አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአገሪቱ እየጨመረ የመጣውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ እንዲቻል ተመጣጣኝ ድጋፍ ለመስጠት የዕቅድ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን ገለጸ፡፡
ማኅበሩ ትናንትና በዓለም ለ73ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ61ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለውን ዓለም አቀፉን የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን “ሰብዓዊነት ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ሲያከብር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጸሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በአገሪቱ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሰብዓዊ ቀውሱንና የዘላቂ ልማት ፍላጎትን ሊመጥን የሚችል ድጋፍ ለማድረግ ማህበሩ በስልታዊ ዕቅዱ ላይ ማሻሻያ እያደረገ የሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸሃፊው በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ድጋፍ የሚፈልጉ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም ማህበሩ የሚጠበቅበትን ሰብዓዊ አገልግሎት በተሻለ መጠን፣ ጥራትና ቅልጥፍና መስጠት እንዲችል የሚያግዙ ሁለንተናዊ የለውጥ ዕቅዶች አዘጋጅቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ጸሃፊው ገለፃ ማህበሩ በህዝብ የተመሰረተና አንጋፋ በመሆኑ ከውጭ ጥገኝነት ተላቅቆ ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ገቢ የሚተዳደር እንዲሆን አስፈላጊው የገቢ ማሰባበሰቢያ ስልትና አደረጃጀትን አጠናቅቆ ወደ ተግባር ለማሸጋገር እየተጠባበቀ ሲሆን፤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በማህበሩ የበላይ ጠባቂ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ አስጀማሪነት ወደ ሥራ ይገባል፡፡
የማህበሩ የበላይ ጠባቂና የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በበዓሉ አከባበር ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ “ ሰብዓዊነት፣ ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉና በከፍተኛ ደረጃ እርስ በእርስ የተሳሰሩ በመሆናቸው ተቀናጅተው ሊከናወኑ ይገባል” ብለዋል፡፡ “ሰብዓዊነት ብቻውን ግብ አይደለም” ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ከዚህ አኳያ ማህበሩ በሚያከናውነው የሰብዓዊነት እርዳታ ውስጥ ሰላምን አካትቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ እንደሚያስመሰግነው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ማህበሩ በአሰራሩና በአደረጃጀቱ ላይ ማሻሻያ ማድረጉ አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህንን የተጀመረውን የለውጥና የማሻሻያ ጉዞ የበለጠ አጠናክራችሁ ሰላምን ከልማት አቀናጅታችሁ መፈናቀሎችንና ሰብዓዊ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት የሚቀንስ ውጤታማ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ ስታከናውኑ መንግስት ከጎናችሁ ሆኖ ይደግፋችኋል ብለዋል፡፡
በኢጣሊያን ጦርነት ዋዜማ ለጦር ቁስለኞች ሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ ከ1927 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ ላለፉት ስምንት አስርት ዓመታት ሰብዓዊ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው አንጋፋው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአሁኑ ሰዓት ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላትና ከአርባ ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች አሉት፡፡ ማህበሩ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ የአባላቱን ብዛት ከእጥፍ በላይ ለማሳደግና የበጎ ፈቃደኞቹን ቁጥርም ቢያንስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንዲሆኑ ለማድረግና በአፍሪካ በአባለቱ ብዛትም ሆነ በበጎ ፋቃደኞች ቁጥር ግንባር ቀደም ብሔራዊ ማህበር ለመሆን የሚያስችል የንቅናቄ ዕቅዱንም በበላይ ጠባቂው በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አማካኝነት በትናትናው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በይበል ካሳ