ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ማን ነው?

ዲፕሎማሲ “ዲፕሎማ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን፤ በግሪክ ቋንቋ ዲፕሎማ ማለት የታጠፈ ወረቀት ማለት ነው። በቀድሞ ጊዜ መንግሥታት የሚፃጿፋቸው መረጃዎችና ስምምነቶች እንዲሁም ለግለሰቦች የሚሰጡ የምስክርና የፈቃድ ወረቀቶች ዲፕሎማ ይባሉ ነበር። በአሁኑ ወቅት ዲፕሎማሲ የሚለው ቃል ለውጭ ግንኙነት መገልገያ ወይም መጠሪያ እያገለገለ ይገኛል።

ዲፕሎማሲ ጥንታዊ ከሚባሉ ሙያዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነው። የቀድሞ ነገሥታት መልእክተኞቻቸውን ወደ አቻቸው በመላክ የዲፕሎማሲ ሥራ ያከናውኑ ነበር። የዲፕሎማሲ ሥራ ውስብስብ ክስተቶችን በዘዴ ለመወጣት የሚያግዝ ከመሆኑ በተጨማሪ የሰላም መሣሪያም ነው። ዲፕሎማሲ መፋጠጥን፣ መካረርንና ወደ ጦርነት ማምራትን ይከላከላል።

በመሆኑም ዲፕሎማሲ የውጭ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ሲሆን፤ በሰላማዊ መንገድ የሀገርን ጥቅም ማስከበሪያ ነው። ዲፕሎማት ደግሞ የዲፕሎማሲ ተግባር የሚፈጽም ሰው ነው። ይሄ ዲፕሎማት ደግሞ ዲፕሎማሲን የመከወን አቅምና ብቃትን ሊላበስ የተገባ ነው። የዛሬው ጽሑፌ ትኩረትም እዚሁ ላይ እንደመሆኑ፤ “አንድ ዲፕሎማት ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ምን ምን ሲያሟላ ነው?” የሚለውን ጉዳይ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።

የሀገራችንን ፖሊሲ ጠንቅቆ የሚያውቅ

በዓለማችን ላይ ያሉ መንግሥታት ከሚከተሉት የመንግሥት ሥርዓት አኳያ የተቀረፀ የውጭ ፖሊሲ አላቸው። የውጭ ፖሊሲ የአንድ መንግሥት የግንኙነት መመሪያ ሲሆን፤ ይህም በሀገር ውስጥ ተግባራዊ የሆነው ፖሊሲ ነፀብራቅ ነው። እነዚህ ፖሊሲዎች ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ፤ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሳይንስ እና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው።

እናም ዲፕሎማቶች እነዚህን የሀገራቸውን ፖሊሲ ጠንቅቀው ማወቅና ለሌሎችም ማሳወቅ አለባቸው። በተለይ በፖለቲካ ዘርፍ የሚካተቱትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚካተቱትን የኢንቨስትመንትና የውጭ ንግድ ፖሊሲ በጥልቀት ማወቅ አለባቸው።

ለምሳሌ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰነድ ለአንድ ዲፕሎማት ወሳኝ እና ጠቃሚ የሥራ መመሪያ ነው። በሰነዱ ውስጥ የተካተቱት ዝርዝር መረጃዎች ካልታወቁ ዲፕሎማቶች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ለሌላ ሀገር ሊሰጡ ይችላሉ። በተመሳሳይ የሀገራችንን የኢንቨስትመንት እና ሌሎች ወሳኝ ፖሊሲዎችን ጠንቅቆ ማወቅ ዲፕሎማቶች በተመደቡበት ቦታ የሚገኙ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ያግዛቸዋል።

ከዚህም ባሻገር አንድ ዲፕሎማት የተመደበበትን ሀገር የውጭ ፖሊሲ ማወቅ ይጠበቅበታል። ለአብነት ያክል ቻይና የአንድ ቻይና(One China Policy) የሚል ፖሊሲ አላት። ለቻይና ሀገር የተመደበ አንድ ዲፕሎማት ይህንን ካላወቀ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሸው ይችላል።

ሀሳቡን በጥሩ ቋንቋ መግለፅ የሚችል

በዓለማችን ላይ ከሰባት ሺህ በላይ ቋንቋዎች እንደሚገኙ ምሁራን ይገልጻሉ። አንዳንድ ቋንቋዎች በርካታ ሕዝብ የሚናገራቸው ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እጅግ በጣም ጥቂት ሰዎች የሚናገሯቸው ናቸው። ለአብነት፣ በቅኝ ግዛት ወቅት የቀድሞ ኃያላን ሀገራት ቅኝ የያዙት አካባቢ ቋንቋቸውን አስፋፍተዋል። በተለይ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ቋንቋቸውን በበርካታ አፍሪካና እስያ ሀገሮች ውስጥ አስፋፍተውታል። የዚህ ቋንቋ ተናጋሪዎች የቡድን ስሜትም እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። በአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ እንደሚታየው ፍራንኮፎን እና አንግሎፎን የሚል ስሜትን ፈጥረዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሥራ ቋንቋም በአብዛኛው ከቅኝ ገዢዎች ቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው። እንግሊዝኛ፤ ፈረንሳይኛ፤ ስፓኒሽ፤ ፖርቹጋል የሥራ ቋንቋ የሆኑት ከቅኝ ገዢዎች ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ አረብኛ እና ሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች የአፍሪካ ህብረት የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ተደንግጓል።

ለዚህ ማሳያው እ.ኤ.አ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2022 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በ35ኛው መደበኛ ጉባኤ ስዋሂሊ ቋንቋ የአፍሪካ ህብረት ስድስተኛው የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ወስኗል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የሚጠቀምባቸው የሥራ ቋንቋዎች ስድስት ሲሆኑ፤ እነዚህም አረብኛ፣ ቻይንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ፈረንሳይኛ፣ ሩሲያኛ እና ስፓኒሽ ናቸው።

በቀድሞ ጊዜ ፈረንሳይኛ የዲፕሎማሲ ቋንቋ እንደሆነ ተደርጎ በርካታ ሀገሮች ይጠቀሙበት ነበር። ከጊዜ በኋላ እንግሊዝኛ ወደቀዳሚነት ደረጃ መጥቷል። ሀገራችን ለአረቡ ዓለም ቅርብ እንደመሆኗ መጠን አረብኛ ቋንቋ ማወቅም ጠቃሚ ነው። እነዚህን ቋንቋዎች የሚያውቅ ዲፕሎማት በበርካታ ሀገሮች ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ለመግባባት ያግዘዋል።

ብዙ ቋንቋዎችን ለማወቅና ለመጠቀም አስቸጋሪ ቢሆንም፤ አንድ ዲፕሎማት የተመደበበትን ሀገር ቋንቋ ማወቁ ግን ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ቀድሞውኑ የሚመደበው ዲፕሎማት ከሚያውቀው ቋንቋ ተናጋሪ ሀገር ጋር እንዲሰራ ቢደረግ መልካም ነው። ይህ ካልሆነ ግን የተመደበበትን ሀገር ቋንቋ መማርና መሥራት ይጠበቅበታል።

ጥሩ የመግባባት ክህሎት ያለው

የዲፕሎማሲ ሥራ በቢሮ ተቀምጦ ብቻ የሚሠራ ሥራ አይደለም። ዲፕሎማቶች በተመደቡበት ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ጋር በመገናኘት የብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ ሥራ ሊያከናውኑ ያስፈልጋል። እነዚህ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች በፖለቲካው፤ በኢኮኖሚው ወይም በማህበራዊ ዘርፍና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ።

እናም ወደእነሱ በመሄድ ስለሀገራችን ፖሊሲ እና አቋም ማስረዳት ያስፈልጋል። የእነሱንም በመስማት በጋራ ሊያሰራ የሚችልባቸውን ጉዳዮችን መለየትና የትብብር ሥራ መሥራት ያስችላል። ለምሳሌ፣ ኢንቨስተሮች ወደሀገራችን መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከተፈለገ የሀገራችንን የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማስረዳትና ሊያገኙ የሚችሉትን ትርፍ ማሳየት ይጠይቃል። ይህንን ለማከናወን ግን ዲፕሎማቶች የመግባባት ክህሎታቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይገባል።

መግባባት ማለት ቋንቋ ከማወቅ ያለፈ ነው። አንድ ዲፕሎማት የተለያዩ ቋንቋዎችን ቢያውቅም ለሥራ ካልተጠቀመበት ቋንቋ ከማያውቀው ዲፕሎማት ጋር ልዩነት የላቸውም። ለዚህ ነው አንድ ዲፕሎማት የመግባባት ክህሎት እንዲኖረው የሚያስፈልገው። ለመግባባት ዲፕሎማቶች ወደ ሌሎች ሰዎች በመሄድ እራሳቸውን የማስተዋወቅና አድራሻ በመቀያየር ተከታታይ ግንኙነት ማድረግ አለባቸው። በእኛ ባህል የማያውቁትን ሰው መተዋወቅና ማነጋገር “ዓይን አውጣ” ያስብላል። ይህ አስተሳሰብ ግን በዲፕሎማሲ ሥራ ቦታ የለውም።

ዲፕሎማቶች የተለያዩ ግብዣዎችን (Receptions) ይጋበዛሉ። ግብዣውን ተቀብለው የሚሄዱ ያሉ ሲሆን፤ የማይሄዱም አሉ። እነዚህ ቦታዎች ግን የምግብና የመጠጥ ብቻ ሳይሆኑ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራባቸው ሥፍራዎች ናቸው። በአብዛኛው የሚስተዋለው ግን በግብዣ ቦታ የአንድ መሥሪያ ቤት ሰዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው ሲወያዩ ነው። ይህ ውይይት ከሥራ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፤ ግን የሌሎች ሀገሮችን ዲፕሎማቶች የማግኘትና የመወያየት እድልን ይነጥቃል።

ምክንያቱም የቢሮ ሥራ በቢሮ ውስጥ ሊሰራ ይችላል፤ የዲፕሎማሲ ሥራ ግን በቢሮና ከቢሮ ውጭ የሚሰራ እንደመሆኑ የግብዣ ጊዜን ለዲፕሎማሲ ሥራ መጠቀም አስፈላጊ ነው። በተለይ የአውሮፓ ሀገር ዲፕሎማቶች በግብዣው ሰዓት እየተዘዋወሩ አዳዲስ ሰዎችን ይተዋወቃሉ፤ መረጃም ይቀያየራሉ።

የተመደበበትን ሀገር ሕግና ባህል የሚያከብር

የተለያዩ ሀገሮች የራሳቸው የሆነ ሕግና ባህል አላቸው። እነዚህ ሕጎችና ባህሎች በራሳቸው ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለዲፕሎማሲ ሥራም ወደ ሀገራቸው የገቡ ዲፕሎማቶች እንዲያከብሩት የሚጠበቅ ነው። እ.ኤ.አ በ1961 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቬይና ዓለም አቀፍ ሕግን በማውጣት ስለዲፕሎማሲ ሥራ እና ስለዲፕሎማሲ ግንኙነት በዝርዝር ደንግጓል። ይህ ህግ እ.ኤ.አ በ1965 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፤ ሀገራችንም የዲፕሎማሲውን ኮንቬንሽን እ.ኤ.አ መጋቢት 22 ቀን 1979 ተቀብላ በሥራ ላይ አውላዋለች።

በዚህ ኮንቬንሽን አንቀጽ 41 ላይ እንደተደነገገው ዲፕሎማቶች ልዩ መብት ያላቸው ቢሆኑም የተመደቡበትን ሀገር ሕግና ደንብ የማክበር ግዴታ አለባቸው ይላል። ለአብነት ያክል በብዙ አረብ ሀገራት የአልኮል መጠጥ አይሸጥም፤ አይጠጣም። ይህ ሕግ ከውጭ ሀገር በገቡ ዲፕሎማቶች ሊከበር የግድ ይላል። የተመደቡበትን ሀገር ሕግ የማያከብሩ ዲፕሎማቶች ከሀገር ሊባረሩ ይችላሉ።

ይሄን ታሳቢ በማድረግም አንዳንዴ የተመደቡበትን ሀገር ሕግና ደንብ ባለማወቅ ስህተት እንዳይሠራ ወደ ተመደቡበት ሀገር ከመሄዳቸው በፊት ዲፕሎማቶች ስለሀገሩ ማንበብና እንደ አስፈላጊነቱ ስልጠና (Cross- Cultural Communications) መውሰድ አለባቸው። ምክንያቱም ስህተት ከተሠራ በኋላ እንደዚህ አይነት ሕግና ደንብ ወይም ባህል እንዳለ አላውቅም ማለቱ አያድንምና ነው።

በዓለም አቀፍ ሕግ ለዲፕሎማቶች የተሰጠን መብትና ግዴታ ጠንቅቆ የሚያውቅ

የተባበሩት መንግሥታት የቬይና ዓለም አቀፍ ሕጎችን(The Vienna Convention on Diplomatic Relations፣ Vienna Convention on Consular Relations ) ሲደነግግ በውስጡ በርካታ መብቶችና ግዴታዎችን ለዲፕሎማቶች አስቀምጧል። በመሆኑም እነዚህን ሕጎች መጣስ ያስጠይቃል።

ታሪክ የሚያሳየን ይህን መሰል የዓለም አቀፍ ሕግ ከመውጣቱ በፊት ዲፕሎማቶች በተመደቡበት ሀገር ውስጥ በርካታ በደሎች ሲደርሱባቸው ነበር። ዲፕሎማቶች የመንግሥታቸውን መልእክት ይዘው ሲሄዱ ተቀባይ መንግሥት መልእክቱ ካላስደሰተው የተላከውን ዲፕሎማት ወይም መልእክተኛ የማሰር፤ የመግረፍና የከፋ በደል የማድረስ ተግባር ተከናውኗል።

ይህ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ግንኙነትን ስለጎዳ ነው የቬይና ሕጎች የወጡት። ስለዚህ ዲፕሎማቶች፤ ባለቤቶቻቸውና በውጭ ኤምባሲ የሚሰሩ የአስተዳደር ሠራተኞች ያላቸውን መብትና ግዴታ ማወቃቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ሕግን አለማወቅ ከጥፋተኝነት አያድንም የሚባለው ለእዚህም ይሰራል።

ለሀገር ክብርና ጥቅም ጠንክሮ የሚሰራ (Patriot)

አንድ ዲፕሎማት ውጭ ሀገር ተመድቦ ሲሰራ የሚወክለው የራሱን ማንነት( ሃይማኖት፤ ብሔር፤ ጾታና ቋንቋ እና ወዘተ) አይደለም። ሀገሩን ወክሎ ነው የሚሰራው። ስህተት ሲሰራም እገሌ የሚባል ሰው ይህንን መጥፎ ሥራ ሰርቷል አይባልም፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ይህንን ሕገወጥ ሥራ ሰርቷል ነው የሚባለው። ስለዚህ በእርሱ/እሷ ስህተት የሱ/የእሷ ስም ሳይሆን የሀገር ስም ነው የሚጠፋው ወይም የሚወቀሰው።

አንድ ዲፕሎማት ሀገርን ይወክላል ሲባልም፣ ለሀገር ክብርና ጥቅም የሚቆምና የሀገር ፍቅር ያለው (Patriot) ሊሆን ይገባል ማለት ነው። የሀገር ፍቅር ከሌለው በጥቃቅን ጥቅማጥቅም የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ለሌሎች ሊሰጥ ይችላል። ከዚህም በከፋ መልኩ ሀገሩን ክዶ ወደሌላ ሀገር ይሰደዳል።

በርግጥ ከሀገር የተሰደዱ ዲፕሎማቶች በሙሉ የሀገር ፍቅር የሌላቸው ናቸው ብሎ ሙሉ በሙሉ መደምደም ባይቻልም፤ የሀገር ፍቅር ያለው ግን ማናቸውንም ጫና እና ተጽእኖ ተቋቁሞና ወደሀገሩ ተመልሶ ሥራውን ይሰራል የሚል እምነት አለኝ።

ለስደት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ ከነዚህም ውስጥ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፣ የቤተሰብ ተጽእኖ፣ የዲያስፖራ አማላይ ስበት እና ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። የሀገር ፍቅርና ክብር ያለው ግን ሀገሩን አይከዳም። ችግርም ካለ ወደሀገሩ ተመልሶ መፍትሔ ያፈላልጋል። ይህን አማራጭ ሞክሮ ሳይሳካለት ቢቀርና የዲፕሎማትነቱን ሥራ አስረክቦ የሚሰደድ ካለ፤ ቢያንስ በዲፕሎማትነት ከተመደበበት ሀገር ጠፍቶ ጥገኝነት ከሚጠይቀው የተሻለ ነው እላለሁ።

እኔን የሚገርመኝ ግን የሀገሩ መንግሥት አምባሳደር ብሎ የሰጠውን የክብር ስም ሀገር ክዶ በሌላ ሀገርም ሲኖር አምባሳደር ተብሎ መጠራቱ ነው። ሀገር ከድቶ በውጭ ሀገር የሚኖር ዲፕሎማት እድሜ ልኩን አምባሳደር ተብሎ መጠራት አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ርዕስ ግን አከራካሪ ሊሆን ይችላል።

በሥራ አጋጣሚ በእጁ የሚገኙ ሀገራዊ ሚስጥሮችን የሚጠብቅ

የዲፕሎማሲ ሥራ ሂደት ውስጥ በርካታ የሀገር ሚስጥሮች በዲፕሎማቶች እጅ ሊገባ ይችላል። እነዚህ መረጃዎች ቢወጡ በሀገሮች መካከል ያለን መልካም ግንኙነት ሊያሻክሩ ይችላሉ። ከዚያም ባለፈ ጦርነት ሊያስነሱ፤ ሀገርን ሊቀይሩ የሚችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንዳይሰሩ ወይም እንዳይጠናቀቁ ሊያደርጉ ይችላሉ። በመሆኑም አንድ የሀገራችንም ይሁን የውጭ ሀገር ዲፕሎማት ብቁ ዲፕሎማት ነው ከሚያሰኘው ተግባር ውስጥ አንዱ በተለያዩ አጋጣሚዎች እጁ የሚገቡ ሚስጥሮችን የመጠበቅ ነው።

አንዳንድ ሚስጥሮች የሚወጡት ሰነዶችን በአግባቡ ካለመያዝና “ከቸልተኝነት” ሊሆን ይችላል። አንዳንድ መረጃዎች ደግሞ የሚወጡት ሆን ተብሎ ሊሆን ይችላል። ከአልኮል መጠጥ ስካርና ተቃራኒ ጾታ ጋር በሚደረግ የስለላ ተግባር ጋር በተያያዘም መረጃዎች ሊወጡ ይችላሉ። ስለዚህ የአንድ ዲፕሎማት ሥነ ምግባር ለእራሱ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩም በበጎም ይሁን በመጥፎ መልኩ ይተርፋል።

ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችለውን በቂ መረጃና ንባብ የሚያከናውን

አሁን ያለንባት ዓለም የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ በየጊዜው ሲቀያየር እናስተውላለን። መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች ናቸው የሚባሉት ተጋጭተው ለጦርነት ሲፈላለጉ እናያለን። በተቃራኒው ደግሞ እነዚህ ሀገሮች በቃ ወደ ጦርነት መግባታቸው አይቀርም የተባሉት ደግሞ መልካም ግንኙነት ፈጥረዋል ሲባል ይሰማል።

ይህ የሚያሳየው የዓለም ሁኔታ እጅግ ተቀያያሪ መሆኑን ነው። ዲፕሎማቶች ይህንን ተቀያያሪ ሁኔታ የሚከታተሉና የሀገራችንን ጥቅምና ጉዳት የሚያዩበት መነጽር ሊኖራቸው ይገባል። ለዚህም አንድ ዲፕሎማት አንባቢና ወቅታዊ ጉዳዮችን በንቃት የሚከታተል ሊሆን ይገባል። በዚህ ረገድ ለዲፕሎማቶች የሚሰጥ የአቅም ግንባታ መኖርም ይህንን መሰል ችግሮች ለመፍታት ያግዛል።

አንድ ከሃያ አመት በፊት ዲፕሎማት የሆነ ሰው ከሃያ አመት በፊት ባገኘው የዲግሪ ትምህርት እውቀት ላይ ብቻ ተሞርኩዞ የሚሰራ ከሆነ በርካታ ስህተቶችን በመሥራት ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዳ ተግባር ሊያከናውን ይችላል። ስለዚህ አንድ ዲፕሎማት የራሱን እውቀት በየጊዜው ማሻሻል አለበት። በርካታ የሀገራችን ዲፕሎማቶች በዲፕሎማትነት በተመደቡበት ሀገር ከሥራ ሰዓት ውጭ ባለው ሰዓታቸው በመማር ራሳቸውን የቀየሩና ያበቁ የመኖራቸውን ያህል፤ ይህንን እድል ያልተጠቀሙም ይኖራሉ።

እነዚህ “አንድ ዲፕሎማት ብቁ ዲፕሎማት የሚባለው ምን ምን ሲያሟላ ነው?” በሚል ማዕከላዊ ጥያቄ መነሻነት የጠቃቀስኳቸው ነጥቦች ስለ ጉዳዩ መረዳትን እንደሚፈጥሩ አምናለሁ። ለዛሬው ያለኝ ሃሳብም ይሄው ሲሆን፤ በሌላ ጊዜ በሌላ ሃሳብ እንደምመለስም ከወዲሁ ቃል በመግባት ነው። እስከዛው ሰላም፡፡

 ከመላኩ ሙሉዓለም ቀ.

(በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የውጭ ግንኙነት ተመራማሪ)

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 10/2015

Recommended For You