ዝርክርክ አሰራር ዝርክርክ ስም ይፈጥራል

ከነዋሪነት መታወቂያ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ወደ አንድ የወረዳ ወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት ሄድኩ። ከስድስት ወራት በፊት (ዕለቱ ቅዳሜ ነበር) ስሄድ በጣም ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት አግኝቼ ስለነበር ያንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው የሄድኩት። እንዲያውም ከዚያ በፊት በቀልድም በቁም ነገርም በተለምዶ ‹‹ቀበሌ›› የሚባሉት በአሰራር መጓተት ሲወቀሱ ነበር የምሰማ። ያንን ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘቴ በጣም አመስግኜ እንደ ቀልድ የተለመደውን ወቀሳ ስኮንን ቆይቻለሁ።

ከወራት በኋላ ስሄድ ግን ያንን ወቀሳ የሚያስታውስ አሰራር ነው ያጋጠመኝ። ከገጠመኝ ልነሳ ብዬ እንጂ ይህ አይነት አሰራር ግን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባሉ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እየገነገነ የመጣ ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአሰራር ቅልጥፍና ከፍተኛ አድናቆት ቢያገኝም ዳሩ ግን ወደኋላ የሚጎትቱ አሁንም ያልተቀረፉ አሰራሮች አሉ። ወደ ትዝብቴ ልሂድ።

ገና ወደ ግቢው ስገባ መቆሚያ መቀመጫ የለም። ሰዓቱ ወደ 4፡00 የተጠጋ ስለነበር ስብሰባ ነገር ኖሮ ለሻይ እረፍት የወጡ ነበር የመሰለኝ። ተጠግቼ ሳይ ግን ሁሉም ባለጉዳይ ነው። ሰልፍ መስሎኝ ልሰለፍ ሳስብ የሰልፍ አደራደር የለውም፤ ዝም ብሎ የተደበላለቀ ነገር ነው። የትኛው ጉዳይ የት ጋ እንደሆነ አይታወቅም። የት ጋ ሆኜ ልሰለፍ? የሚነበብ ነገር ስፈልግ በየግድግዳው ላይ የሚታየኝ የማይተገበር መፈክር ነው!

ሦስት ሆነው ለብቻቸው ፈንጠር ብለው የሚያወሩ ሰዎችን፤ ያ ሁሉ ሰው ለምን ጉዳይ እንደመጣ ጠየቅኳቸው። ጥያቄዬ ልክ እንዳልሆነ የገባኝ ጥያቄዬን በጥያቄ ሲመልሱልኝ ነው። የዚያን ሁሉ ሰው ጉዳይ እንዴት ያውቃሉ ብዬ ነበር? እኔ ምን እንደምፈልግ ጠየቁኝ። ነገርኳቸው። እስኪ ግባና ጠይቅ አሉኝ። የወረፋ ችግር የለውም ማለት ነው ብዬ አመስግኜ ገባሁ።

ገና በሩ ላይ ስደርስ ውጭ ላይ የገረመኝ የሰው ብዛት ከውስጥ ደግሞ የባሰ ነው። አግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጡ አሉ፣ የቆሙ አሉ፣ መቆም ሰልችቷቸው ወለሉ ላይ ቂጢጥ ብለው የተቀመጡ አሉ። አንድም ባለጉዳይ ወደ ውስጥ እንዳይገባ በባለጉዳይና በሠራተኞች መካከል ትልቅ ገመድ ተወጥሯል። ሠራተኞችን ማናገር ሳይሆን ማየት ብቻ ነው የሚቻለው። የእኔን አይነት ባለጉዳይ ካለ ብዬ አጠገቤ ያሉትን ሁሉ ብጠይቅ የኔን አይነት ጉዳይ አጣሁ። የተቀጠርኩት ደግሞ ከዚሁ ቢሮ ነው።

የሚተረማመሰው ሰው ከጠረጴዛ ላይ እየተሻማ ወረቀት ያነሳል፤ የሚሞላ ቅጽ ነገር መሰለኝ። እሺ እኔስ ምን ይሻለኛል? የምጠይቀው ሰው አጣሁ። ገመዱን ዘልዬ አልሄድ ነገር እንዳልሄድ ነው የተወጠረ። ቢጨንቀኝ ስም ይጠራ ይሆን? በሚል የየዋህነት ግምት ገመትኩ። ሁሉም ሠራተኞች ቁጭ ብድግ እያሉ ይተረማመሳሉ፤ ወረቀት ያነሳሉ ያስቀምጣሉ። የትኛው ጉዳይ የት ጋ እንደሆነ አይታወቅም።

እንዲህ እየተወዛገብኩ አንዲት ወጣት ሠራተኛ የጠረጴዛውን ወረቀት የሚያገለባብጡትን ልትቆጣ የተወጠረው ገመድ አጠገብ መጣች። ግርርር ብለው አጠገቧ አሰፈሰፉ። ሌላ ወረቀት ፕሪንት ተደርጎ ይመጣል ተቀመጡ አለቻቸው።

በዚህ መሃል እንደምንም ተሰራስሬ ለቀጠሮ የተሰጠኝን ወረቀት ሰጠኋት። ገና ዓይኗን ወደ ወረቀቱ ስትሰድ አንዱ መጥቶ ሌላ ወረቀት ይሰጣታል፣ ሌላኛው መጥቶ የሆነ ነገር ይጠይቃታል። በእኔ ላይ ተደርበው የየራሳቸውን ጉዳይ ይጠይቃሉ። እሷም አንድ ጊዜ እኔን እያዋራች፣ አንድ ጊዜ ለአንደኛው መልስ እየሰጠች ተዋከበች። የተቀየረ አሰራር ስላለ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እያስረዳችኝ ድንገት አንዱ ይመጣና ያናጥላታል። ሌላኛው ሌላ ወረቀት እጇ ላይ ያደርጋል፤ ብዙ ግራ ገብቶት የቆየ ሰው ነበር ማለት ነው። እንደምንም እየተዋከበች የነገረችን፣ የነገረችኝን ብቻ ይዤ ዘወር አልኩ፤ ምክንያቱም ተጨማሪ ጥያቄዎችና በቂ ማብራሪያ የሚገኝበት የተረጋጋ ሁኔታ የለም። የዕለቱ ጉዳዬ በዚህ ተቋጨ።

ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? ለምን ግልጽ መረጃ አይነገርም? የትኛው ጉዳይ የት ጋ እንደሆነ ቢያንስ በጽሑፍ እንኳን ለምን አይገለጽም? በሠራተኞችና በባለጉዳይ መካከል ያ ሁሉ ርቀት ካለ ባለጉዳዮች እንዴት መረጃ ሊያገኙ ይችላሉ? ለስድስት ወር የተቀጠረ ሰው የተቀያየሩ አሰራሮችን በምን ያውቃል? ማን ወረፋ መጠበቅ እንዳለበት፣ ማን ያለቀለት ወረቀት ይዞ እንደሚሄድ… በአጠቃላይ የትኛው ጉዳይ የትና እንዴት መሆን እንዳለበት መረጃ የሚሰጥ አካል መኖር አለበት፤ ምክንያቱም በብዙ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ እንዲህ አይነት ቀልጣፋ አሰራር አይተናል።

በአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት የሚደገፉ ተቋማት መድረኮችን ሲያዘጋጁ ከምቀናባቸው ነገሮች አንዱ ሰዓት አጠቃቀም ቅልጥፍናቸውን ነው። ሀገር ውስጥ ያሉ እነዚህ ተቋማት በመሥሪያ ቤታቸው የሚሰጡት አገልግሎትም የተቀላጠፈ ነው። መድረክ ሲዘጋጅ የጊዜ ሰሌዳ (Schedule) ይዘጋጃል። እያንዳንዱ ፕሮግራም የሚከናወነው በተቀመጠው ሰዓት ልክ ነው። መንግሥታዊ በሆኑ ተቋማት ግን እንኳን ሰዓቱ የተጻፈው ፕሮግራም ራሱ የሚቀናነስ ይኖረዋል፤ ምክንያቱም ሰዓቱ ባክኗል።

ከሰለጠኑት ሀገራት መኮረጅ የነበረብን እንዲህ አይነት ሥልጣኔዎችን ነው። አገልግሎትን ማቀላጠፍ የሰዎች የመሰልጠን ምልክት ነው። በዚህ በረቀቀ የቴክኖሎጂ ዘመን ዛሬም ኋላቀር አሰራር ላይ ነን። ኋላቀር ሲባል የግድ የመገልገያ ዕቃዎችን ዘመናዊነት አይደለም፤ የሰዎችን የአመለካከትና የቅንነት ዘመናዊነት መኖር አለበት። በአንዳንድ ሠራተኞች ዘንድ ቅንነት ራሱ የለም። አንዲት ገጠመኝ ልጥቀስ።

አገልግሎት መስጫ ተቋሙ በር ላይ ብዙ ባለጉዮች ተሰልፈዋል። አንደኛዋ ሴትዮ (ሠራተኛ) እየገባች ነው። የሚገርመው የገባችው ራሱ ከ2፡30 በኋላ ነው። አንድ የመንግሥት ሠራተኛ (የሕዝብ ማለት ነው) 2፡30 የሥራ ገበታው ላይ መገኘት አለበት። አለመገኘቷ ብቻ አይደለም ችግሩ። ልክ ስትደርስ በሩ ላይ ባለጉዳይ ይተረማመሳል።፡ ፊቷን ኮስተር አድርጋ በተሰላቸ ወኔ ‹‹ነጋላቸው ደግሞ!›› አለች።

እንደዚች ሴትዮ እምነት እነዚያ ባለጉዳዮች የመጡት እሷን ለማስቸገር እንጂ ጉዳይ ኖሯቸው አይደለም። እዚያ የተሰለፉት ሥራ ፈት ሆነው እንጂ ጉዳዩ አስገድዷቸው አይደለም። እሷ ቁጭ ብላ ከባልደረቦቿ ጋር አሉቧልታ ታወራ ዘንድ እነዚህ ሰዎች እሷን ሥራ ማስፈታት አልነበረባቸውም። ይሄ መሆን አለበት እንግዲህ ያናደዳት። ሲገቡ በስንት ጸሎትና ስለት ይገቡና በኋላ ግን እንዲህ ግዴለሽ ይሆናሉ።

ይህንን ስል በባለጉዳዮች ላይ ያለውን ችግር ያልታዘብኩት ሆኖ አይደለም፤ እንዲያውም በተገልጋዩ አለመሰልጠን ላይ የጻፍኩት ትዝብት ይበዛል። ከምንም በላይ የሚያስገርሙት ደግሞ የሚፈለገውን መረጃ ሳያሟሉ መጥተው አገልግሎቱን ካልሰጣችሁኝ ብለው የሚጣሉት ናቸው። አሰራሩ በማይፈቅደው መንገድ አገልግሎቱን ካልሰጣችሁኝ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ናቸው። ሥራ እንዲጓተትና የተዝረከረከ አሰራር እንዲሰፍን የሚያደርጉ እነዚህ ናቸው። በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት ያለበት የሚገባው ሰው አብሮ ለመጉላላት ይገደዳል ማለት ነው።

እንደ አገልጋይም እንደ ተገልጋይም ብዙ ይቀረናልና ከሰለጠኑት ተቋማትና ተገልጋዮች ዘመናዊነትን እንማር!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 10/2015

ዶናልድ ትራምፕና ሌሎች 18 ሰዎች የጆርጅያ ምርጫን ለማጭበርበር በመሞከር ተከሰሱ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጆርጅያ ግዛት የተደረገውን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ አሲረዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከእርሳቸው በተጨማሪ ሌሎች 18 ግለሰቦችም በዚሁ የክስ መዝገብ ተካተዋል። ይህ ክስ በዚህ ዓመት ብቻ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተመሰረቱ ክሶችን ወደ አራት ከፍ አድርጓቸዋል።

ለቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመፋለም የተዘጋጁት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉንም ክሶች እንደማይቀበሏቸው ገልጸዋል። በዚህ የክስ መዝገብ ከትራምፕ ጋር ከተከሰሱት ሰዎች መካከል የቀድሞው የትራምፕ ጠበቃ፣ የቀድሞው የዋይት ሃውስ ኃላፊ እና የቀድሞው የፍትህ ሚንስትር ይገኙበታል።

የተመሰረተባቸው ክስ “በማወቅ እና ሆን ብለው የምርጫ ውጤትን ለመቀልበስ በመተባበር” የሚል ነው ።

በዚህም ምክንያት ተከሳሾችን “የወንጀል ድርጅቶች” በማለት ክሱ የሰየማቸው ሲሆን፣ የሀሰት ጽሑፍ በማዘጋጀት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን በግል በመደለል፣ በሐሰተኛ ሰነድ ዝግጅት፣ ታዛቢዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር፣ ኮምፒውተርን በመሰለል እና ስርቆት የመሳሰሉ ክሶች ተካተውበታል።

ከእነዚህ ክሶች መካከልም ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኘ ሰው እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጡ የወንጀል ድርጊቶች ተካተውበታል። ይህ የቅጣት ድንጋጌ የተቀመጠው የምርጫ ተወዳዳሪዎች በማፊያዎች እና በሕገ ወጥ ቡድኖች ታግዘው የምርጫ ውጤትን እንዳይቀለብሱ ለመከላከል ነው።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ቀዳሚ ዕጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የተመሰረተባቸው ክስ ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው ነው ብሏል።

ይህም የሆነው የ2024 የትራምፕን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ለማስተጓጎል መሆኑን የትራምፕ የሕግ ክፍል ገልጿል።

“ይህ ወገንተኛ በሆነው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዓቃቤ ሕግ የተቀነባበረው ክስ በአሜሪካውያን ዘንድ እምነት ከማሳጣቱም በላይ የሀሰት ክስ ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ገፊ ምክንያት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል” ብሏል የትራምፕ የሕግ ክፍል ባወጣው መግለጫ።

ትራምፕ ቀደም ሲል በዋሽንግተን የነበረውን የምርጫ ውጤት ለመቀልበስ አሲረው ነበር በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ትራምፕ በ2021 የጆርጅያን አስተዳዳሪ ባይደንን ለማሸነፍ የሚያስችላቸውን 11 ሺህ 780 ድምጽ እንዲፈልግላቸው ሲጠይቁ በስልክ ተቀድተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 10/2015

Recommended For You