ሦስቱም የልጆቻቸው ትምህርት ቤት ጉዳይ አሳስቧቸዋል፡፡ ተሰማ መንግስቴ፤ ዘውዴ መታፈሪያን በትኩረት እያየው ነው፡፡ ዘውዴ ደግሞ እጁን ጉንጩ ላይ አድርጎ ፈዞ ገብረየስ ገብረማርያምን ይመለከታል። ሦስቱም ከምን ጊዜውም በላይ የከፋቸው ይመስላሉ። የልጆቻቸው የትምህርት ቤት የመመዝገቢያ እና የመማሪያ ቁሳቁሱ ወጪ ያንገዳግደናል ብለው ሰግተዋል፡፡
ያዘዙትን ቢራ ከመጠጣት ይልቅ እየቆዘሙ ነው። ተሰማ እና ገብረየስ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት አንድ ዓለም አቀፍ በሚባል ትምህርት ቤት ነው። ዘውዴ ግን እንደአቅሙ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ልጆቹን ያስተምር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ክፍያው ስላማረረው ለቀጣይ ዓመት ልጆቹን የመንግሥት ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ ቆርጧል፡፡
እነገብረየስም በበኩላቸው ትምህርት ቤት ቀይረው ቀነስ ያለ ክፍያ ወደሚከፈልበት ትምህርት ቤት ለማስገባት አቅደዋል፡፡ ዘውዱ ፊቱን አኮሳትሮ ግንባሩን ቋጥሮ፤ ‹‹ይኸው የልጆቼ ትምህርት የማያባራ ጭንቀት ውስጥ ከቶኛል፡፡ ልጆቼ በዓለም የሠራተኛ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ለሀገራቸው ዶላር ያስገኛሉ ብዬ እንደእናት ጡት ሁለት ብቻ ወልጄ እነርሱኑ በብቃት ለማስተማር ቆርጬ ነበር፡፡ ሁለት ብቻ ቢሆኑም አሁንም ህልሜ እውን የሚሆን አልመሰለኝም፡፡ በዓለም የሠራተኛ ገበያ ቀርቶ በአፍሪካ እንዲያውም በሀገር ደረጃ መወዳደር የሚችሉበትን ትምህርት የማስተምራቸው አልመስልህ ብሎኛል፡፡›› አለ።
ተሰማ የዘውዴ ንግግር የተከፋ ፊቱን ቀየረለት። ወዲያው ከት ብሎ ሳቀ ‹‹ምን ማለትህ ነው? የአንተ ልጆች ትምህርታቸውን ጨርሰው ሲመረቁ ዶላር የዓለም መገበያያ ገንዘብ መሆኑ ያበቃለታል፡፡ ›› ሲለው ገብረየስ በበኩሉ በሁለቱ ምልልስ ራሱን መቆጣጠር እስከሚያቅተው እንባው እየፈሰሰ በሳቅ ተንከተከተ። ያ የመከፋት ድባብ በሳቅ ተቀየረ። ገብረየስ ፊቱን ወደ ተሰማ አዙሮ ‹‹የፈለግከው እና ያሰብከው ሁሉ ወዲያው የሚሆን ይመስልሃል። እርሱ ዶላር ይበል እንጂ ዓለም የሚገበያይበትን ገንዘብ ኢትዮጵያ በልጆቼ በኩል እንድታገኝ እፈልግ ነበር ማለቱ ነው። ዶላር የዓለም መገበያያ ገንዘብ መሆኑ ሊያበቃም፤ ላያበቃም ይችላል፡፡ እንዲህ አንተ እንደምታስበው ቀላል አይመስለኝም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የትምህርት እና የትውልድ ጉዳይ ነው። ዘውዴም ተስፋ ለመቁረጥ ቅርብ ነህ፡፡ ሁለታችሁም ትቸኩላላችሁ፡፡ ትንሽ ልምድ ሳያስፈልጋችሁ አይቀርም። ገና ለገና መክፈል አቃተህና ልጆችህ ተወዳዳሪ መሆን ያቅታቸዋል ማለት ነው?›› በማለት ጥያቄ ሰነዘረ፡፡
ዘውዱ በበኩሉ፤ ‹‹ነገሩ ያልተነካ ግልግል ያውቃል እንደሚባለው ነው፡፡ አምና ‹በአጠቃላይ መደበኛ ተፈታኞችን ካስፈተኑ 2ሺህ 959 ትምህርት ቤቶች መካከል 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት የተመዘገበባቸው ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 798 ብቻ ናቸው፡፡ አስቡት እስኪ የማስተማርና እውቀት የማስጨበጥ ችግር ያለባቸው 1ሺህ 161 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም፡፡› ተብሏል።
ጥናት ቢካሔድ አብዛኛዎቹ እነዚህ አገር ዓቀፍ ፈተናውን በተመለከተ አንድም ልጅ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው፤ ተማሪዎቹም በቅጡ መጽሐፍ የማይደርሳቸው፤ በመምህራኖቻቸው ተገቢው ትምህርት የማይሠጣቸው መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩት የድሃ ልጆች ስለመሆናቸው መቼም መከራከር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡
ገንዘብ ከሌለህ ልጆችህ ጥራት ያለው ትምህርት ተምረው የብሔራዊ መመዘኛም ሆነ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያቀርቡትን የመመዘኛ ፈተና ማለፍ ያዳግታቸዋል፡፡ ይህ ሲታይ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ልጆችን ማስተማር ማለት የተማሪዎቹን ዕድሜ ከማባከን ውጪ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ልጆቼን በእነዚህ ትምህርት ቤቶች አስተማርኩ ማለት አበቃላቸው ማለት ነው፡፡›› አለ፡፡
ገብረየስ፤ ‹‹ተረጋጋ አንደኛ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በነበሩበት አይቀጥሉም፡፡ አሁን ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው በኅብረት ልንቀይራቸው እየተነሳን ነው፡፡ በቀጣይ መሻሻላቸው አይቀርም፡፡ ሁለተኛ አንተ ልጆችህን በደንብ ካገዝክ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ እንዲያውም ተቀጣሪ ከመሆን ይልቅ ሥራ ፈጣሪ ቢሆኑ ይሻላቸዋል፡፡ ይህ እንዲሁም ከማንም በላይ ያንተ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ለተማሪ ውጤታማነት ትምህርት ቤት ወሳኝ ቢሆንም የወላጅ እገዛ ካልታከለበት ዋጋ የለውም፡፡ በተጨማሪ ተማሪ እና መጽሐፍ መነጣጠል የለባቸውም፡፡ በዋናነት ትኩረትህ መጽሐፍ እያቀረብክ በራስህ አቅም ልጆችህን ማብቃት ይሁን፡፡
በየትኛውም ትምህርት ቤት ብቃት ያለው መምህር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን በየትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ ሁኔታዎች የሉም። በየትምህርት ቤቱ ቀልደው ሲያልፉ ቆይተው በመጨረሻ ብሔራዊ ፈተና ላይ ቢወድቁ አያስገርሙም፡፡ ስለዚህ መሥራት ከታች ቀድሞ ነው፡፡ ለዚህ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚያስተምሩበት እና ከክፍል ወደ ክፍል የሚያሸጋግሩበት ሁኔታ በደንብ መጤን አለበት። በተጨማሪ ልጆችን ቤት ውስጥ መርዳት እና መከታተል ትምህርት ቤቱ ላይም ክፍተት ካለ ማሳወቅ መቅደም አለበት፡፡›› ሲል ዲስኩሩን አጠናቀቀ፡፡
ዘውዴ ግን የገብረየስ ንግግር አልተዋጠለትም። ‹‹ጡጫ እና ምክር ለሰጪው ቀላል ነው እንደሚባለው አንተም ምክሩን አዥጎደጎድከው። ነገር ግን እንደምትለው ቀላል አይደለም፡፡ ጥራት ያለው ተመጣጣኝ ትምህርት የማይሰጥበት ሁኔታ እያለ፤ ከትምህርት ቤቶች በላይ ወላጆች ሚናቸውን ቢወጡ ስኬታማ መሆን ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡
በቅድሚያ ሁሉም ተመጣጣኝ የትምህርት ዕድል ማግኘት አለበት፡፡ ያለበለዚያ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 3 ነጥብ 3 በመቶ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን ትረሳለህ ብዬ አላስብም። ይህ ማለት ፈተናውን ከወሰዱት ከ896ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ ማለፍ የቻሉት 29 ሺህ 909 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታ ችግር ያለበት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ይዘው የሚመጡት እውቀት አናሳ ከሆነ እና የትምህርት ቤቶቹ አቅምና ሌሎች ችግሮች መፍትሔ ካልተበጀላቸው የእኔም ልጆች እንደ አብዛኞቹ ልጆች ውጤታማ የማይሆኑበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡›› በማለት ዘውዴ ሃሳቡን ቋጨ፡፡
ተሰማ ግን ሃሳቡን አልጨረሰም ነበር፡፡ በገብረየስ ሃሳብ ላይ ተመርኩዞ እርሱም የተሰማውን ማስተጋባቱን ቀጠለ፤ ‹‹በእርግጥ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል የአንድ ወላጅ ትጋት ብቻ በቂ አይደለም፤ ዋናው ጉዳይ ትምህርት እና ትውልድ የአጠቃላይ የሕዝብ ትኩረትን ይሻሉ፡፡ በእርግጥ ሕዝብ ትምህርት ቤት ይገነባል ሲባል መሬቱን ይሠጣል፤ አንዳንድ ባለሀብት ደግሞ ለትምህርት ቤት ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ምንም ቢሆን በኅብረት ሆኖ መረባረብ ኃይል ይጨምራል፤ ስለዚህ ለየብቻችን ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈልን ከማስተማር፤ የትምህርት ቤት ክፍያ ሲጨምር ከመቆዘም ይልቅ በየዓቅማችን በዕውቀታችን፣ በገንዘባችን እና በጉልበታችን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት እንዲያድግ ብንሠራ ይሻላል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ብቃት ያላቸውን መምህራን ከማፍራት ጀምሮ፤ የትምህርት ሥርዓትን እና አጠቃላይ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ላይ በጥናት የተደገፈ ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር እንድትወጣ ለትምህርት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አያጠራጥርም፡፡ በድህነት ምክንያት ሰዎች ቁርስ ማብላት ስለማይችሉ ለመማር የሚቸገሩበት ሁኔታን ለማስተካከል ምገባ ላይ መሠራቱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በእርግጥም ዩኒቨርሲቲዎችን በየክልሎች እና በዞኖች ሳይቀር መገንባታቸው ይበል የሚሰኝ ነው፡፡
ነገር ግን ዩኒቨርሲቲ ከመገንባት በፊት ከታች ጀምሮ ተመጣጣኝ የትምህርት ዕድል እንዲኖር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ የሕፃናት መዋያዎች መገንባት አለባቸው እየተባለ ነው። ይህ ሙሉ ለሙሉ መደገፍ ያለበት ሐሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም «አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ» እንደሚባለው ከሥር መሥራት ካልተቻለ ከላይ ከላይ መሮጥ ውጤታማ አያደርግም፡፡
የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር እና እርሻን ማሳደግ ያልቻልነው የትምህርት ጥራታችን ችግር ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ ገበሬ ሃምሳ ዳቦ ከመላስ አንድ ዳቦ መግመጥ ይሻላል ይላል፡፡ እውነት ነው፤ አርሶ አደሩ እና የሕዝቡ አንጀት ላይ ጠብ የሚል ጉርሻ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በትምህርት ላይ የጋራ ርብርብ የግድ ነው፡፡
መረባረብ የግድ አንድ ትምህርት ቤት መገንባት ላይ አይደለም፡፡ አንዱ ትምህርት ቤት ሲገነባ ሌላው ቁሳቁስ ማሟላትን ጨምሮ ሌሎች ለትምህርት ዘርፉ ድጋፍ የሚሆኑ ሥራዎችን መሥራት አለበት፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ለማሟላት ጥረት ማድረግ ለአንዳንዶች ብዙ ከባድ ላይሆን ይችላል፡፡ ኮምፒዩተር እና መጽሐፍ ያስፈልጋል፡ አንድ ትምህርት ቤት ሲገነባ ሁሉም በቻለው መጠን ድጋፍ ካደረገ ብዙ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
«ወድቆ ቢነሱ በእጅ ቆይተው ይከብሩ በልጅ» ይባላል። እጅ ከተቆረጠ ወድቆ መነሳት አይቻልም። ልጅን በቅጡ ካላሳደጉ መከበሪያ ሳይሆን ማፈሪያ ይሆናል፤ ማትረፊያ ሳይሆን መክሰሪያ ይሆናል። ትምህርትን ማስፋት ካልተቻለ በልጆች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁነት ከጎደለ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በርብርብ ካልተሠራ ሀገር ባለችበት ትረግጣለች፡፡ ከእርዳታ መላቀቅ ህልም እንደሆነ ይቀራል፡፡ ረሃቡ፣ ችግሩ እና ጦርነቱ ይቀጥላል፡፡›› ብሎ ተሰማ ረዥም ንግግሩን አቆመ፡፡
ዘውዴ በበኩሉ ፈገግ አለ፤ ቢራውን ከተጎነጨ በኋላ፤ ‹‹ንግግራችን ምርጥ ነው፡፡ የምንናገረውን ብንተገብረው የት በደረስን፡፡›› ዘውዴ ተሰማን እያየ፤ ‹‹ለሮጠ አይደለም ለቀደመ ነው እያሉ በተናጠል አቋራጭ መንገድ እየፈለጉ ለመቅደም መዋከብ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ልጅን ምንም ያህል ከፍለው ቢያስተምሩት ሀገር ካላደገች የእርሱ ሕይወት የተስተካከለ ቢሆንም፤ ደስታው ሙሉ አይሆንም። የፈለገውን ያህል ሠርቶ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ቢያገኝም የሀገር ፍቅር አይኖረውም፡፡ ምክንያቱም ድሃን ማንም አይወድም፡፡ እንዲያውም ያ ውድ ገንዘብ ተከፍሎለት የተማረው ልጅ በሀገሩ ያፍራል። ባልተገባ መልኩ አንዳንዴም ራስ ወዳድ እየሆነ በማደጉ መልሶ ለሀገሩ ለመክፈል አይጓጓም፡፡
ለእዚህ መፍትሔው ሀገር ድሃ እንዳትሆን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ነው፡፡ ስንል እጅግ የተጋነነ ገንዘብ እየከፈልን ከምናስተምር ለሁሉም ጥሩ የትምህርት መሠረት እንዲኖር ከሀገር ደረጃ አንፃር አስበን ብንሠራ ይሻላል፡፡ የሚወለዱት ልጆች ከሕፃናት መዋያ ጀምረው ጥሩ መሠረት ካላገኙ ሀገር የመለወጥ ሁኔታዋ ይስተጓጎላል፡፡
በቀጣይም ትውልዱ ከመቀጠር አስተሳሰብ ወጥቶ ጥረት በማድረግ ሥራ ፈጥሮ ቀጣሪ ከመሆን ይልቅ ለመቀጠርም ብቁ መሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈላችሁ ያላችሁት እናንተው ጓደኞቼ ተባብረን አሁን እስኪ ከምንጠጣበት ላይ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንን ከምናስተምርበት ገንዘብ ላይ ቀንሰን በየትምህርት ቤቱ መጽሐፍ የሚዳረስበትን፣ ቴክኖሎጂ የሚስፋፋበትን ሌሎችም ለመማር ምቹ የሆኑ ድጋፎችን እናድርግ።›› ብሎ ዘውዴ ከኪሱ ብር አውጥቶ ለመክፈል ተነሳ እንደለመደው ተሰማ የዛሬን እኔ ልክፈል ሲለው ዘውዴ መልከት አድርጎ ‹‹ከዚህ በኋላ መገባበዛችን ለትውልዱ ትምህርት ቤት በመገንባት ላይ አይሻልም? ›› ሲለው ሦስቱም በመስማማት አንገታቸውን ነቀነቁ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2015