይም ድርጅት ውጪ የሚሠራ በሙሉ ግብር መክፈል አለበት። ማለትም የግብር የእፎይታ ጊዜ ከተሰጣቸው አካላት ውጪ ሌላው የሚመለከተው ሁሉ ግብር የመክፈል ግዴታ አለበት። የተሰበሰበው ግብር ደግሞ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል። ይሔም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ዋናው ግን ግብር መክፈል ብቻ አይደለም።
ግብር መክፈል ተገቢ መሆኑንና ይህም አስተሳሰብ በሕዝብ ውስጥ መስረፅ እንዳለበት መተማመን ያስፈልጋል። ከዛም ሀገርን በማስተዳደር ላይ ያለ መንግሥት ከሕዝብ በግብር መልክ የሰበሰበውን ገንዘብ ደግሞ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ይጠበቅበታል። ይህ ሁሉ ካልሆነ መንግሥት ሕዝብን ግብር እንዲከፈል የማስገደድ መብት እንዳለሁ ሁሉ፤ ሕዝብም መንግሥትን የከፈለው ግብር ምን ያህል በአግባቡ ሥራ ላይ እንደዋለ የመጠየቅ መብት አለው። ችግር አለ ብለን ከተነሳን ችግሩ ያለው በሁለቱም በኩል ነው።
በሌላ በኩል የትኛውም ተቋም ግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ እያገለገለ ስለመሆኑ ማወቅ አለበት። ስለዚህ የግብር ክፈሉ ጥያቄ እንደሚቀርበው ሁሉ፤ ከሕዝቡ የሚቀርቡ የመገልገል ጥያቄዎችንም ተቋማት ምላሽ መስጠት አለባቸው። ሁሉም ጉዳይ ሰጥቶ መቀበል መሆኑን መርሳት አያስፈልግም።›› ብሎ ብድግ አለ። ለዛሬ በግሮሰሪው ባለቤት በተካሔደ ግብዣ ደረሰኝ አልጠይቅም። ከነገ ጀምሮ ግን ለከፈልኩት ክፍያ የትም ቢሆን ደረሰኝ እጠይቃለሁ ብሎ ሲስቅ፤ ሁለቱም ተከትለውት እየሳቁ ተነሱ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2015