“ምርቃትን‘ በምርቃት

ከጥበብ ጀምበር ወዲህ ማዶ በርካታ ጠቢባን ከአንዲት ጣራ ስር ተሰባስበዋል። ገጣሚያን፣ ደራሲያን እንዲሁም ሃያሲያን ሁሉንም አንድ ጉዳይ አገናኝቷቸዋል። የአራት ኪሎዋ አብርሆት አዳራሽ ደግሞ የጥበብ ድግሷን ደግሳ እንግዶቿን ለማስተናገድ ወገቧን ታጥቃ ሽር ጉድ እያለች ነው።

ባሳለፍነው እሁድ ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በእለቱ ሁሉንም ከዚህች አዳራሽ ያገናኘው ጉዳይ የአንድ የግጥም መድብል ምረቃ ነበር። ደራሲው አለምነህ ረጋሳ አመታትን በጥበብ ምህዋር ላይ መጥቆ በምልከታና በምናብ ቅኝት፣ በብዕሮቹ ጠብታ የወለዳቸው የግጥም ሥራዎቹ አድገው በወግ ማዕረግ ሊያስመርቃቸው “ምርቃት” ሲል ለምርቃቱ ተሰናድቷል። 46 ያህል ግጥሞችን በውስጧ ያካተተችውን ይህቺን የግጥም መድብል ደራሲው አለምነህ ረጋሳ “ምርቃትና ሌሎች” ሲል ሰይሟታል። እኛም በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችን ማዕድ ምርቃትን በመመረቅ ከምርቃቷ ገጸ በረከት እናቋድሳችሁ።

በዘመን ጥበባችን ለጉዟችን መነሻ ይህን ብለን ምናባዊ የሆነውን አውቶብሳችንን ሞተር አስነስተን ገጣሚውን ከመሪው ላይ፣ ምርቃትን ደግሞ ከፊተኛው ጋቢና አስቀምጠን እንጓዝ። ከደራሲው የቀድሞ ሥራዎች እንደ ማርሽ፣ ምርቃትን እንደ ነዳጅ እያስገባን የሃሳብ ፍሬናችንን እረገጥ! ማድረጋችን የማይቀር ነው። ለማንኛውም ሞተራችንን አስነስተን መልካም ጉዞ! በማለት አብረን ወደፊት…

በእለቱ ባለ 114 ገጽዋ ምርቃት በ46 ግጥሞች ታጅባ እንዲህ ተመረቀች። የግጥም መድብሏን ሂሳዊ ግምገማ ይዞ ከመድረኩ ላይ የወጣው ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ከግጥሞቹ ይዘት እስከ ሃሳብ ተዋቅሮ ያለውን መልክ ቁልጭ ብሎ በሚታይ መልኩ ለታዳሚውና ለእለቱ የክብር እንግዶች በማስደመጥ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ጀመረ ሳይሆን ቀጠለ እንበል። በእለቱ በመድብሏና በሌሎችም የደራሲው አበርክቶዎች ዙሪያ ሂሶች ቀርበዋል፤ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል… ደራሲውም ምስጋናና አድናቆትን ተችሯል።

ታዲያ ደራሲው አለምነህስ ምን አለ…ከመልዕክቱ መልዕክቷን ቆንጥረን፣ ከንግግሩ እኚህን ዓረፍተ ነገሮች ወሰድን፤ “ከሁሉ አስቀድሜ፤ ላለፉት 38 ዓመታት የደከምኩባቸውን የግጥም ሥራዎች ለሕትመት ብርሃን ላበቃልኝና ለዚህ የምረቃ በዓል ላደረሰኝ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናዬን አቀርባለሁ:… ግጥም የፍቅር መግለጫ፣ ፍትህ መጠየቂያ፣ ብሶት መንገሪያ፣ ደስታን ማብሰሪያ ትንቢት መተንበያ፣ ፈሪን ማጀገኛ፣ ትውልድን ማዳኛ፣ መፍትሄ ማስገኛ ህብረትን ማወጃ፣ ጦር አውርድ ማብረጃ፣ ጦርን መቀስቀሻ፤ ግጥም ለኔ ቢጤው ኢትዮጵያዊውማ ሁሉ ነገሩ ነው፣ የእግዜር መማለጃ ሙሾንም ማውረጃ… በመጨረሻም ወደ ሥነ ጽሑፍ ዓለም ዘልቄ እንድገባ ተሰጥኦዬ መሆኑን እንዳውቅ ለረዳኝ ለታላቁ መምህሬና በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው ለረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ….”

ስለ ደራሲው መቅድም ሥራዎች ጥቂቷን በገረፍታ ለማለት ያህል። ይህቺ መደብል በግጥም ደረጃ ለደራሲው የመጀመሪያ ብትሆንም በመጽሐፍ ደረጃ ግን አራተኛው ናት። ከዚህ ቀደም ሌሎች ሶስት ሥራዎችን ለንባብ አብቅቷል። በልቦለድ ድልድይ ተሻግሮ በታሪክ መንገድ አሳልጦ፣ እነሆ በግጥም ደጅ በሩን ከፍቶ ሰተት ብሎ መጥቷል። መሀን እናት የአጫጭር ልቦለዶች ስብጥርና የበኩር ልጁ ናት። ይቺን መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ ታትማ ለንባብ ለመብቃት 30 አመታትን በእንግልት ስለማሳለፏ ደራሲው አለምነህ ይናገራል። ከእነዚህ ሁሉ የእንግልት ጉዞ በኋላ በ2002 ዓ.ም ለህትመት በቅታለች። መጽሐፏ ለህትመት እንድትበቃ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የጥበብ ጽንስ እንዳይጨናገፍ በማሰብ የጥበብ እጁን ዘርግቷል። የተባ ብዕር ይዘው የማሳተም አቅም ላጡ ደራሲያን ያዘጋጀውን እድል በመጠቀም አለምነህ ይህን የልቦለድ ሥራውን ይዞ ከማኅበሩ ደጅ ደረሰ። ማኅበሩም የበርካታ ደራሲያንን ሥራዎች በመገምገም በመሀን እናት አሸናፊነት ተጠናቆ ለደራሲው የድል ብስራት ሆነ። በተስፋ ስንቅ የለመለመው ውስጡ ዳግም ለሌላ የጥበብ ማዕድ መሰናዳት ጀመረ።

ሌላው የአለምነህ ረጋሳ ጥበባዊ የብዕር ዐሻራ ከአንድ ታላቅ ሰው ላይ አርፏል። የመጀመሪያው የሀገራችን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን “የዘመናዊ ውትድርና አባት ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ” ከሚል የርዕስ አጽናፍ ስር አድማሱን እያሰፋ ባማረ መልኩ አዋቅሮ አስነብቧል። በቅርብ ጊዜ ደግሞ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የዶክተር ሙላቱን የሕይወት ታሪክ እንዲሁም በሥራቸው ዙሪያ የሚያጠነጥን ባለ 440 ገጽ ታሪክ ወለድ መጽሐፍ ለመጻፍ ችሏል። መጽሐፏንም እንዲህ ሲል ሰይሟታል “ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ”

ይህን የግጥም መድብል ደራሲው ለሁለት ታላላቅ የጥበብ አርበኞች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከልብ የቀረበ ስጦታው አድርጎታል። የመጀመሪያው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ታሪክ በተዋበ ህብረ ቀለማዊ ብዕር ከትቦ ለንባብ ላበቃው ለባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በብዕር ስሙ ጎመራው፣ ለአመጸኛው ብዕረኛ ለኃይሉ ገ/ዮሐንስ ክብር መግለጫ ይሆን ዘንድ መታሰቢያ አድርጎ አቅርቦታል። በአብዛኞቹ ግጥሞች ላይ የሰፈሩት የገጣሚው ምልከታ በሀገር፣ ባህልና ተፈጥሮ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ ረቂቅና ግሩም በሆነ እይታ የተቃኙ ናቸው። የሀገር ባለውለታዎቻችንን የመዘንጋት አባዜያችንን ለመፋቅ ገጣሚው በግሉ ያሰበ ይመስላል። በግጥሞቹ ክብር ለሚገባው ክብርን እየሰጠ ዳግም ወደኋላ ተመልሰን እንድናስባቸው በሚያደርግ መልኩ አውስቷቸዋል። ስለ ብዙዎቹም በስንኝ ቋጠሮ የትውስታን ስንቅ ሰንጎ በመጽሐፉ ላይ ታሪክን አኑሯል። ጀግኖቹን እያወደሰ ታሪካቸውን ከዘከረባቸው ግጥሞች መሃከል አንደኛው “ዮፍታሔን ሞተ ያለው ማነው?” እያለ የታላቁን ሰው የጥበብ ህያዊነት ይነግረናል።

“ዮፍታሔ አልገበረም ለጠላቱ

ለመድፍ ለታንክ፣ ለመትረየስ ኮተቱ

በርቱ ቢል እንጂ ለነፃነቱ

ምርኮ ኩነኔ፣ ድል እንጂ ሞቱ።

የኪነጦሩ ፍጆታ

ከደም ቀለሙ ተቀድታ

ለስቃይ ለብካይ ሳትፈታ

ለዘላቂ ሕይወት ፀንታ፣

ዮፍታሔን ሞተ ያለው ማነው?

የጀግና ወኔው ሰንደቅ አርማው

ብዕር ቀለሙ ህያው ነው!!”

ከዚህች የግጥም መድብል ምረቃ በኋላ እኔም የዚህ አምድ አዘጋጅ ወደ ደራሲው አለምነህ ጎራ በማለት ከፊቱ ቁጭ ብዬ ለማውጋት ፈለኩ። እናም ካለበት ድረስ ሄጄ ሁሉንም በጥቂት ጥቂቱ አወጋነው። እንዲያው ለመግቢያ ያህል ዘንድሮ ግጥምና ገጣሚ ለየቅል ሆነዋል ይባላል እንዴት ነው ነገሩ ብዬ ለመጠየቅ ቃላቱን በአፌ ስጉመጠመጣቸው ቀድሞ ሰማኝ መሰለኝ እንዲህ ሲል ጀመረልኝ፣ “አሁን አሁን ሁሉም ገጣሚ ሆነና አንዱን ከአንዱ መለየት አዳጋች ሆነ እኮ..” ሲል አንዳች ቅሬታ ውስጡን እየቆጠቀጠው ንግግሩን ቀጠለልኝ። ከገጣሚ ፊት ቁጭ ስል ገጣሚ የመሆን ፍላጎቴ ተቀሰቀሰ መሰለኝ በአንድ ወቅት በቃላት ጠረባ እያልኩ በግድም ቢሆን በብዕሬ የጣልኳት አንዲት ግጥም ትዝ አለችኝ።

ግጥም ቤት ሲመታ፣

በቃላት እሩምታ፣

ሲመታ ሲመታ፣

ቤቱም ፈረሰና

ወደቀ አንድ ማታ።

የግጥም ቤት ጎጆ

ቤቷ ከፈረሰ፣

ገጣሚና ግጥም

አብሮ ከታመሰ፣

የግጥሟ ባለቤት

ጥበብ አለቀሰ፣

ብዕር ተቃወሰ።

ከሁሉም ከሁሉም በተለይ ደግሞ በአሁነኛው አንዳንድ የሙዚቃ ግጥሞቻችን ላይ ጥበብ የምታነባው እምባ አይወሳ፣ ይደር ይዋል…እሱን እድል ጊዜ ትስጠንና እናወጋው ይሆናል። አሁን ግን ጉዞዋችን በምርቃት አውቶብስ ላይ ነውና ወደዚያው እንመለስ።

ግጥም ቤት እየመታ እውነትና ስሜትን ካፈረሰ ፋይዳው ከምኑ ላይ ነው…የአንባቢውን ሕይወት ተርኮ ልቡን ካልኮረኮረው ግጥምን ግጥም የሚያሰኘው ከምኑ ላይ ነው?…ግጥም ከማህበረሰቡ የኑሮ ባህር እየተጨለፈ ሲቀዳ ጥምን ያረካል፤ አንጀትንም ያርሳል። ይህን መድብል ያሰናዳው ደራሲው አለምነህም ይህን እውነታ ተረድቶ መሆን አለበት ከእውነተኛ የሕይወት ባህር እየጨለፈ በግጥሞቹ ሀገራዊና ማህበረሰባዊ እኛነታችንን አይቶ ለማሳየት የተጋው። ግጥም በስሜት የታጨቀ የቃላት ድርደራ ብቻ አለመሆኑንም ያሳየን ይመስለኛል።

ብዕር ይናገራል እንዲሉ በዚህ መድብል ውስጥ በተካተቱት ግጥሞች በሀገር ፍቅር በተለወሰ ስሜት የተኛውን እየቀሰቀሰ፣ የነቃውን እያሞገሰ በጥያቄና ተግሳጽ እያጀበ የመልካም ትውልድ ምሰሶን ለማቆም ታትሮባቸዋል። የተማረው በትምህርቱ፣ ነጋዴውም በትርፉ ይህን ምሰሶ በደቦ እናቁማት በሚመስል ጥሪ መልዕክቱን በግጥሞቹ ሰዷቸዋል። “አንተ ትውልድ ተናገር” እያለ በብዕሩ እንዲህ ይናገራል፤

“ችግር ስታስተጋባ ለዘመናት ስትወተውት

አምጣ መፍትሄ ፍታት

የሚያላቅቅ ከታሰርንበት ትብትባት…

አምጣ ዘዴ ስልት ቀመር

የስልጣኔ የእድገት መስመር”

……..

እያለ ይቀጥላል።

የገጣሚው ግጥሞች፣ ገጣሚው ስለ ሀገሩ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የመዳሰስ ፍላጎቱን በግልጽ ይነግሩናል። ከምርቃት ውስጥ የተካተተችውንና ስለ ዓባይ “ዓባይ ብርሃን ሆነ” ሲል ያሰፈራትን ግጥም እንመርቅላችሁ።

«ብርሃንሽ ወጥቷልና የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺና አብሪ…//»

ዓባይ ብርሃን ሆነ

ዓባይ የምድረ ሀበሻ ትሩፋት

የጥቁር አፍሪካዊው ወዝ ውርዛት

በፍጥረት ዓለም የሚጠነጠን

ሩቅ ተጓዥ ከሰከላ እስከ አስዋን

የሚብሰከሰክ በበረሃ አሸዋ በሲናይ

ተፍለቅልቆ ዘላቂ የምድረ በዳ ሲሳይ

ዱር አዳሪ በባእድ ሀገር በዋልድባ

የዘመናት ብሶት የዘመናት እንባ፡፡

ፈርዖን……

ዓባይ ለኛ ብቻ ነዲድ ይሁን ይብራ

ጠብታም አንፈቅድም ጨለማቸው ይድራ

ዝንተ ዓለም ሰቆቃ መከራ ይዝፈቁ

እኛ እንኑርበት እነሱ ይማቅቁ.. ብለው ተሳለቁ/2

ብለው አሟረቱ ፈርዖን በብርቱ

አከተመ….

ግና ሁሉን አግበስብሶ ሀገርን መክዳቱ

በየተጓዘበት በየደረሰበት ወረተኛነቱ

አድርባይም ሆኖ ሀገሩን መርሳቱ

ዓባይ ልብ ገዛ አበቃ አከተመ ወገነ ለእናቱ፡፡

ስለ ምርቃትና ሌሎች የግጥም መድብል በጥቂቱ ይሄችን ካልን ታዲያ ደራሲው ማነው ማለታችሁ አይቀርምና ከትንሹ መስታወት ፊት አቁመን ጥቂቱን እንቋደስ። ደራሲ አለምነህ ረጋሳ 1978 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተመርቋል። በተለያዩ ጊዜያትም በጋዜጠኝነትና የሕዝብ ግንኙነት ከ15 በላይ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመውሰድ ያለውን ክህሎት ለማዳበር ችሏል። ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ የባህል ሚኒስቴር ውስጥ የሥነ ጽሁፍ አደራጅና የሥነ ጥበባት ቡድን መሪ በመሆን አገልግሏል። እንዲሁም የአማራ ክልል የማስታወቂያ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ፣ የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ አገልግሎት ኃላፊና የቴሌቪዥን ቡድን መሪ፣ የኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት የፕሬስ ሕዝብ ግንኙነትና የቃለ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ኃላፊ፣ የኢፌዴሪ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙዩኒኬሽን ተ/ዳይሬክተር በመሆን ሀገርና ሕዝቡን አግልግሏል።

በምርቃትና ሌሎች ግጥሞች መድብል አውቶብስ ተሳፍረን፣ እንዲሁም ከሌሎችም የደራሲው ሥራዎች ጋር ተጉዘን ከፌርማታው ላይ ደርሰናልና እዚህ ጋር እንቆም ዘንድ የግድ ይለናል፡፡

 ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *