የቢሾፍቱ ሪጂዮ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደር፤ ኩሪፍቱ፣ ቢሾፍቱ፣ ባቦጋያ፣ ሆራ አርሰዲ፣ መገሪሳ፣ ኪሎሌ እና ጨለለቃ የሚባሉ ሐይቆች የሚገኙባትና የቱሪስቶች መዳረሻ ከተማ መሆኗ ይታወቃል። በተቸራት ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ፣ ባላት ምቹ የሆነ የአየር ፀባይ፣ እንዲሁም በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት መዳረሻነቷ ትታወቃለች። ከአዲስ አበባም በ47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የቱሪስ መናኸሪያ ናት።
በኢትዮጵያ የባቡር መሰረተ ልማት እውን መሆንን ተከትሎ ከተቆረቆሩና በሂደትም ካደጉ ከተሞች መካከል አንዷ መሆኗ የሚነገርላት ቢሾፍቱ፤ በ1917 ዓ.ም እንደተመሰረተች መረጃዎች ያሳያሉ። ቢሾፍቱ የሚለውን ሥያሜ ያገኘችውም ከተማዋ በርካታ ሀይቆች እንደሚገኙባትና የእነዚህ ሀይቆች መገኛም በተራራዎች መካከል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሆኑ ነው የሚገለጸው። ቢሾፍቱ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል ሲሆን፣ በአማርኛ ‹‹በውሃ የበለፀገች›› የሚል ትርጓሜ አለው።
በዛሬው በተጠየቅ አምዳችንም የቢሾፍቱ ሪጂዮ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደር ባለፈው በጀት ዓመት ምን አከናወነ፤ እንደ ከተማ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እና ችግሮቹን ለማቃለል እየተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት ዙሪያ የከተማዋ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ጋር ያደረግለውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ አበይት ክንውኖች ምንድን ነበሩ?
አቶ አለማየሁ፡-በበጀት ዓመቱ በርካታ ተግባራትን አከናውነናል። በተለይም ደግሞ የከተማዋ ዕድገት በሚያፋጥኑ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገን ሠርተናል። በዚህም አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል። በበጀት ዓመቱ በትኩረት በመሥራታችን በ2014 በጀት ዓመት ከነበረው አፈጻጸማችን በላቀ ሁኔታ ውጤታማ ለመሆን ሠርተናል። በ2015 በጀት ዓመት በዋናነት የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የሥራ ፈጠራ እና የንግዱን ማህበረሰብ ማንቀሳቀስ፣ ዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓትን መተግበርና የከተማዋ እድገት ሊያፋጥኑ በሚያስችሉን መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን ስንቀሳቀስ ነበር።
በአጠቃላይ ሲታይ የከተማ አስተዳደሩ የሚቀጥሉትን 10 ዓመታት ማዕከል ያደረገ ፍኖተ ካርታ ነድፎ እየሠራ ነው። ከ10 ዓመቱ እቅድ ደግሞ የአምስት ዓመት ብሎም የበጀት ዓመቱ እቅድ ተነድፎ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል። አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ለመሆናቸው በምግብ ዋስትና እና ሌሎች ዘርፎች ያከናወናቸው ተግባራት ምስክር ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በምግብ ዋስትና ምን የተለየ ተግባር ሠርታችሁ ነው ለውጤታማ አፈጻጸማችሁ እንደ አብነት ሊጠቅሱት የቻሉት?
አቶ አለማየሁ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች አንዱና ዋነኛው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። እኛ ደግሞ እንደ ከተማ አስተዳደር ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምን መሥራት አለብን? ለዚህስ እንደ ከተማ ያለን ፀጋ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ነበረብን። በዚህም መሰረት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደምንችል አረጋጥናል። ለአብነትም በዶሮ እርባታ የሠራነው ሥራ ከከተማ አስተዳደሩ ባለፈ እንደ ክልል የሚጠቀስ፤ ምናልባትም እንደ ሀገርም ተምሳሌት የሚሆን ሥራ ነው ያከናወነው።
ምክንያቱም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሠራነው ሥራ በዓመት አንድ ሚሊዮን ጫጩቶችን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ፈጥረናል። በዚህ ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል። አሁንም አመርቂ ተግባራት በመከናወን ላይ ሲሆኑ፤ በዓመት ብቻ 12 ሚሊዮን ጫጩቶችን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። ይሄ ማለት ደግሞ በዚህ ዘርፍ ያሉትን ዕድሎች በሰፊው መጠቀም መጀመራችንን የሚያሳይ ነው። በአጠቃላይ የሥጋ እና የእንቁላል ዶሮችን በማርባት ረገድም ተስፋ ሰጪ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የሥጋ እና የእንቁላል ዶሮችን በማርባት የተገኘው ውጤት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለወተት ምርትም በልዩ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በዚህም ዘርፍ በተሠራው ሥራ ብዙ ውጤቶች የተገኙ ሲሆን፤ ለአዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞችም የሚተርፍ ምርት እየተመረተ ነው። የተገኘው አበረታች ውጤትም ዘላቂ እንዲሆን ለማስቻል ከተናጥል ይልቅ በክላስተር እንዲከናወኑ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- የወተት እና የእንቁላል ልማት ክላስተር በምን መልኩ የሚከናወን ነው?
አቶ አለማየሁ፡– እንደ ቢሾፍቱ ከተማ በተበታተነ መንገድ ሳይሆን በተደራጀ መንገድ የዶሮ እርባታ ሥርዓት እየተዘረጋ ነው። በዚያው ልክ ለገበያም ማቅረብ እየተቻለ ነው። በተበታተነ ሁኔታ የሚሰሩ ሥራዎች ለክትትልም ሆነ ለድጋፍ አይመቹም። በመሆኑም ይህን ማስቀረት የሚችል ሥርዓት ነው የዘረጋነው። በወተትም ተመሳሳይ ሥራ ነው የተከናወነው።
በክላስተር አደረጃጀት 10 ወረዳዎች ያላቸው አቅም የተለየ ሲሆን፤ በየትኛው አካባቢ ምን ላይ ማተኮር አለብን ብለን በጥናት ለይተን ወደ ሥራ ገብተናል። በዚህም መነሻ የወተት ክላስተር፣ የዶሮ እርባታና የመሳሰሉት ክላስተሮችን መፍጠር ችለናል። በውጤታማነት ሲታይም በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም በእንቁላል፣ በሥጋ እና ወተት ክላስተር የተሰሩ ሥራዎች ለሌሎችም አካባቢዎችም ተምሳሌት ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡- ቢሾፍቱ ከተማን ከመዝናኛ እና ቱሪዝም ከተማነት ባሻገር በሌላ ገጽታ ለማስተዋወቅ ምን ሃሳብ አላችሁ?
አቶ አለማየሁ፡– የቢሾፍቱ ከተማ ዋነኛ መለያዋ ቱሪዝም ነው። ይህን እኛ የበለጠ ማጠናከር እንጂ በሌላ ሁኔታ ገጽታዋን መቀየር አላሰብንም። ነገር ግን ከቱሪዝም ጎን ለጎን በጣም ከፍተኛ አቅም መኖሩ መታወቅ አለበት። ይህን አቅም መጠቀም ስለሚገባ እየሠራንበት ነው። ከተማዋ ሁሉንም አቅምና ፀጋ ያካተተች ናት። በቱሪዝም ትታወቃለች።
ይሁንና በከተማዋ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች የሚካሄዱባት በመሆኗ ትኩረት መሳብ ችላለች። በእንቁላል፣ በሥጋ እና ወተት ክላስተር በጉልህ እየሠራንበት ያለው ሥራ ከቱሪዝሙ ጎን ለጎን ማደግ አለበት። ሥራውም አንዱ ሌላውን የሚመግብ፣ አብሮ የሚያድግም ዘርፍ ነው። በአጠቃላይ የተናበቡ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው እያከናወንን ያለነው። በመሆኑም ከቱሪዝም ጎን ለጎን ኢንቨስትመንቱም እያሳደግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢንቨስትመንቱ አንዱ የትኩረት መስካችሁ ከሆነ፣ አሁናዊ የከተማዋ ኢንቨስትመንት ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አለማየሁ፡– በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አንድ ሺህ 600 ኢንቨስትመንቶች እየተከናወኑ ሲሆን፤ የከተማዋ መለያ በሆነው ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎች በርካታ ናቸው። በዚህም የቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ መዳረሻ ከመሆኗ በተጨማሪ፤ የጎብኚዎችን ቀልብ የምትስብ ሆና ከፍተኛ ገቢ እየተገኘ ነው። የከተማዋ አስተዳደርም በቀጣይ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚይዙ ማራኪ አሠራሮችን እና መሰረተ ልማቶችን እያሟላ ነው።
ይህ ኢንቨስትመንት ደግሞ በየጊዜው እያደገ ሲሆን፤ በዚህም የከተማዋ ገቢም እያደገ ነው። ለምሳሌ፣ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 18 ሪዞርቶች አሉ። እነዚህ ለበርካታ ሺህ ዜጎች ሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ ለከተማዋ ገቢም የአንበሳውን ድርሻ እያበረከቱ ነው። ይህ ለከተማዋ ትልቅ ፋይዳ አለው። በቀጣይም ከእነዚህ በተጨማሪ የከተማዋ ገፅታ የሚያሳምሩና የማልማት አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የሀይቆች ዳርቻ የኢንቨስትመንት ቦታዎች ተዘጋጅዋል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የሚገኙት አንድ ሺህ 600 ኢንቨስትመንቶች አሉ ብለዋል። ታዲያ ሁሉም በሥራ ላይ ናቸው?
አቶ አለማየሁ፡- ሁሉም ኢንቨስትመንቶች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ናቸው ብሎ መናገር አይቻልም። በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ካሉ አንድ ሺህ 600 ኢንቨስትመንቶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ የገቡት 44 ከመቶ የሚሆኑት ናቸው። አንዳንዶቹ ግንባታ ጀምረው ያቆሙ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ በሂደት ላይ ናቸው፤ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ አልገቡም። ምርት ጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው ልክ ያልሄዱ አሉ። ስለዚህ በከተማዋ ውስጥ ያሉት ኢንቨስትመንቶች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ናቸው ማለት አይቻልም። ነገር ግን ወደ ሥራ በትክክል እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።
እንደ ከተማ አስተዳደር በርካታ ድጋፎችና ክትትሎች ይደረጋሉ። ይሁንና ይህን መጠቀም ያልቻሉ አሊያም በአግባቡ ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉትን መታገስ ባለብን ደረጃ እንታገሳለን። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ህጋዊ እርምጃ እንወስዳለን። አንዳንዶቹ ከሚገባው በላይ እየተጓተቱ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚፈጥሩ ናቸው፤ እነዚህ የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ስለሚሆኑም ፈቃዳቸው ይሰረዛል። የተወሰነ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የሚገቡ ካሉ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ ያደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- ምንም እንኳን አንዳንዶቹ በሙሉ አቅም ምርት የሚያመርቱ ነው ቢባልም፤ እነዚህ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንቱ ከሚፈልገው በላይ ቦታ አስፋፍተው ስለመያዛቸው ይነገራል። በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ አለማየሁ፡- ከዓመታት በፊት ሰፋፊ ቦታዎችን የያዙ ኢንዱስትሪዎች እንደሚኖሩ ይታመናል። አንዳንዶቹ ይህን ያደረጉት የማስፋፊያ ቦታ እጥረት እንዳይገጥማቸው በሚል በጎ እሳቤና ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ የማይሰሩበትን ቦታም ቢሆን በሰፊው ለመያዝ ከማሰብ የመነጨ ነው። እኛ የትኛው ኢንዱስትሪ
ምን እየሠራ ነው የሚለውን ለይተናል። እንደተባለው ከኢንቨስትመንታቸው ባህሪ አኳያ ያልተናበበ እጅግ የተለጠጠ መሬት የያዙትን ያለአግባብ የያዙ መሆናቸውን በማስገንዘብ ለተገቢው ጥቅም እንዲውል እየተደረገ ነው።
ሌላኛው ከኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ውጭ ያልተፈቀደ ቦታ አስፋፍቶ የመያዝ ዝንባሌ አለ። ይህ አግባብነት የጎደለው ከመሆኑም አልፎ የሀብት ብክነት የሚያስከትል ነው። ይህ ልምምድ እንደከተማ አስተዳደር የምንታገሰው አይደለም። በመሆኑም በህግ አግባብ የሚጠየቁ ይሆናል። ከተፈቀደው ውጪ የያዙትንም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ከተማ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት ትኩረት መሰጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሥራው የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ አድርጓል ማለት ይቻላል?
አቶ አለማየሁ፡- እኛ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ስንሰጥ ለከተማዋ ብሎም እንደ ሀገር ጥቅሙ ምንድን ነው የሚለውን ደጋግመን አይተን ነው። በተለይም ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆን አለበት። በተጨማሪም ለከተማዋ ገቢ የሚያመጣ መሆንም ይጠበቅበታል።
ከዚህ አኳያ በቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ቀላል አይደለም። የፈጠረው የሥራ እድልም በዚሁ ልክ ሰፋ ያለ ነው። በአንዳንድ ሆቴሎች እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች አሏቸው። በዚህ ልክ ለመናገር የሚያስችል ሥራዎች ናቸው የሚከናወኑት። እነዚህም ሥራዎቹ ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረጉ ለመሆናቸው ማሳያ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የሆቴሎችና ሪዞርቶች ግንባታዎች በሀይቆቹ ዙሪያ በቅርበት ስለተገነቡ፣ በሀይቆቹ ላይ ብክለት እያስከተሉ መሆናቸው ይነገራል። በዚህ ላይስ ምላሽዎ ምንድን ነው?
አቶ አለማየሁ፡- የከተማዋን የቱሪዝም ፍሰት ታሳቢ በማድረግ በርካታ የሆቴል፣ ሎጆችና ሪዞርቶች ፈቃድ ተሰጥተዋል፤ በመሰጠትም ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት እስከ አምስት ኮከብ የሚደርሱ ውብ መዝናኛ ሆቴሎች ተገንብተዋል። እነዚህም ለሀገሪቱም ጭምር ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ ነው። ከተማዋም በርካታ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያ መዳረሻቸው እያደረጓት የምትገኝ ከተማ መሆኗ ይታመናል። በዚህም ከተማዋ ትልቅ ሀብት እያመጣች መሆኑን በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው።
ይሁንና በሀ ሀይቆች ዳርቻ የተገነቡ ሪዞርቶች ጉዳት እያደራሱ ነው የሚለው በተወሰነ ደረጃ የሚያስማማ ጉዳይ ነው። አንዳንዶቹ ወደ ሀይቆቹ በጣም ተጠግተው የተገነቡ በመሆናቸውና ‹‹በፈር ዞን›› የምንለውን ጭምር የኢንቨስትመንታቸው አካል አድርገው እየተጠቀሙበት ነው። ይህ አግባብ እንዳልሆነ እንረዳለን። ሆኖም ቀደም ሲል ግንባታ አከናውነው የነበሩትን አካላት የያዙትን ቦታ በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው። ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ በህግ አግባብ የሚጠየቁ ናቸው። በሀይቆቹ ላይ አግባብ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀም ካለ ወይንም ለሚያደርሱት ብክለት የከተማ አስተዳደሩ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል።
አዳዲስ የሚሰጡ ፈቃዶች ግን ከባለፉት ጋር በፍጹም የሚመሳሰል አይደለም። ‹‹በፈር ዞኖች›› አይነኩም፤ ይልቁንም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። ሀይቆቹንም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል። በዚህ ላይ የከተማ አስተዳደሩም ከባለሀብቶች ጋር በተለያዩ መድረኮች ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ መግባባት ላይ ተደርሷል። በአጠቃላይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ሲሰጡ የከተማዋን ፀጋ በኃላፊነት መጠቀም በሚያስችል ሁኔታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የቢሾፍቱ ሃይቆች የህዝብ ሃብት ቢሆኑም በዚህ አካባቢ መዝናናት የተፈቀደለት የገንዘብ አቅሙ ከፍተኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳም ይነሳል። ይህን ለማስተካከል ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ አለማየሁ፡- ሀይቆቹ የሀገር ሀብት ናቸው። ይህን ሀብት ደግሞ በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው። በእርግጥ ዙሪያውን የተገነቡት ሪዞርቶችና ሆቴሎች አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች አይጠቀሙም የሚለው ያስማማል። ይሁንና ግን ሀይቁ የጋራ ሀብት በመሆኑ መጠቀም የሚችሉበትን ዕድል መንፈግ አይገባም። አንዳንዶቹ ለመግቢያ ጭምር እንደሚያስከፍሉ ይታወቃል። ይህ አግባብ አለመሆኑን ተገንዝበናል። በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በምን ሁኔታ መቃለል አለባቸው የሚለው ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት አለበት።
ሕዝብ የሚጠቀምበትና በሀይቆቹ ዙሪያ ሊዝናናበት የሚችልበት ዕድል መፈጠር አለበት። ይህን ለማድረግ ደግሞ ነፃ የሆነ አካባቢ ለሁሉም መፍጠር ይገባል። ይህን ለማድረግም መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል። በተለይም አዳዲስ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሰጥ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግና ከቅሬታ የፀዳ መሆን አለበት። ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ከተማዋን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ቢሉም፤ የመሬት ወረራ ግን ለከተማዋ ፈተና እንደሆነባት ይነገራል። እዚህ ላይስ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ አለማየሁ፡- አዎ! በከተሞች አካባቢ አንድ የተለመደ አካሄድ አለ። በተለይ ውስን እና ውድ የሆነው የመሬት ሀብት ለመቀራመት የሚደረግ ከፍተኛ ትግል አለ። የመሬት ወረራ አሳሳቢ ነው። እንደቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ይህ ፈተና ሆኖብናል። ነገር ግን እጃችን አጣጥፈን አልተቀመጥንም። ህጋዊ ያልሆኑ ግንባታዎች ሲገኙ እርምጃ እንወስዳለን፤ በመውሰድም ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- ከሕገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ ያከናወናችሁት ሥራ አለ?
አቶ አለማየሁ፡– በበጀት ዓመቱ ሕገ ወጥ ግንባታን በመከላከል ረገድ በሰፊው ሠርተናል። ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ በተመለከተ በሁለት ወረዳዎች በሰፊው የተስፋፋ ሲሆን፤ ይህም ሕጋዊ መንገድን በተከተለ አካሄድ እርምጃ ወስደናል። ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ለመከላከል በተደረገው ጥረትም 2ሺ500 ሕገ ወጥ ቤቶችን አፍርሰናል።
የከተማ አስተዳደሩ ሕገ ወጥ ግንባዎችን አይታገስም። መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው። ይህ ውስን ሀብት ደግሞ በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። በመሆኑም ሕገወጥ ግንባታዎችን ማስቆም ከተገነቡም ማፍረስ አለብን። ከማስተር ፕላን የሚቃረኑ ግንባታዎች መፍረሳቸው የከተማዋን ዕድገት አይጎዳም። በመሆኑም ከማስተር ፕላን የሚቃረኑ ግንባታዎችን እናፈርሳለን።
አዲስ ዘመን፡- መሬት በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ የከተማዋን መሬት በካሬ ከአምስት ብር እስከ 10 ብር ለመኖሪያ ቤት በሚል በሊዝ የተሰጠ ስለመሆኑ መረጃዎች ደርሰውናል። ይህ አግባብ ነው?
አቶ አለማየሁ፡– በካሬ በዚህ ደረጃ የሚሰጥ መሬት የለም፤ ይህ ውሸት ነው። በከተማዋ ለመኖሪያ በሚል በሊዝ የሚሰጥ መሬት አሁን የለም። ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ቆሟል። ይህ አሠራር ለሙስና የሚያጋልጥ በመሆኑ አዲስ አሠራር መከተል ግድ ብሏል። አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን መሬት በአግባቡ መጠቀም አለብን። ይህን ማስከበር ደግሞ የተወሰኑ አካላት ለብቻቸው የሚወጡት ሳይሆን ሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት።
እኛ እንደ ከተማ አስተዳደር ይሄ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል የፀና እምነት አለን። በዚሁ መሠረትም አዋጆችን፣ ደንብና መመሪያን እየተገበርን ነው። ከሙስና የጸዳ አሰራር ለመዘርጋት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። በበጀት ዓመቱ በዚህ ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውነናል።
አዲስ ዘመን፡- ሰላምና ፀጥታ ለከተማዋ ልማት እጅግ ወሳኝ ከመሆኑ አኳያ ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሠራ ነው?
አቶ አለማየሁ፡– እውነት ነው። የአንድን ከተማ ወይንም አካባቢ እድገት ከሚወስኑ ጉዳዮች መካከል ሰላምና መረጋጋት ነው። እኛም የከተማችን ዕድገት ለማፋጠን በቅድሚያ ትኩረት የሰጠነው ለፀጥታው ነው። በመሆኑም ኅብረተሰቡን እንዴት የሰላሙ አካል ማድረግ ይቻላል በሚል እቅድ ነድፈን እየሰራን ነው።
በዚህም በሦስቱም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ኅብረተሰቡ ቀዳሚ የሠላም አምባሳደር እንዲሆን መዋቅሮች ተዘርግተዋል። ማህበረሰቡ ከፖሊስና ሌሎች ጸጥታ አስከባሪዎች ጋር እንዴት መተባበር አለባቸው የሚለውም በራሱ እቅድ የሚመራ ነው። ይህ በአግባቡ በመከናወኑም በአንፃራዊነት ከተማዋ በበጀት ዓመቱ ሰላማዊ ሆናለች።
ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ሸኔ እና ሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ከከተማዋ ወጣ ብሎ ቢሆንም ጥቃት ለማድረስ ሙከራ አድርገዋል። በከተማዋ ውስጥ ለእነዚህ አካላት ሎጂስቲክስ ለማቀበልና በመረጃ ለመመገብ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች የሉም ማለት አይቻልም። ይሁንና ግን እነዚህ ጥቂት አካላት ከሰላም ወዳዱ ማህበረሰብ የተሰወሩ አይደሉም፤ ከአቅም በላይ ናቸው የሚል እምነትም የለኝም። በመሬት ላይ ያለው እውነታም ይህ ነው።
የከተማዋን ኢንቨስትመንት ለማሳደግና ቱሪዝሙን የበለጠ ለማጎልበት ፀጥታው ትልቅ ድርሻ ስላለው በትኩረት እየሠራን ነው። በአጋጣሚ ሆኖ ከተማዋ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮችም ያሉባት ከተማዋ ናት። ከሕዝቡ ጎን ሀገር ወዳድ ሠራዊት ያለበት በመሆኑ በዚህ ደረጃ የሚያሰጋ ችግር የለም። ምናልባት በከተማዋ የጠላት ሕዋስ ቢኖር እንኳን ዓላማቸውን ማሳካት የሚችሉበት ዕድል የለም።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ከተማ አስተዳደር አሁናዊ ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አቶ አለማየሁ፡– ከተሞች በርካታ ፈተናዎችን ያስተናግዳሉ። እንደ ቢሾፍቱ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ የሚስተዋሉ ፈተናዎች እኛ ዘንድም ይኖራሉ። መሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታና የመሳሰሉትን ችግሮች መጥቀስ ይቻላል። ነገር ግን ችግሮች አሉ ብለን አንቀመጥም። በየጊዜው መፍትሄው ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ እየተመካከርን እንሰራለን።
ከዚህም ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች አሁን ላይ የሉም። አዳዲስ ችግሮች ናቸው። ለእነዚህም እንደየሁኔታው ምላሽ በመስጠት ነው የምንሄደው። ፈተናዎች ሁሌም አሉ፤ እኛም ሁሌ መፍትሔ አለ ብለን እናቅዳለን፤ እንፈተዋለንም። በመሆኑም ባለፈው በጀት ዓመት ያሉትን ችግሮች በማረም፤ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የምንሠራ መሆኑንም እግረ መንገዴን መጠቆም እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ በአንባብያን ሥም አመሰግናለሁ።
አቶ አለማየሁ፡- እኔም ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015