አዲስ አበባ፡- 3ኛው የኢትዮጵያ ግብርና፣ ምግብና መጠጥ ማቀነባበር እና ተያያዥ የፕላስቲክ ህትመት ፓኬጂንግ አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፈተ::
የአገር በቀሉ የፕራና ኩነት አዘጋጅ ዋናሥራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ ለማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ አገሪቷ ከግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለምታደርገው ሽግግር የግብርና ምርቶች እሴት በሚጨምር መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን በማድረግ ሂደትም እንደዚህ አይነት የንግድ ትርኢቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ፣ መጠጥና ፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ፤ የንግድ ትርኢቱ መዘጋጀቱ ኢትዮጵያ ያላትን የግብርና እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑን በመጠቆም፤ እስከ አሁን በጥሬው የሚላኩትን የግብርና ምርቶች እሴት በመጨመር ወደ ውጪ አገር መላክ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በአገሪቱ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ (የአግሮ ፕሮሰሲንግ) በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣በደቡብና በአማራ ክልሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የግብርና ምርቶች እሴት በሚጨምር መንገድ እንዲቀነባበሩ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሂደትም የቴክኖሎጂ ሽግግር እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ የንግድ ትስስር ለመፍጥር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የፕራና ኩነት ከጀርመኑ አቻው ‹‹ፌር ትሬድ›› ጋር በቅንጅት የ18 አገራት 148 አለም አቀፍ ንግድና ቴክኖሎጂ መሪዎች እንዲሁም ሥራ ፈጣሪዎች የተሳተፉበት የ3 ቀን ንግድ ትርኢት ማዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በሙሐመድ ሁሴን