የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፤ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ከፓን አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር በጋራ በመሆን “የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ” ከሰሞኑ አንድ የምክክር መድረክ በስካይ ላይት ሆቴል አካሂደው ነበር። የምክክር መድረኩ በርካታ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን ያገናኘ ሲሆን መፍትሔ የሚሹ ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮችም ተነስተውበታል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት በቱሪዝም ሚኒስቴር የመዳረሻ እና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ነበሩ እርሳቸው እንደሚሉት “መድረኩ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ የዘርፉን ተዋንያን በአንድ ማዕከል አገናኝቶ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተን ወደፊት በጋራ አቅደን ሥራዎችን መሥራት የሚያስችል ይሆናል። በአሁኑ ሰዓት የቱሪዝም ዘርፍ ላለፉት ዓመታት ሲፈትኑት የነበሩት የኮቪድ ወረርሽኝ ከሞላ ጎደል ዓለም አቀፍ ጫናዎች ቀንሰዋል” በማለት ተናግረዋል። በተለይ ዘርፉ ቀደም ሲል ገጥሞት ከነበረው መፋዘዝ እየወጣ እንደሆነ በንግግራቸው አፅንዖት ሰጥተው ለማብራራት ሞክረዋል።
“በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት ቆሞ ሀገራችን በአሁን ወቅት የተሻለ ሰላም ላይ ትገኛለች” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እነዚህን መሰል አጋጣሚዎች መፈጠራቸው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ስላሉ ቁልፍ ጉዳዮች አንስቶ ምክክር ለማድረግ ሁነኛ ግዜ መሆኑን አመላክተዋል። በተለይ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቱሪዝም ዘርፍ በሆቴል፣ በቱር ኦፕሬሽን፣ በሬስቶራንት እና በሌሎች የቱሪዝም ዘርፎች ተሠማርተው የሚገኙ አካላትን አስተባብሮ በመንግሥት በኩል ከሚመለከተው ተቋም የቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር መወያየቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ “የግሉ ዘርፍ ምልከታዎች የኢትዮጵያ ቱሪዝም” በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሲዬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አንድነት ፈለቀ የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ፣ መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ኃሳቦች ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። የዝግጅት ክፍላችንም የቀረበው ጽሑፍ የዳሰሳቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው አቅርቧል።
ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች
በውይይት መድረኩ ላይ ወይዘሮ አንድነት በቅድሚያ ካነሷቸው አንኳር ነጥቦች መካከል እንደ አጠቃላይ በቱሪዝሙ ዘርፍ እንዲሁም በተለይ በአስጎብኝዎች ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የተለያዩ ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ነው። በጥናቱ የተሰበሰቡ መረጃዎች የሚያሳዩትም ይህንኑ መሆኑን አመላክተዋል። በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ያስከተለው ጫና፣ ከቀረጥ ነጻ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የግብር ሕግና የኦዲት አሠራር፣ ዘርፉን እንደ ወጪ ንግድ ዘርፍ ተመልከቶ ትኩረት መስጠት፣ ከመሠረተ ልማት አውታሮች ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች ከደረጃ በታች መሆን እንዲሁም በብሔራዊ እና በክልል ደረጃ በሚከናወኑ የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች መካከል ያለው መናበብ አነስተኛ መሆን ዋንኛ የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን ገለፃ አድርገዋል። እነዚህን ጉዳዮች በዝርዝር ለመረዳት እንዲያስችለን የተወሰኑትን ለማየት እንሞክር።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ
የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሲዬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አንድነት የጥናታዊ ጽሑፉን ግኝት መነሻ አድርገው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ዘርፉን ለመደገፍ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ከቱሪዝሙ ዘርፍ የአገልግሎት ዘርፎች አንዱ የሆነው የሆቴሎችና መስተንግዶ ዘርፍ በአነስተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኝ መደረጉን ያነሳሉ፤ አያይዘውም ከዚህ የብድር ድጋፍ መካከል ለአስጎብኝው ንዑስ ዘርፍ የደረሰው 11 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆነ ይገልፃሉ። ለዚህም እንደ መከራከሪያ የቀረበው “የሆቴል ዘርፍ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ እንደመሆኑ ጫናው ከፍ ያለ ነው” በሚል ነው የሚሉት ፕሬዚዳንቷ። የአስጎብኝዎች ዘርፍ ግን ይህ ጫና የለበትም የሚል አመለካከት እንደነበር አንስተዋል። ሆቴሎች የሚያስተናግዷቸውን እንግዶች በዋናነት የሚያገኙት ከአስጎብኝዎች መሆኑን በወቅቱ ለመገንዘብ ፍላጎት እንዳልነበር ያነሳሉ።
“እንግዶችን ለሚያመጣው ዘርፍ አነስተኛ ትኩረት በመስጠት የሚደረግ ድጋፍና እገዛ ውጤታማ ላይሆን ይችላል” የሚሉት ወይዘሮ አንድነት፤ በመሆኑም ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ለሁሉም የዘርፉ ባለድርሻዎች በፍትሐዊና በሚዛናዊነት መከፋፈል ይኖርበታል የሚል ምክረ ሀሳብ አንስተዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን፤ የ11 በመቶ የገንዘብ ብድር አቅርቦቱም ቢሆን ከአፈጻጸም ጋር በተያያዙ ቢሮክራሲያዊ አሠራሮች ምከንያት እስካሁንም ድረስ ተግባራዊ ቀዳሚው የዘርፉ ተግዳሮት እንደሆነ ገልፀዋል።
እንደ ወጪ ንግድ ዘርፍ እውቅና መስጠት
“የቱሪዝሙ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ዋነኛ ዘርፎች አንዱ ነው” የሚሉት ወይዘሮ አንድነት፤ ዘርፉ ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ የ2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን ይጠቅሳሉ። ያም ሆኖ ግን፤ ሁሉም የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች እንዲሁም የአሠራር መመሪያዎች ዘርፉ የሚያበረክተውን አስተዋፅዖ አሳንሰው የሚያዩና ተገቢውን ትኩረት የማይሰጡ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህን ችግር የመፍታት ጥረት የሚጀምረው፣ ዘርፉ አገልግሎትን ለወጪ ንግድ የሚያቀርብ እንደሆነ አምኖ በመቀበልና እውቅና መስጠት መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገርም ዘርፉ የግብር እፎይታ የተለያዩ የጉዞና አስጎብኝ መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን ጨምሮ ለወጪ ንግድ ዘርፎች ከተሰጡ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባም ነው የሚጠቁሙት።
የመሠረተ ልማትና የጥበቃ ችግሮች
ወይዘሮ አንድነት በጥናታቸው ካስቀመጧቸው ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚታየው የመሠረተ ልማት ችግር እጅግ የከፋ መሆኑን ነው። የቱሪስት ስፍራዎች፣ ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች የሚወስዱ መንገዶች፣ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎች ጉዳዮች እንደ አጠቃላይ በቂ ትኩረት አልተሰጣቸውም የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ እንደሚቻል የሚያነሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እና ባሌ ብሔራዊ ፓርክ በዙሪያቸው የሚገኙ ነዋሪዎች በሚያደርጉባቸው ጣልቃ ገብነት ሳቢያ የሚገኙበት የከፋ ሁኔታ ቱሪስቶችን የሚያሸሽ ድርጊት መኖሩን በዚህ ምክንያት ፓርኮቹን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመቀነስ ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2005 ላይ 5300 የነበረው የጎብኝዎች ቁጥር በ2007 ወደ 20500 ቢያድግም ከ2010 አንስቶ የጎብኝዎች ቁጥር ቅናሽ ማሳየት የጀመረ ሲሆን በ2017 ላይ 7600 መድረሱን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ።
የቱሪዝም መረጃ ክፍተት
ወይዘሮ አንድነት በጥናታቸው ላይ ያስቀመጡት ሌላው ጉዳይ የቱሪዝም መረጃ ክፍተት ነው። በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው የቱሪስቶች ቁጥር የተመዘገበው እአእ በ2017 መሆኑን ጠቁመው፣ በዓመቱ 933 ሺህ ያህል ቱሪስቶች አገሪቱን እንደጎበኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ይናገራሉ። ይህንን መረጃ ግን በተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች በመጠቀም ምላሻቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ግን የዚህን መረጃ ትክከለኛነት እንደማያምኑበት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አስገብኝዎች ማኅበር ባሠራው ጥናት ላይ የተሳተፉት፣ ወደ ሀገሪቱ የመጡት ለንግድ ወይም ለሌላ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የቱሪስት ቪዛ ይዘው የሚገቡ ወይም አዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሲደርሱ የቱሪስት ቪዛ የሚጠይቁ ሰዎችን ማየት የተመለደ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህን መሰሉ የቱሪስት መረጃ አሰባሰብ ትክከለኛውን የቱሪዝም ገጽታ ለመገንዘብም ሆነ ለዘርፉ ውጤታማ ዕቅድ ለማውጣት ከፍተት እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰው የዘርፉ አንደኛው ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።
የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ቅንጅት
“ኢትዮጵያ የምትከተለው የፌዴራላዊ ሥርዓት ዓላማ ሕዝቦች ራሳቸውን የማስተዳደር ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነበር” የሚሉት ወይዘሮ አንድነት፤ ይህም በአገሪቱ ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ ባሕልን ለማስፋፋት እንደ አንድ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ይናገራሉ። ያም ሆኖ ግን፤ ከብሔራዊ ዕቅድና ራዕዩ ጋር የማይጣጣሙ አካባቢያዊ አሠራሮች በመስፋፋታቸው ሳቢያ ቱሪዝምን በመሳሰሉ መስኮች በየክልሎች የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎች ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኝ ያስረዳሉ። በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚታዩት የቱሪስት አገልግሎት ክፍያዎች፣ የቱሪስት አስጎብኝነት አገልግሎት መመሪያዎችና ሌሎች ከዘርፉ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች አስጎብኝዎች የራሳቸውን ዕቅድ እንዳያወጡና የቱሪስቱን ፍላጎት በሚገባ እንዳያሟሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን ያነሳሉ::
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የሚመለከታቸው አካላት በግብር ሥርዓቱ ላይ የፖሊሲና ሌሎች ተገቢ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ምክረ ሀሳባቸውን ይሰጣሉ። ለአስጎብኝዎች ተመሳሳይ የግብር ስሌት ሥርዓትን በሥራ ላይ ማዋልና ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች የሚሰበሰቡ ደረሰኞች ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።
እንደ ምክረ ሀሳብ
የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሲዬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አንድነት ፈለቀ ከላይ ከተነሱት የቱሪዝም ዘርፉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ባሻገር ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ሀሳቦች ይናገራሉ። በቀዳሚነትም የሕግና ፖሊሲ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት እንደሚሹ ተናግረው መንግሥትም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
“የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቱሪዝሙ ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያለውን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በሰጠው የብልጽግና ዕቅድ መሠረት በ2009 የወጣውን የቱሪዝም ፖሊሲ ገምግሞ አሻሽሏል” የሚሉት ወይዘሮ አንድነት፤ መንግሥት የፖሊሲ ግቦችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለማሳካት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን መቀየሱን እንደ መልካም አጋጣሚ ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ በክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ሃብቶችን በማስተዳደር ረገድ በመንግስት የሚከናወኑ ስራዎችን ከቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ጋር የሚያጣጥም አጠቃላይ አካሄድ መቀየስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም “የሀገሪቱ የቱሪስት ስፍራዎች ኢንቨስትመንትና ባለቤትነት የሚመራበት ሕግ ማውጣት” እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የቱሪስት ስፍራዎች ልማት እንቅስቃሴዎች የሚመሩበት ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማውጣት ተገቢ መሆኑንም አመላክተዋል። የቱሪዝሙን ዘርፍ እንቅስቃሴ በመደበኛነት መከታተል የሚያስችል ሕግ በሚመለከት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አስወጥቶ በሥራ ላይ ሌላኛው መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል ።በዘርፉ እውቀትና ልምድ ያላቸውን ሰዎችን ያካተቱ የቱሪዝም ቦርድ፣ የቱሪዝም ካውንስልን የመሳሰሉ ተቋማትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በመጨረሻም የፓርኮች ጥበቃ እና ልማት (በቴከኖሎጂ የታገዘ አሠራር የሚከተል የፓርኮች ጥበቃ ቦርድ በኬንያ እንዳለ በምሳሌነት አንስተው) መሰል ተቋማትም በኢትዮጵያ መፍጠር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም