የአሜሪካ በሽታ ቁጥጥር ማዕከል ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የሚሞቱ አሜሪካዊ እናቶች ቁጥር የመጨመሩ ምክንያት ጥቁር መሆናቸው እንደሆነ ጥናት ማመልከቱን ገለጸ።
ጥናቱ እንዳመለከተው የጥቁር አሜሪካውያን፣ የአላስካ አሜሪካውያንና የነባር አሜሪካውያን እናቶች ሞት ቁጥር ከነጭ አሜሪካውያን በሦስት እጥፍ ይበልጣል። በየዓመቱ 700 ያህል ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱም ጥናቱ ይፋ አድርጓል። 60 በመቶ የሚሆነውን የሞት ምክንያትም ቀድሞ መከላከል ይቻላል ሲልም ጥናቱ ጠቅሷል።
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ዳይሬክተር አን ሹቻት በርካታ ሴቶች ቀድሞ መከላከል በሚቻል ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የጤና ዕክል እንደሚሞቱ ገልጸዋል። እነዚህን ችግሮች ለመለየትና ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጥቁር እናቶችን ሞት በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መግለጫ አውጥቶ የነበረው የአሜሪካ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ኮሌጅ በጤና ጥበቃው ሥርዓትና በጤና ተቋማት የዘር መድሎ እንደሚፈፀም ገልጿል። “ለእናቶች ሞት ምክንያት ዋናው ዘረኝነት ነው” ሲልም በመግለጫው አስፍሯል። አያይዞም ለችግሩ በጤና ተቋማትና በጤና ጥበቃ ሥርዓቱ ያለው ጥግ የደረሰ ዘረኝነት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል።
በጥናቱ ከአውሮፓውያኑ 2011-2017 ድረስ ያለውን የእናቶች ሞት የተመለከተ ሲሆን፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከእርግዝና ጋር በተያያዘ 3400 ሞት መመዝገቡን አስታውቋል። በነጭ ሴቶች ከሚወለዱ 100 ሺዎቹ 13 እናቶች ሲሞቱ፤ ይህ በጥቁር እናቶች ሲታይ ደግሞ ቁጥሩ በሦስት እጥፍ አድጎ ከ100 ሺዎቹ 42 እናቶች ሕይወታቸው ያልፋል።
በነባር አሜሪካውያን እና በአላስካ ሴቶች ሲታይ ቁጥሩ 32ነጥብ5 ሲሆን፤ የእሲያ እና የፓስፊክ ሴቶች 14ነጥብ2 ሆኖ ተመዝግቧል። በጣም ዝቅተኛ ቁጥር የሚያሳየው የሂስፓኒክ ሴቶች ሲሆን፤ ከ100 ሺዎቹ የሚሞቱት 11 እናቶች ብቻ ናቸው። ዋነኛው በእርግዝና ወቅት ለሞት ከሚዳርጉ ምክንያቶች የተጠቀሰው ከልብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲሆኑ፤ የልብ ህመምና ስትሮክ ሞቱን በሦስት እጥፍ ይጨምሩታል።
በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት በአሜሪካ የእናቶች ሞት ቁጥር መጨመሩ ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃፀር ያልተጠበቀ ቢሆንም ከአውሮፓውያኑ 1990 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በዓለም ላይ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የነበረው የእናቶች ሞት በ44 በመቶ እንደቀነሰ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በየትናየት ፈሩ