ሞዴሊንግ ከሙያ ባሻገር

ስለፋሽን ስናነሳ ሞዴሊንግን ማንሳት የግድ ይለናል። የፋሽንና ሞዴሊንግ ሙያ ተመጋጋቢ የሆኑ ሙያዎች ናቸው፡፡ ፋሽን የምንላቸው በዲዛይነሮች አምረው የሚሠሩ ነገሮች ሲሆኑ፤ እነዚህ የፋሽን ዲዛይነሮች የሠሯቸው ሥራዎች ለእይታ ለማብቃት ደግሞ የሞዴሊንግ ሙያ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ፋሽን ዲዛይነሮች የሚሠሩትን አልባሳት፣ ጫማዎችን እና ቦርሳዎችን ያለ ሞዴሎች ሊተዋወቁ አይችሉም፡፡

እነርሱ ለብሰውና ተጫምተው እንዲሁም አንግተው ባማረ ውበትና አረማመዳቸው በአደባባይ ሲያቀርቡላቸው ነው እውቅናን አለያም ሽያጭ የሚያገኙት፡፡ በተለይ ሥራዎች በፋሽን ትርኢት እንዲቀርቡና እንዲታዩ ማድረግ ካስፈለገ ሞዴሎች የግድ ያስፈልጋሉ ፡፡

የሞዴሊንግ ሙያ ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ ቁመትና ውበት ስላለ ብቻ የሚከወንም ሊሆን አይችልም፡፡ እውቀትን ትምህርትን ይፈልጋል፡፡ እንደ አንድ የሙያ መስክ ሠልጥኖ የሚወጣበትም ነው፡፡ እናም በፋሽን ዲዛይነሮች የሚሠሩ የፋሽን ሥራዎች ለእይታ ለማቅረብ የሞዴሊንግ ሙያ በእጅጉ አስፈላጊ ነውና ሙያውን እውቀትም፤ ችሎታም፤ ውበትም እንደሆነ መረዳት ግድ ነው፡፡

ሞዴሎች ለፋሽን ዲዛይነሮች የጀርባ አጥንት ናቸው። ሥራዎቻቸውን ለእይታ በማቅረብ ከማስተዋወቅ ባለፈ እውቅና እንዲኖራቸው ያደርጓቸዋል የሚለው አፍሮ ፊገር ሜካፕና ሞዴሊንግ ስኩል መሥራችና ባለቤት ሞዴል አብረሃም ዮሐንስ ነው፡፡ ሞዴል አብረሃም እንዳለው፤ የሞዴሊንግ ሙያ የተለያዩ ለገበያና ለግል አገልግሎት የምንጠቀማቸውን እቃዎች ሳይቀር የሠራው ድርጅቶች ጭምር በመወከል የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ለማስተዋወቅ (ፕሮሞት) እና ለመሸጥ የምንጠቀምበት ሙያ ነው፡፡

የሞዴሊንግ ሙያ ከፋሽን ጋር ብቻ ሳይሆን ከማርኬቲንግ ጋርም ተያያዥነት ያለው ሙያ ነው፡፡ ሙያው እራሱን የቻለ ቁመትና ተክለ ሰውነት የሚያስፈልገው ቢሆንም ከዚያም ባሻገር እውቀትን ይጠይቃል፡፡ ማንኛውም ሰው በሞዴሊንግ ሙያ ሊሳተፍ እና ሞዴል ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በተለምዶ በሞዴሊንግ ሙያ ላይ የሚሳተፉ ቁመታቸው ረጃጅም የሆኑ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይህ አመለካከት በተለምዶ የሚባል እንጂ እውነት ላይ የተመሠረተ አይደለም ይላል፡፡

ሰዎች ይህንን እንዲሉ ያደረጋቸው ቀደም ሲል የነበረው የሞዴሊንግ ሙያ አሠራር እንደሆነ የሚያነሳው ሞዴል አብረሃም፤ በዘርፉ የሚሳተፉ ረጃጅም ሞዴሎች ስለነበሩ አሁንም ያ ብቻ መስፈርቱ እንደሆነ ስለሚታመን ነው፡፡ ነገር ግን የሞዴሊንግ ሙያ ከዚያም ባሻገር ነው። የሞዴሊንግ ሙያ 23 አይነት ንዑስ ክፍሎች አሉት። ስለዚህም በእነዚህ ሁሉ ንዑስ ክፍሎች ውስጥ ሰዎች ተሳትፈው ሞዴል መሆን ይችላሉ ብሏል፡፡

እንደ ሞዴል አብረሃም ማብራሪያ፤ ለአብነት ፋሽን ትርኢት ላይ የምናያቸው ራንአዌ ሞዴሊንግ (Runaway modeling) የሚባሉ ሞዴሎችን ነው፡፡ እነዚህ ሞዴሎች በአብዛኛው የሚሠሩት የፋሽን ትርኢት ሥራዎችን ነው፡፡ እንዲሁም ፔቲቲ ሞዴሊንግ (petiti modeling) የሚባሉ ደግሞ በተቃራኒው አሉ፡፡ ቁመታቸው አጭር የሆኑ ሞዴሎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ የጫማ ማስታወቂያዎችን ለመሥራት የሚሳተፉበት ነው፡፡ እናም እንደ ንዑሳን ክፍሎቹ አይነት የሞዴሊንግ ሥራውም ይለያያል፡፡ እያንዳንዳቸው ሞዴሎች የሚፈለጉበት ጊዜ እና የሥራ አይነትም አለ፡፡

ሁሉንም ሞዴሎች በአንድ ተመሳሳይ ሥራ ላይ ማሳተፍም ሆነ ማየት እንደማይቻል የሚገልጸው ባለሙያው፤ ይህም ደግሞ የሞዴሊንግ ሙያ ሁሉንም አካታች(inclusive ) መሆኑን ማሳያ ነው ይላል፡፡ የአራት ዓመት እድሜ ካላቸው ሕጻናት ጀምሮ እስከ አዛውንት ድረስ ያሉ ሰዎች የሚሠሩ የሞዴሊንግ ሙያ አይነቶች አሉ የሚለው ሞዴል አብረሃም፤ ነገር ግን ሞዴሎቹ ተሳትፎ እንደዲዛይነሩ ፍላጎትና ምርጫ የሚወሰን እንደሆነ ይናገራል፡፡

ይህ ሲባል ለአዛውንቶች የተሠራ ልብስ በወጣቶች አይተዋወቅም፤ በተመሳሳይ በአዛውንቶች የተሠራ ልብስ በሕጻናት አይተዋወቅም፡፡ ዲዛይነሩም ዲዛይን ያደረገው ምርት ለወጣቶች የሚሆን ከሆነ እንዲያስተዋወቁት የሚፈልገው ወጣቶች ናቸው፡፡ እንዲዚሁ ሁሉ ጎልማሶች ታሳቢ አድርጎ የተሠራ ከሆነ ደግሞ እንዲተዋወቁ የሚፈልገው በጎልማሳ የእድሜ ክልል ያሉ ሞዴሎችን ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው እንደሚተዋወቀው የሥራ አይነት ሞዴሎችም ይለያያሉ የሚለውን ነው፡፡

ሞዴል አብረሃም እንደሚለው፤ የሞዴሊንግ ሙያ በሀገራችን ገና ጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ በዘርፉ የባለሙያ እጥረት አለ፡፡ ስለሙያው አብዛኛው ማህበረሰቡ ጋር ያለው አመለካከትና ግንዛቤም የተሳሳተ ነው፡፡ ይህ አመለካከት እስኪቀየር ድረስ ብዙ ሥራዎችን መሥራት ይፈልጋል፤ ይጠበቃልም፡፡

‹‹አሁን ላይ በሞዴሊንግ ዘርፍ ያለን ባለሙያዎች ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት እያደረገን ነው፤ በተመሳሳይም ሚዲያው ግንዛቤ የሚፈጥሩ ሥራዎችን ቢሠሩ ይህንን አገልግሎት የሚፈልጉ ድርጅቶች ሙያተኛውን ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታን ያስቀምጣሉ፡፡ በዚያው ልክ ሙያው ክብር ያገኛል፤ የሙያተኛው ቁጥርም ይጨምራል››ይላል ፡፡

ወጣቶች ወደ ሞዴሊንግ ሙያ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሆኖ ሳለ ኅብረተሰቡ ዘንድ ባለው አመላካከት የተነሳ ፍላጎታቸው ይገታል፡፡ ይህንን አልፈው የሚገቡትም ጥቂቶች እንደሆኑ የሚያነሳው ሞዴል አብረሃም፤ ወጣቶቹ እንችላለን ብለው ለመማር ቢመጡ እንኳን ወላጆቻቸው ስለሙያው ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ‹ልጄ ትበላሽብኛለች ወይም ይበላሽብኛል፤ ሌላ ነገር ትለምድብኛለች ወይም ይለምድብኛል ብለው ስለሚያስብ ልጆቻቸው ወደ ሙያው እንዲገቡ አይፈልጉም፤ ትምህርቱንም እንዲማሩ አይፈቅዱላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ ለሙያው ማደግ እንቅፋት መሆኑን ያብራራል፡፡

‹‹እንደአፍሮ ፊገር ሜካፕና ሞዴሊንግ ስኩል የሞዴሊንግ ሙያን ስናስተምር ግን ሙያው የራሱ ዲስፒሊን እንደሚፈልግ ሁሉ የግብረገብነት ትምህርት ደግሞ ራሱ ችሎ እንደ አንድ ትምህርት ይሰጣል ›› የሚለው ሞዴል አብረሃም፤ ሙያው እንደ ትምህርትነት ሲሰጥ በሙያ ስለሚያስፈልገው የአለባበስ፣ የአረማመድ፣ የአነጋገር እና የተለያየ ነገሮች ተካተው ነው፡፡ አንድ ሞዴል ሞዴል ለመባል ምን ምን ነገሮችን ማሟላት አለበት፤ እንደ ሞዴል ቁምሳጥን ውስጥ ምን አይነት ልብሶች እንዴት መቀመጥ አለባቸው፤ ምንአይነት ቀለም ከምን አይነት ጋር አብሮ ይሄዳል የሚለውን ፋሽን(ስታይል) የሚማሩበትም ነው፡፡

ወንድ ሆነ ሴት ሞዴሎች ሁሉም የሚመለከታቸው ትምህርት እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ወላጆች ግን ይህንን ሁሉ ስለማይረዱ ልጆቻቸው ሞዴሊንግ ሙያ ሲመርጡ የሚበላሹ ስለሚመስላቸው ልጆቻቸው ወደ ሙያ እንዳይገቡ ጫና ይፈጥሩባቸዋል፡፡ እናም ሙያውን ከማሳወቅ አኳያ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ነው፡፡

‹‹በእኔ እምነት ሞዴሊንግ ከሁሉም ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው›› የሚለው ሞዴል አብረሃም፤ ሙያው ከራስ አልፎ ሀገርን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ትልቅ ሥራ የሚሠራበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንደ ሀገር ሙያው በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች ያሉበት ነውና እነዚህ ባለሙያዎች ተባብረው አንድላይ መሥራት አለባቸው ሲልም ይመክራል፡፡ በሞዴሊንግ ሙያ ብዙ መልካም አጋጣሚዎች በመፍጠር ሀገር በዓለም ላይ እንድትተዋወቅ ከማድረግ ባሻገር ባሕላችንን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የምናደርግበትም ነው ይላል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ድጋፍ እና ትብብር ያስፈልጋል ሲል ምክረ ሀሳቡን ይለግሳል፡፡

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *