«አገር የመጥላት ምኞት»

የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር አንድ ጓደኛዬን ስለግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ብቃት ጠየቅኩት። ለመጠየቅ የተነሳሳሁበት ምክንያት የግል ትምህርት ቤቶች ብቃት ያለው ተማሪ የሚወጣባቸው ናቸው ሲባል ስለምሰማ ነው። ልጅን የግል ትምህርት ቤት ማስተማር እንደመፎካከሪያ ስለሚቆጠር ነው።

እናም ይህ ከስድስት ዓመታት በላይ በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶች ያስተማረ ጓደኛዬ እንደነገረኝ፤ የአብዛኞቹ ወላጆች ፍላጎት ልጆቻቸው ውጭ አገር የመሄድ ዕድል እንዲያገኙ ነው። የተማሪዎቹም ምኞት ውጭ አገር መሄድ ነው። ወላጆች እንደ ትልቅ ስኬት የሚያዩት ልጆቻቸው ብቁ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ሆነው ውጭ አገር እንዲሄዱ ነው። ለዚህም ነው ከምንም በላይ ትኩረታቸው ቋንቋ ላይ የሆነው።

ይሄ ነገር የምር መሆኑን ደግሞ ከተለያዩ ገጠመኞች ማስተዋል እንችላለን። የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ናቸው የሚባሉት ሁሉ ሳይቀር ምኞታቸው ከኢትዮጵያ መውጣት ነው። ‹‹ይቺን አገር መገላገል ነው!›› የሚሉ ብዙ ናቸው። የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የተማሩ እና አገር ይለውጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ምኞታቸው ይሄ መሆኑ ነው።

ይህ ለምን ሆነ ? የአገር ፍቅር አጥተን ወይስ ስደተኛ ለመሆን የሚያበቃ በደል ደርሶብን ? ውጭ ሆኖ አገርን ለመጥቀም ወይስ የራስን ምቾት በማደላደል አገር የራሷ ጉዳይ በሚል ? ታዲያ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ የሰለጠነ ዜጋ የሚኖራት መቼ ነው ?

በቻይና ጉብኝት ያደረገ አንድ ኢትዮጵያዊ ሰሞኑን የጻፈውን ገጠመኝ አንብቤ ነበር። እንደ ጸሐፊው አገላለጽ፤ አስፋልቱ ላይ ምግብ ቢበላበት ለጤና የሚያሰጋ ነገር ያለው አይመስልም። ይህን ከመሰለ አገር የመጣ ቻይናዊ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ አቧራ ለብሶ፣ ጭቃ ተለውሶ እናየዋለን። ለምን? ለአገሩ መሥራት ስላለበት !

ወደ እኛ ስናመጣው ግን በተቃራኒው ነው። ይቺን ጎስቋላ አገር በምን ልገላገላት በሚል ነው። የግልና የቤተሰብን ምቾት ፍለጋ ነው። ይቺን ድሃ አገር እንዴት ላሳድጋት በማለት ሳይሆን እንዴት ልገላገላት በሚል ነው።

ግልጽ ግልጹን እንነጋገር ከተባለ ይህን የሚያደርጉት በብዛት የባለሥልጣናት እና የባለሀብት ልጆች ናቸው። የሚማሩት በውጭ አገር መስፈርት ነው፤ ውጭ አገር መኖርን ታሳቢ በማድረግ ነው። ስለአገር ፍቅር በየመድረኩ ቢናገሩም በተግባር ግን አያሳዩም፤ ራሳቸው የናቁትን የጤና እና የትምህርት ተቋማት ነው ሲያቆለጳጵሱ የሚውሉት። ልጆቻቸው የሰለጠኑ አገራት ውስጥ እንዲኖሩ ነው የሚፈልጉት። ታዲያ አገሪቱን ማን ያሰልጥናት ?

‹‹በሰለጠነ አገር ቢኖሩ ምን ችግር አለው?›› ይባል ይሆናል። ችግር አለው! ችግሩ ኢትዮጵያ የተማረ ዜጋ እንዳይኖራት ያደርጋል። አገር መመራት ያለባት አማራጭ ባጡ ዜጎች አይደለም፤ ወደሰለጠነው አገር ለመሄድ ዕድሉን ባላገኙ ሰዎች አይደለም። ዕድሉን በማጣት የሚሰሩ ሰዎች ውጤታማ ሥራ አይሰሩም። የግብር ይውጣ ሥራ ነው የሚሆን፤ የተሰላቸ እና የብሶት ሥራ ነው የሚሆነው። የመውጫ ዕድሉን እያመቻቸ የሚሰራ ሰው አገርን ሊያሰለጥን አይችልም።

እስኪ አንድ ነገር ልብ በሉ! አገር አቀፍ የፈተና ውጤቶች ይፋ ሲደረጉ ከፍተኛ ውጤት ያመጣ ተማሪ አጀንዳ ይሆናል። በወቅቱ የሚሰጡ አስተያየቶች ‹‹አደራ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይቀር›› የሚል ነው። ዕድሉን አታበላሹበት ውጭ አገር ይሂድ የሚል ነው። የተማረ፣ የተመራመረና ጎበዝ ሰው ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የለበትም ማለት ነው እንግዲህ !

በሰለጠነው አገር የተሟላ ነገር ስላለ የፈጠራ ሰው እዚያ ቢሄድ የተሻለ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ዳሩ ግን ለአገር በሚጠቅም መንገድ ተምሮ እንዲመጣ ወይም እዚያ በተማረው አገሩን እንዲያገለግል መባል ሲገባው፤ የሚባለው ግን ጭራሽ ወደ ኢትዮጵያ ፊቱን ማዞር እንደማይገባው ነው።

በነገራችን ላይ በውጭ አገር ቆይተው አገራቸውን ለማገልገል ያሰቡትም አልተሳካላቸውም። ከዓመታት በፊት በቱሪዝም ጉዳይ ላይ ከዲያስፖራዎች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ታድሜ ነበር፤ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ሲዘረዝሩ ተስፋ ቢቆርጡ አይፈረድባቸውም ያሰኛል። አንድ የህክምና ባለሙያ ደግሞ በአንድ ሚዲያ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ በሙያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ነገር ለማስጀመር አስበው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ተስፋ ቆርጠው ነው የተውት።

አገር የምትለወጠው ከትንንሽ ነገሮች ጀምሮ እስከ ግዙፍ ተቋማት ድረስ በተማረ ኃይል ነው። በየዘርፉ ብቁ ባለሙያ መኖር አለበት። በትምህርት ውጤታማ የሚሆኑ ሰዎችን ለውጭ አገራት መገበር ከሆነ፤ ታዲያ ኢትዮጵያ መቼ ነው ወደ ከፍታ የምትሄደው?

አገርን ለማሰልጠን ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። ቢያንስ አንድ ትውልድ ጨክኖ ዋጋ መክፈል አለበት። ሁሉም የግል ምቾቱን ብቻ የሚፈልግ ከሆነ ስደትን ብቻ የሚመኝ ዜጋ ይኖረናል። የሰለጠኑት አገራት ከምን ተነስተው ነው እዚህ ላይ የደረሱ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

የአገር ፍቅር በተግባር ማለት የመድረክ ዲስኩር አይደለም። ‹‹ውቢቷ፣ ለምለሟ›› የሚል ዘፈን በየመድረኩ ማስጮህ አይደለም። የአገር ፍቅር ዋጋ በመክፈል ሲገለጽ ነው ውጤት የሚያመጣው። አገርን ያህል ነገር ‹‹ምናባቱ!›› ማለት አደገኛ ስንፍና ነው።

ወደ ውጭ መሄድን ታሳቢ አድርጎ መኖር አሰልቺ ያደርጋል። በትንሽ ትልቁ ብሶተኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። የውጭውን ዓለም ብቻ እየተመኙ የራስን ለመጥላት ያስገድዳል። ካላስተሳሰቡት ግን ምኞት ሁሉ አገርን ለማገልገል ይሆናል። ምንም እንኳን ለአገር ይህን አደረኩ የምለው ባይኖረኝም ‹‹ዲቪ›› የሚባል ነገር ሞልቼ አላውቅም። የአገር ፍቅር አለኝ ብየ ለመመጻደቅ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሳስበው ገደል ሆኖ ስለሚታየኝ ነው። ይድረሰኝ አይድረሰኝ ባይታወቅም ቢያንስ ግን አገሬን የመሸሽ ምኞቱ የለኝም። ምኞቴም አገሬ እንድትለወጥ እንጂ እኔ ወደተለወጡት ሄጄ መገላገል አይደለም፤ የጅልነት የአገር ፍቅር የሚል ይኖር ይሆናል።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ውጭ አገር ሄደው በተሟላ ሁኔታ አይማሩ ማለት አይደለም፤ ዳሩ ግን ኢትዮጵያን ለመገላገል በሚል ስሜት የሚደረጉ ስደቶች ራስ ወዳድነት ናቸው። ደግሞስ ምን አድርገው አየን ? የብዙ ባለሥልጣናትና ባለሀብት ልጆች ውጭ አገር አሉ፤ ዳሩ ግን በአገር ደረጃ ይህን አደረጉ ሲባል አልሰማንም። ስለዚህ አገርን ሳይሆን ራስንና ግፋ ቢል ቤተሰብን ነው እያገለገሉ ያሉት።

ልብ ብላችሁ ከሆነ የአንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልጆች ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ተመረቁ ሲባል አጀንዳ ይሆናል። ያልተለመደ ስለሆነ ማለት ነው። አንዳንዱ በማድነቅ፣ አንዳንዱ ደግሞ ባለሥልጣኑን እንደ ሞኝ በማየት ይነጋገሩበታል። መሆን የነበረበት ግን የባለሥልጣን ልጅ በአገሩ ተምሮ አገሩን የሚያገለግል ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህን ያደረጉ ባለሥልጣናት ምሥጋና ይገባቸዋል።

ለመሆኑ ግን ቆራጥነቱ ካለ ኢትዮጵያ ውስጥ መማር የኢትዮጵያን ሀብት ለመጠቀም ያንስ ነበር ? ሥርዓተ ትምህርቱን ከኢትዮጵያ ነባራዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር ማስኬድ ውስብስብ ነገር ነበር ? የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ምንም ባልተማሩት አርሶ አደሮች እንኳን አይመረትም ነበር? በማህበራዊም ይሁን ተፈጥሯዊ ሀብቶች ምርምር ተደርጓል ?

እሺ ግዴለም! በውጭ አገር መማሩም ክፋት የለውም! ዳሩ ግን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም የሚያስችል ዕውቀት ተገኝቶበታል? ስንት ምርምር ሰሩ? የትኛውን ጥሬ ሀብት ወደ ምርት ቀየሩልን? እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎች በራሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሰዎች የሚሰሩ ናቸው።

የብዙ ሰዎች ምኞት አገር ጥሎ መሄድ እየሆነ ነው፤ ትልልቅ የሚባሉ ሰዎችን ምክራቸው ይሄው ነው። የትምህርት ግቡ ውጭ አገር ለመኖር ከሆነ፤ ታዲያ ኢትዮጵያ የተማረ አልባ ትሁን ?

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015

Recommended For You