ባለፈው ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታዋቂው እንግሊዛዊ አስትሮ ፊዚስትና ሳይንቲስት ዓለም የምትጠፋው በኑክሊየር አለያም በአየር ንብረት ለውጥ ሊሆን እንደሚችል በተደጋጋሚ ተናግሯል።
ምናልባትም የሰው ልጅ ካለፈው ታሪኩ በመማር አንዱ በአንዱ ላይ ኒዩክሊየር ላይተኩስ ይችላል። የአየር ንብረት ለውጥ ግን ቀስ በቀስ የሚከሰትና ውጤቱ ወዲያው የሚታይ ባለመሆኑ አደጋው የከፋ መሆኑን ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። ስቴቨን ሃውኪንግ እአአ በ2017 ፕሬዚዳንት ትራንፕ የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት ውድቅ ባደረጉበት ወቅትም ፕሬዚዳንቱን በመቃወም ውሳኔው በዓለም ህዝብ ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ አስመልክቶ ሙያዊ አስተያየት ሰጥቶ ነበር። “ውሳኔው በዓለም ላይ የተፈጠረውን የአየር ንብረት ቀውስ የሚያባብስና የሙቀት መጠኑም የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያደርግ ነው።
እናም በሚቀጥሉት ሺ ዓመታት ውስጥ ልክ እንደ ቬኑስ ምድራችን የሙቀት መጠኗ 250 ዲግሪ የሆነባትና አሲድ የሚዘንብባት ሰው የማይኖርባት ፕላኔት ልትሆን ትችላለች” ማለቱ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ከሰሞኑ ሌላ አስገራሚ ዜና ተሰምቷል። የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ሥነ ምህዳር ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎች ሥርዓተ ተዋልዶ ላይም ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን የሚያሳይ አዲስ ጥናት ይፋ ሆኗል። ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድኖች የተሳተፉበትና “ኢንቫይሮሜንታል ሪሰርች ሌተርስ” ላይ የወጣው አዲስ ጥናት “የአየር ንብረት ለውጥ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በመውለድ አቅምና በአጠቃላይ የሰዎች ሥርዓተ ተዋልዶ ሂደት ላይም ወሳኝ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን ባደረግነው ጥናት ደርሰንበታል” ብሏል።
ይህም የሆነበት ምክንያት ሰዎች የሚወልዷቸውን ልጆች ብዛትና አስተዳደግ የሚወስኑት ባላቸው ጊዜና ገንዘብ መጠን ላይ ተመስርተው በመሆኑ ነው። “ያለንን የጊዜና የገንዘብ ሃብት ተጨማሪ ልጆችን እንውለድ ወይንስ የተወለዱትን እናሳድግበት? የሚለው መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄ የጥንዶችን የመውለድ አቅም ይወስናል። ጥናቱ የሥራ ዘርፍ ለውጥ፣ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የሥራ ክፍያ ልዩነት፣ እርጅናና ሞትን ጨምሮ በመውለድ አቅም ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተገናኙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት የአየር ንብረት ለውጥ ኢኮኖሚው ላይ የሚያመጣውን ውጤት ገምግሟል።
የኮሎምቢያንና የስዊዘርላንድን ኢኮኖሚም በናሙናነት ተጠቅሟል። በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ በህዝብ ስብጥር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ያህል ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆኑንና በሃብታምና በድሃ አገራት መካከል ያለውን ልዩነትም ምን እንደሚመስል ለማሳየት ሞክሯል። ከዚህም በአሻገር የጥናት ቡድኑ ህጻናትን በአንድ ወገን አዋቂዎችን በሌላ ወገን አድርጎ የወላጆች ልጆችን የመውለድና የማሳደግ አቅም የሚወሰነው ባላቸው ውስን የቤተሰብ ገቢና በጀት መሆኑን አሳይቷል። ጥናቱን በበላይነት የመሩት በማሳቹትስ አሜሪካ የዊሊያምስ ኮሌጁ ዋና ተመራማሪ ዶክተር ግሪጎሪ ኬሴይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን በግብርናው ላይና ከግብርናው ውጭ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የተለያየ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ተመራማሪው አባባል በርካታ ድሃ አገራት የሚገኙበት የምድር ወገብ አካባቢ የአየር ንበረት ለውጡ በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። “ይህም የግብርና ውጤቶች እጥረት እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል፤ በዚህ የተነሳም የግብርና ምርቶች ዋጋ ይወደዳል፤ ለሰራተኛ ጉልበት የሚከፈለው ክፍያና ደመወዝ ይጨምራል፤ በመጨረሻም ግብርናው ቦታውን ለሌሎች ሥራዎች ለመልቀቅ ይገደዳል። ምክንያቱም ግብርናው ያን ያህል የሰለጠነ የሰው ኃይል አይፈልግም።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በግብርናው ላይ እየተፈጠረ ያለው ተፅዕኖ ደግሞ ዘርፉ የበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዳይፈልግ የሚያደርግ በመሆኑ ከስልጠና የሚገኘው ክህሎት ዋጋ እንዳይኖረው አድርጎታል። ስለሆነም በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸው ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክና ገንዘባቸውን በትምህርት ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ ተጨማሪ ልጆችን ለመውለድ እንዲወስኑ መንስኤ ሆኗል” ይላሉ ተመራማሪው። ይሁን እንጂ ከምድር ወገብ ርቀው በሚገኙ መካከለኛና ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ክልል ውስጥ በሚኖሩ አገራት ሁኔታው ተቃራኒ መሆኑን አጥኚዎቹ በሰሩት ጥናት አረጋግጠዋል።
የጥናቱ ተባባሪ አዘጋጅ በሚላን ጣሊያን የቦቾኒ ዩኒቨርሲቲው ዶክተር ሶሂል ሻይግ “የአየር ንብረት ለውጥ ከሃሩራማ የአየር ክልል አገራት በተቃራኒው በሰሜናዊ ዞን በሚገኙ ሃብታም አገራት የሚወለዱ ልጆች መጠን እንዲቀንስና ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ኢ-ፍትሀዊነቱን እያባባሰው መሆኑን የጥናታችን ውጤት ያሳያል” በማለት ግርምታቸውን ይገልጻሉ። “ከተፈጥሮ ሃብቱም በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ምክንያት ከሚመጣው የአየር ንብረት ለውጥም ያለተቀናቃኝ በብቸኝነት ተጠቃሚ የሆኑት ሃብታሞቹ አገራት መሆናቸው የሚገርምም የሚያሳዝንም ነው” ብለዋል ተመራማሪው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በይበል ካሳ