ደቡባዊ አፍሪካዊቷ ሃገር ናሚቢያ በሃገሪቱ የተከሰተው ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሦስት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተጣለ ሲሆን ሁሉም የመንግሥት የሥራ ክፍሎች ናሚቢያውያንንና ከብቶቻቸውን ለመጠበቅ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃጌ ጄይንጎብ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፤ “በቂ ዝናብ ሳናገኝ የዝናቡ ወቅት አልፏል። ይህም ማለት ተፈጥሯዊ የድርቅ አደጋ ገጥሞናል ማለት ነው። ስለሆነም ድርቁ የብዙዎችን ህይወት አደጋ ላይ የመጣል ዕድል ስላለው የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁላችንም በተጠንቀቅ መንቀሳቀስ ይኖርብናል” ብለዋል። በሃገሪቱ የተከሰተው ድርቅ አምስት መቶ ሺ ናሚቢያውያንን ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡ ማድረጉን መንግሥት አስታውቋል። ይህም ከአምስት ናሚቢያውያን አንዱ በቂ ምግብ አያገኝም እንደማለት ነው። ድርቁ ከተከሰተ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ስድሳ ሺ የቤት እንስሳት ሞተዋል።
ስለሆነም መንግሥት በድርቁ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ዜጎች ምግብና ውሃ ለመግዛትና እንስሳቱን ግጦሽ ወደሚገኝበት ቦታ ለማጓጓዝ አርባ ሚሊዮን ዶላር መድቧል። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳራ ኩጎንግልዋ- አማዲላ በበኩላቸው ዕርዳታ እንዲያደርግላቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አድርገዋል። “በድርቁ የተጎዱ ወገኖቻችንና ከብቶችን ለመታደግ ሁሉም ናሚቢያውያንና የዕርዳታ ድርጅቶች በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉና ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” በማለት በሃገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ተገኝተው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሃገሪቱ የተከሰተውን የተራዘመ ድርቅ ያስከተለውን ቀውስ ለመፍታት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በድርቁ የተጎዱ ዜጎች ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው መሆኑን አስታውቋል። ፕሬዚዳንት ጀጎብ በበኩላቸው ከጥር እስከ መጋቢት ያሉትን ወራት ተከትሎ የሚመጣው ዝናባማ ወቅት የሚገኘው ዝናብ አነስተኛ መሆን ለችግሩ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን በምሬት ተናግረዋል። በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍሎች ወንዞች መድረቃቸውንና የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብና ውሃ ለማግኘት የመንግሥትን እጅ ለመጠባበቅ መገደዳቸውን ጋዜጠኛ ቲዩሞ ሃይዱላ ለቢቢሲ ተናግራለች። ከብቶች ለከፋ ጉዳት መጋለጣቸውንም ጋዜጠኛዋ ገልጻለች።
የሃገሪቱ የኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትር ስታንሊ ሲማታ በበኩላቸው ሁኔታዎች እስኪቀየሩ ድረስ አርሶ አደሮች ምግብና ውሃ ማቅረብ በሚችሉት መጠን የከብቶቻቸውን ቁጥር እንዲቀንሱ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሃገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ኤን.ቢ.ሲ ዘግቧል። በማዕድን የበለጸገችው በቆዳ ስፋት ትልቋ ደቡብ አፍሪካዊት አገር ናሚቢያ በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል እየተስፋፋ በመጣው ደረቃማ የአየር ንብረት የተነሳ ለእርሻ ምቹ ባለመሆኑ 70 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍጆታዋን የምታስገባው ከጎረቤት ደቡብ አፍሪካ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።
በአንጻሩ ናሚቢያ ለከብት እርባታ ምቹ በመሆኗ ከዋነኞቹ ሥጋ ላኪ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ሆኖም ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት አገሪቱ በተከታታይ በድርቅ እየተመታች በመሆኗ በእንስሳት ሀብቷ ላይም አደጋ ተደቅኗል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በይበል ካሳ