የ2015 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት መሰጠቱ ይታወሳል። ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት 77 ሺህ 981 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን የተፈተኑ ሲሆን፤ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደግሞ 72 ሺህ 203 ተፈትነዋል። በድምሩ ከመንግሥትና ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለፈተናው ከተቀመጡት ውስጥ 40 ነጥብ 65 በመቶ የሚሆኑት 61 ሺህ 54 ተማሪዎች የማለፊያውን 50 እና ከዚያ በላይ ነጥብ አስመዝግበዋል።
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናውን ከወሰዱ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች 62 ነጥብ 37 በመቶ የሆኑት ማለትም 48 ሺህ 632 ተማሪዎች አልፈዋል። በአንጻሩ ደግሞ ለፈተና ከተቀመጡት 17 ነጥብ 2 በመቶ የሆኑት ማለትም 12 ሺህ 422 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማለፊያውን 50 እና ከዚያ በላይ ነጥብ ማስመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ መሰረት በተለይ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች ውስጥ ከ82 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመውጫ ፈተናውን አላለፉም ማለት ነው። ከዚህ አኳያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ዝቅተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ የቻሉበት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው? የተማሪዎቹን ውጤት ለማሻሻል ቀጣይ የቤት ሥራዎች ምን መሆን አለባቸው? በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግሯል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የጥራትና ብቃት ማሻሻያ ዴስክ ኃላፊ እንዲሁም ተመራማሪና የፖሊሲ አማካሪ እጩ ዶክተር ሰይድ ሙሃመድ እንደሚሉት፤ ለፈተና ከተቀመጡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች 17 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ የማለፊያውን 50 እና ከዚያ በላይ ነጥብ አስመዝግበዋል። በጥቅል ድምሩ ሲታይ ውጤቱ ዝቅተኛ ነው። ይሁን እንጂ በተቋም ደረጃ ሲታይ የግል ተቋማት ሆነው በመውጫው ፈተናው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡና በጣም ተወዳዳሪ ተቋማት አሉ።
በአንጻሩ የመንግሥት ሆነው የማለፍ ምጣኔያቸው በጣም አነስተኛ የሆኑ ተቋማቶች አሉ። እንዲሁም በግልም፣ በመንግሥት ተቋማትም መቶ በመቶ ተማሪዎች ያለፉባቸው የትምህርት መስኮች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው የማለፍ ምጣኔያቸው ዜሮ የሆነ የትምህርት ፕሮግራሞች መኖራቸው ተስተውሏል። ስለዚህ እንደ መንግሥትም ሆነ በተለይ እንደ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ውጤቱ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያቱን ማወቅ የሚቻለው ውጤቱ ሲተነትን ነው። ሚኒስቴሩ የውጤት ትንተና እየሠራ ነው። በቀጣይ በትንተናው መሰረት የተገኙ ግኝቶች ይፋ ይደርጋሉ።
ሆኖም በመውጫ ፈተናው በተመዘገበው ውጤት ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት የሚስተዋሉ ችግሮች አሉ። በመሆኑም ለተመዘገበው ውጤት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እራሱን የቻለ ጠባሳ ያሳርፋሉ። የመጀመሪያው ችግር የተማሪ ቅበላ ሥርዓት ነው። ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፣ ተቀራራቢ ብቃትና ደረጃ ያላቸው ተማሪዎች ወደ መንግሥት ተቋማት ይገባሉ። ወደ መንግሥት ተቋማት መግባት ያልቻሉና ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነው የሚገቡት። ይህ የሚያሳየው ከመንግሥት ይልቅ የግል ተቋማት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ሌላኛው ትምህርት የሚሰጥበት መርሃ ግብሮች (መደበኛ፣ የርቀት፣ የማታ፣ ኤክስቴንሽን … ወዘተ) የተማሪዎችን ውጤታማነት ይወስናሉ። በየትኛው የትምህርት መርሃ ግብር የተማሩ ተማሪዎች ናቸው የመውጫ ፈተናውን ዝቅተኛ ውጤት ያመጡት? የሚለው በውጤት ትንተናው የሚታይ ይሆናል። ነገር ግን በርቀት ትምህርት መርሃ ግብር ተማሪዎችን ተቀብለው በስፋት እያስተማሩ ያሉት የግል ተቋማት ናቸው። ይህም ለተማሪዎች ውጤት መውረድ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሆኖም የርቀት መርሃ ግብር ለተማሪዎች ውጤት ዝቅ ማለት ምክንያት ነው? ወይም አይደለም? የሚለው የሚታወቀው ከውጤት ትንተናው በኋላ ነው። በጥቅሉ በመንግሥትም የሆነ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመዘገበው ውጤት የሚያሳየው ባለድርሻ አካላት መሥራት ያለብንን የቤት ሥራ እየሠራን እንዳልሆነ ነው። በመሆኑም ገበያው የሚፈልገውን ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን አላፈራንም ሲሉ እጩ ዶክተር ሰይድ ያብራራሉ።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁም የትምህርት አመራርና አስተዳደር ባለሙያ ዶ/ር አማኑኤል ኤሮሞ በበኩላቸው፤ የግል ከፍተኛ ተቋማት እንደ መንግሥት ተቋማት ተማሪዎች የሚያድሩበትና የሚኖሩበት መኝታ ቤት የላቸውም። ስለዚህ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት በመመላለስ ነው። ይህም ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።
ሌላው የግል ተቋማት ከግብዓት አኳያ ብቁ መምህራን፣ ሥርዓተ ትምህርት፣ ተማሪዎች፣ እንዲሁም መሰረተ ልማት አሟልተው ነወይ ወደ መማር ማስተማሩ የገቡት? ከተባለ ሰፊ ክፍት አለባቸው። ስለዚህ መማር ማስተማሩ ላይ ብቁ መምህር፣ ተማሪዎችን የሚያበቃ ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎች አንድ ክፍል ውስጥ ሳይገናኙ ውጤት መጠበቅ ሞኝነት ነው። በተለይ የግል ተቋማት ተማሪዎች በመውጫ ፈተናው ያስመዘገቡት ውጤት ግብዓት ከማሟላት ሂደቱ ጋር የሚቆራኝ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ዓለምን እየመሩ ያሉት እንደነ ሀርቫርድ፣ ኦክስፎርድ፣ … ወዘተ የመሳሰሉ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። እነዚህ ከፍተኛ ተቋማት በምርምር ያገኟቸውን ውጤቶችንና የፈጠራ ሥራ እየሸጡ ሁለንተናዊ አቅማቸውን አጎልብተዋል። ተልዕኳቸውም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ማብቃት እና የዓለምን ችግር የሚፈቱ ተአምራዊ የፈጠራ ሥራ የሚሠሩ ተመራማሪዎችና ተማሪዎችን ማፍራት ነው። ሆኖም ወደኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ በመጠነኛ ትርፍ ሀገርና ሕዝብን ለማገልገል የሚሠሩ ተቋማት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። የአብዛኞቹ የግል ተቋማት ተልዕኳ ተማሪዎችን በገፍ መዝግበው ከፍተኛ ትርፍ ማግበስበስ ነው። የተማሪ ቁጥር ሲበዛ መምህሩ ሁሉንም ተማሪዎች ማብቃትና መከታተል አይችልም። ለተማሪ ውጤታማነት ደግሞ መምህር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።
እንዲሁም ብዙዎቹ የግል ተቋማት ራዕያቸው ለሁሉም ዜጋ የዲግሪና ዲፕሎማ ሰርተፍኬት ማዳረስ ነው። ነገር ግን የትምህርት ደረጃውን የሚመጥን ዕውቀት ለዜጎች ያስጨብጣሉ ወይ? መሟላት የሚገባውን ግብአት ያሟላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ ወረቀት እንደመርጨት ወይም እንደማደል ይቆጠራል። በተጨማሪም “ከ ‘ሲ’ በታች ውጤት አትስጡ” ብለው መምህራንን የሚያስገድዱ የግል ተቋማት አሉ። ተማሪዎች ከደረጃ በታች እያስመዘገቡ ለሁሉም “ኤ” እና “ቢ” የሚሰጥበት አግባብ አለ። ስለዚህ ተማሪዎቻቸውን ተከታታይ በሚሰጡት ምዘና ለይተው፤ ክፍተት ያላባቸውን አላበቁም። ይህም በመውጫ ፈተና ተማሪዎቹ ያስመዘገቡት ውጤት አመላካች ነው ይላሉ።
እንደ ዶ/ር አማኑኤል እምነት የግል ተቋማት የመውጫ ፈተናውን ውጤት ተንተርሰው የሁነት ትንተና በመሥራት ድክመትና ጥንካሬያቸውን ለይተው እንደገና አቅደው ወደ ሥራ ከገቡ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ሆኖም የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ባለሀብቱና አመራሩ ቁርጠኛ መሆን አለበት። ቀደም ሲል የነበረውን የሥራ ባህላቸውን በመቀየር ተማሪዎችን ውጤታማ በሚያደርግ የሥራ ባህል በመቀየር ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ ይገባቸዋል። እንዲሁም ትርፍን ማግበስበስ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው ግባቸው ብቁ፣ ተወዳዳሪና መልካም ሥነ-ምግባር ያለው ዜጋ ለማፍራት መጣር አለባቸው።
ከግብዓት አኳያም ተማሪዎችን የሚያበቃ ሥርዓተ ትምህርት መቅረጽ ይኖርባቸዋል። በሙያው ብቃት ያላቸውና የሰለጠነ መምህራኖች ሊኖራቸው ይገባል። በክፍል ውስጥ የሚያስተምሩትን ተማሪዎች ቁጥር ውስን ማድረግ አለባቸው። ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በትምህርት ላይ እንዲያሳልፉ በተቋሙ እያደሩና እየኖሩ ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት ሥርዓት መጀመር አለባቸው። በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት ሥርዓተ ትምህርታቸውን የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም በሚጨምርና ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ መከለስ ይኖርባቸዋል። ለተቋሙ እድገትና ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ማህበረሰቡ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ተሳታፊ ማድረግ አለባቸው።
በሌላ በኩል አሁን ላይ መንግሥት እየተከተለ ያለው የትምህርት ጥራት አመራርና አስተዳደር በደፈናው ጥራትን ማረጋገጥ (Quality assurance) የሚባል ነው። ይሄ ዘዴ በቼክ ሊስት የሚሠራ ነው። መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አይለካም። መንግሥት ይህንን ኋላቀር የትምህርት ጥራት አመራርና አስተዳደር ዘዴን በመለወጥ አሁን ላይ ዓለም እየተጠቀመበት ያለውንና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ውጤታማ የሆነውን ሁለንተናዊ አቀፍ የትምህርት ጥራት አመራርና አስተዳደር (Total Quality education managment) ስልትን መከተል አለበት። በዚህ ስልት መሰረት መንግሥት የመንግሥትና የግል ተቋማትን ክፍተታቸውን እየለየ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ማብቃት እንዳለበት መምህሩ ያሳስባሉ።
በሌላ በኩል ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሱን የቤት ሥራ ወስዶ ተግቶ ሊሠራ እንደሚገባ እጩ ዶክተር ሰይድ ገልጸው፤ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ከቁጥጥር ሥራው ጎን ለጎን የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞችን ቀርቦ በማየት ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲሞሉ አብሮ መሥራትና መደገፍ ይጠበቅበታል። በአንጻሩ ተቋማቱ ደግሞ ተማሪዎቻቸው ብቁና ገበያው ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን የአሠራር ሥርዓት መከተል አለባቸው። የመማር ማስተማር ዘዴያቸውን ሊፈትሹ ይገባል።
እንዲሁም አንድ የትምህርት ፕሮግራም ላይ አንድ እና ሁለት ምዕራፍ ብቻ ትኩረት ተደርጎ ተማሪዎች የማጠቃለያ ፈተና የሚወስዱበት አግባብ አለ። ይህ የምዘና ሥርዓት የተማሪዎችን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በጥቅሉ ሁለንተናዊ ብቃት አይለካም። ስለዚህ የተማሪዎችን ሁለንተናዊ ብቃት በሚለካ መልኩ የምዘና ሥርዓታቸውን መቀየር አለባቸው። በተጨማሪም ተቋማቱ የተማሪዎቻቸውን ውጤት ለማሻሻል ትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተናውን ከመስጠቱ በፊት አስቀድመው የመውጫ ፈተናውን የሚመስል ሞዴል የሙከራ ፈተና አዘጋጅተው ለተማሪዎቻቸው መስጠት አለባቸው። ይህም ተማሪዎቻቸው ያሉበትን ደረጃ በመፈተሽ ያልበቁትን ያለባቸውን ክፍተት ለይቶ ለማብቃት ያስችላቸዋል።
ተማሪዎቻቸውን ለመውጫ ፈተና ብቁ አድርገው የማሳለፍ ብቃታቸው የተሻሉ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት በተማሪ እንዲሁም በማህበረሰብ የተሻለ ተመራጭነትና እውቅና ይኖራቸዋል። በተቃራኒው የማሳለፍ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተቋማት ደንበኞቻቸውን በሂደት እያጡ ይሄዱና ህልውናቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። በተመሳሳይ የትምህርት ክፍሎች የመውጫ ፈተና የማሳለፍ ምጣኔያቸው ዜሮ ከሆነ ተማሪዎች ትምህርት ክፍሉን መርጠውት ለመማር ዝግጁ ላይሆኑ ይችላሉ። ትምህርት ክፍሎች ጠንክረው የማለፍ ምጣኔያቸውን ከግዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ ካልጣሩ በስተቀር ተመራጭነታቸው እየቀነሰ ስለሚሄድ በሂደት እስከ መዘጋት ይደርሳሉ። ይህ ደግሞ የዘርፉ ምሁራንና ሠራተኞችን በሂደት አደጋ ላይ የሚጥልና የሥራ እድል የሚያሳጣ እንደሆነ እጩ ዶክተር ሰይድ ይናገራሉ።
በአጠቃላይ እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች እምነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ችግሩን አንዱ ወደ አንዱ ሳይገፋ ችግሩ የኔ ነው ብሎ ወስዶ በግልም ይሁን በመንግሥት ተቋማት የመውጫ ፈተናውን ተፈትነው ያላለፉ ተማሪዎችን አብቅቶ ፈተናውን ማለፍ የሚችሉበትን አቅም መፍጠር አለበት። ይህ ከሆነ ተማሪዎቹ ነገ ላይ ከራሳቸው አልፈው ሀገርና ወገናቸውን ይጠቅማሉ። ተማሪዎች እንዲበቁ ማድረግ ከተቻለ ፈተናውን የማያልፉበት ምንም ምክንያት የለም። በመውጫ ፈተናው ለወደቁ ተማሪዎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸው ምሁራኑ ያስረዳሉ።
በአንጻሩ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ማለፍ ካልቻሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው በትንሹ ከሶስት ዓመት በላይ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን አባክነው ምንም የትምህርት ማስረጃ ሰርተፍኬት አይኖራቸውም። ይህ ደግሞ የተማሪዎችን እና የወላጆችን የዓመታት ድካም ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ከመሆኑ ባለፈ እንደሀገር ትልቅ ኪሳራና ጉዳት የሚያደርሰው። በሂደትም ብሔራዊ ቀውስ የሚፈጥር ነው።
ስለዚህም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያሉባቸውን ችግሮች ነቅሰው በቀጣይ ተዋዳዳሪና በመውጫ ፈተናም በቂ ውጤት ማምጣት የሚችሉ ተማሪዎችን ማፍራት ከወዲሁ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ተግባር መሆኑን ሁለቱም ምሁራን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015