የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ አማዞን ነፍሰ ጡር ሠራተኞቹን ከሥራ እያሰናበተ ነው የሚል ክስ ቀረበበት። ቢቢሲ በድረገጹ እንዳስነበበው፣ አማዞን ቢቨርሊ ሮዜልስ የተባለች አሜሪካዊት ሠራተኛውን ነፍሰ ጡር ነሽ በሚል ምክንያት ከሥራ በማሰናበቱ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበታል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት ተመሳሳይ ክስ ሲያቀርቡ የነበሩ ሴቶች እንደገለፁት፣ በኩ ባንያው ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ድርጅቱ ፍላጎታቸውን ሊያሟላላቸው ፈቃደኛ አልነበረም።
ከነዚህ መካከል ቢቢሲ ያናገራት ስሟ እንዳይገለፅ የጠየቀች አንድ እናት በኩባንያው ቆይታዋ ነፍሰ ጡር በነበረችበት ወቅት የምትሰራው ሥራ ለነፍሰጡር እናቶች በሀኪም የሚመከር ባለመሆኑ ወደ ሌላ ክፍል እንድትዘዋወር ጥያቄ ብታቀርብም ሳይፈቀድላት እንደቀረ ገልጻለች። ይህች እናት ሥራዋ ክብደት ያለው ጋሪ መግፋት፤ ከባድ ዕቃ ማንሳትና ጎንበስ ቀና ማለት የሚበዛው በመሆኑ ጤናዋ ላይ ችግር ገጥሟት እንደነበር ተናግራለች።
በእንግሊዝ የሚገኘው ጂኤምቢ የሠራተኞች ማኅበር ቃል አቀባይ “በአማዞን የሚሠሩ ነፍሰ ጡር እናቶች የሚነግሩን ለ10 ሰዓታት ያህል ቆመው እንደሚሰሩ ነው። እንደ አማዞን ያሉ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በአግባቡ መያዝ ይጠበቅ ባቸዋል፤ እንደ ሮቦት ሊያሠሯቸው አይገባም” ብለዋል።
አማዞን በበኩሉ “ሠራተኞቹ በማርገዛቸው ብቻ ተባረሩ የሚለው ክስ ፍፁም ከእውነታ የራቀ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። አክሎም ሁሉንም ሠራተኞች በእኩል ዓይን ነው የማየው። ለሠራተኞቼ የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና እገዛ አደርጋለሁ፣ ይህም ነፍሰ ጡር ለሆኑ እናቶችም ጭምር ነው። በተጨማሪም ልጅ ለወለዱ እናቶችና አባቶች የወሊድ ፈቃድ እየሰጠው ነው ብሏል።
በተጨማሪም ኩባንያው ማንነታቸውን በግልፅ ስላልተናገሩ ሠራተኞቹ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠብ ገልጾ፤ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ካሳወቁ ከሠራተኞቹ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ተናግሯል። ነገርግን ኩባንያው ባለፉት ዓመታት ስለቀረቡበት ቅሬታዎችና ከሕግ ውጪ ስለተነሱ ጉዳዮች አስተያየቱን ከመስጠት ተቆጥቧል።
የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ አማዞን ከ613 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በገና በዓል ሰሞን ብቻ እስከ 100 ሺህ ጊዜያዊ ሠራተኞችን ይቀጥራል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ተመሳሳይ ክሶች የቀረበበት አማዞን ቢቨርሊ ሮዜል ያቀረበችበት ክስ በካሊፎርኒያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰኔ ወር መታየት ይጀምራል፡፡
አዲስ ዘመን ግብቦት 2/2011
በሶሎሞን በየነ