ከታኅሣሥ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ምያንማር ውስጥ ታስረው የነበሩት የሮይተርስ (Reuters) ጋዜጠኞች ከእስር መለቀቃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የ32 ዓመቱ ዋ ሎን እና የ29 ዓመቱ ካው ሶ ኡ በታኅሣሥ ወር 2010 ዓ.ም የታሰሩት የምያንማር መንግሥት የፀጥታ አካላት በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የፈፀሙትን ግድያ በመዘገባቸው ነው፡፡ የምያንማር ፍርድ ቤትም በጋዜጠኞቹ ላይ የሰባት ዓመታት የእስር ቅጣት አስተላልፎባቸው ነበር፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ዲፕሎማቶችም በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ምያንማር ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የምታደርገውን ሽግግር ያቀጭጨዋል በማለት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ዋ ሎን ከሥራ ባልደረባው ካው ሶ ኡ ጋር ከእስር ከተለቀቁ በኋላ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ሙያየን እቀጥልበታለሁ፡፡ ወደ ሥራዬ እስከምመለስ ቸኩያለሁ” በማለት ተናግሯል። የምያንማር መንግሥት ስድስት ሺህ 520 እስረኞችን በምህረት እንደሚፈታ ከአገሪቱ ፕሬዚዳት ጽሕፈት ቤት የወጣ መረጃ ያሳያል፡፡
ፕሬዚዳንት ዊን ማዪንት ባለፈው ወር በሺዎች ለሚቆጠሩ እስረኞች ምህረት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የምያንማር ባለስልጣናት በአገራቸው የዘመን መለወጫ በዓል ወቅት እስረኞችን በይቅርታ የመፍታት የቆየ ልማድ አላቸው፡፡ የሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዋና አዘጋጅ ስቴፈን አድለር “የምያንማር መንግሥት ሁለቱን ጀግና ጋዜጠኞቻችንን ከእስር ስለለቀቃቸው ደስ ብሎናል፡፡ ጋዜጠኞቻችን ከታሰሩበት ቀን ጀምሮ የፕሬስ ነፃነት በመላው ዓለም አስፈላጊ ስለመሆኑ ምልክት ሆነው ቆይተዋል፡፡ መመለሳቸውን በደስታ ተቀብለነዋል” ብለዋል፡፡
ሮይተርስ ጋዜጠኞቹ ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልሠሩና ከእስራትም ሊለቀቁ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለአብነት ያህል፤ የዜና አገልግሎቱ ዋና አዘጋጅ ስቴፈን አድለር ባለፈው ታኅሣሥ ወር የጋዜጠኞቹ እስራት የምያንማር መንግሥት ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ስለመሆኑና ጋዜጠኞቹ እስር ቤት ውስጥ በሚያሳልፏቸው በእያንዳንዱ ቀናት የአገሪቱ መንግሥት ለፍትህ መስፈን ሊያበረክተው የሚገባው አስተዋፅዖ እያመለጠው እንደሆነም ተናግረው ነበር፡፡
ጋዜጠኞቹ ከመታሰራቸው ቀደም ብሎ የምያንማር መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው የራኪን ግዛት ውስጥ በሚኖሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ ስለፈጸሙት ግድያ የምርመራ ዘገባ እየሠሩ ነበር፡፡ ጋዜጠኞቹ የሠሩት የምርመራ ዘገባም የ2019 የፑሊትዘር ሽልማት (Pulitzer Prize) የዓለም አቀፍ ዘገባ (International Reporting) ዘርፍና በሌሎች የጋዜጠኝነት ሽልማቶች አሸናፊ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ ዋይኔ ሃይ የምያንማሯ መሪ ኦንግ ሳን ሱ ክዪ የአገሪቱ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የሚፈፅሙትን ገደብ የለሽ በደልና ወንጀል ማስቆም አለመቻላቸው በአንድ ወቅት “የፍትህ፤ የዴሞክራሲና የእኩልነት ጠበቃ ናቸው” ተብለው ውዳሴ የጎረፈላቸው የኖቤል ተሸላሚዋ ሴትዮ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ትልቅ ተቃውሞ እንዲገጥማቸው ምክንያት መሆኑና የሮሂንጋዎች ጉዳይ በምያንማር ውስጥ ትልቅ አጀንዳ ስለመሆኑ ከባንኮክ ባሰራጨው ዘገባው አመልክቷል፡፡ የምያንማር መንግሥት የአገር ምስጢር የሆነ ወታደራዊ መረጃ ለዘገባ ተጠቅማችኋል ብሎ በታኅሣሥ ወር 2010 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ያዋላቸውንና የሰባት ዓመታት እስር የፈረደባቸውን ሁለቱን የሮይተርስ ጋዜጠኞች እንዲፈታ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረገው ጫና በርትቶበት ነበር፡፡
ለአብነት ያህል ጋዜጠኞቹ የታሰሩበትን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋች ቡድኖች ባሰናዱትና በምያንማር ዋና ከተማ በተካሄደ ሰልፍ “ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” የሚል መፈክር በማሰማት፣ መንግሥት ጋዜጠኞቹን እንዲለቅቅ ተጠይቆ ነበር፡፡ በወቅቱም ሰልፈኞቹ የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ፤ እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማፈን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም አበክረው አሳስበው ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፤ ዲፕሎማቶች፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ኮንነው የምያንማር መንግሥት ጋዜጠኞቹን በነፃ እንዲያሰናብታቸውም ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዋ ሎን እና ካው ሶ ኡ በእስራት ላይ በነበሩባቸው ወራት በርካታ ሽልማቶችን አሸንፈዋል፡፡ በዚህም፤ ዝነኛውና አንጋፋው “ታይም” (Time) መጽሔት የ2018 “የዓመቱ ሰው” (Person of the Year) ሽልማቱ ውስጥ ካካተታቸው ግለሰቦች መካከል ሁለቱ ጋዜጠኞች የክብሩ ተጋሪዎች መሆን ችለዋል፡፡
ከሁለቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ የመጽሔቱ የዘንድሮው ተመራጮች ግድያው ዓለምን እያነጋገረ የሚገኘው ሟቹ ሳዑዲ አረቢያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ፤ ባለፈው ሰኔ ወር አምስት ሠራተኞቹ (አራት ጋዜጠኞችና አንድ የሽያጭ ሠራተኛ) የተገደሉበት የአሜሪካው “ካፒታል ጋዜጣ” (Capital Gazette)፣ ፍሊፒናዊቷ የ2018 የ“ሲ.ፒ.ጄ “(Committee to Protect Journalists – CPJ) የዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ ማሪያ ሬሳ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
የ2019 የፑሊትዘር ሽልማት (Pulitzer Prize) የዓለም አቀፍ ዘገባ (International Reporting) ዘርፍ አሸናፊዎችም እነርሱ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ፤ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን (World Press Freedom Day) በየዓመቱ ሚያዝያ 25 (May 3) ሲከበር የሚሰጠውና ለፕሬስ ነፃነት መከበር ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፤ ተቋማትና አካላት በተለይ ደግሞ በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ለፕሬስ ነፃነት መከበር መስዋዕትነት ለሚከፍሉ ባለሙያዎችና አካላት የሚበረከተው ዓመታዊው የዩኔስኮ/ጉሌርሞ ካኖ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት (UNESCO/Guillermo Cano World Press Freedom Prize) የ2019 አሸናፊዎች እነዚሁ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
በዚህ ሽልማትም 25 ሺህ ዶላር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ክብርና ታዋቂነት ያገኛሉ፡፡ ምያንማር በወታደራዊ መንግሥት በምትተዳደርባቸው ዓመታት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ክፉኛ የታፈነ እንደነበር ይነገራል። በወቅቱም በርካታ ጋዜጠኞች ለስደት፤ ለእስራትና ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ቴይን ሴይን የተባሉት የወታደራዊው መንግሥት ባለስልጣን እ.ኤ.አ በ2011 ወደመሪነት ከመጡ በኋላ በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን አሠራርና ነፃነት ላይ ተስፋ ሰጪ ለውጥ መታየት ጀምሮ ነበር፡፡ ቅድመ ምርመራ እንዲቀርና ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ ጋዜጠኞች ስለአገሪቱ ጦርና ስለወታደራዊ መስሪያ ቤቱ የሙስና ቅሌት መዘገብ ህልም ሆኖ ቀርቶባቸዋል ይባላል። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች እስራትም ምያንማር ውስጥ ጋዜጠኞች ምንም ዋስትና እንደሌላቸው ማሳያ እንደሆነ ሲገልጹ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 ለረጅም ዓመታት በመብት ተሟጋችነታቸው የሚታወቁት ኦንግ ሳን ሱ ኪዪ ወደመሪነቱ መንበር ሲመጡ ለፕሬስ ነፃነት እንደትልቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፤ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ክሪስፒን ይናገራሉ፡፡
“ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ” (National League for Democracy – NLD) የተባለው የኦንግ ሳን ሱ ኪዪ ፓርቲ በምርጫ አሸንፎ ስልጣን በያዘ ማግሥት በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ቢፈቱም ፓርቲው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እውቅናና ፈቃድ ውጪ መረጃ ለጋዜጠኞች እንዳይሰጥ ያፀደቀው ሕግ የተስፋ ጭላንጭል አይቶ ለነበረው የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ በተለይ ደግሞ መንግሥትን የሚቃወም ማንኛውንም መልዕክት በፌስቡክ መጋራት ለክስ እንደሚዳርግ የሚደነግገው የአገሪቱ የቴሌኮሙኒኬሽንስ ሕግ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ መብት ላይ የተጋረጠ አደጋ ሆኗል፡፡
“አታን” (Athan) የተባለው የመብት ተሟጋች ቡድን ባለፈው ጥቅምት ወር ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ “ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ” ፓርቲ ስልጣን ከያዘ ወዲህ 44 ጋዜጠኞች ተከስሰው ችሎት ቀርበዋል። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ለችሎት የቀረቡት በዚሁ የቴሌኮሙኒኬሽንስ ሕግ ድንጋጌ ምክንያት ነው፡፡ በዚሁ የሕግ ድንጋጌ ምክንያት ለእስር ተዳርጎ የነበረው የ ‘አታን” መሥራችና ዳይሬክተር ማንግ ሳንግ ካ “ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት በምያንማር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጥቷል፤ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ካልተከበረ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አደጋ ላይ ይወድቃል” ይላል፡፡
ጋዜጠኞች የአገሪቱ ጦር በንቃት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ተጉዘው ዘገባዎችን ለመሥራት ጥያቄ ሲያቀርቡ ፈቃድ እንደማያገኙና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችም ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያልፉት ሂደት አድካሚና ቁጥጥር የበዛበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ “ዴሞክራቲክ ቮይስ ኦፍ በርማ” (Democ ratic Voice of Burma) ለተባለ መገናኛ ብዙኃን ትሠራ የነበረችው ኪምበርሌይ ፊሊፕስ የተባለች ጋዜጠኛ፤ ሕዝቡ ለጋዜጠኞች ያለው አመለካከት መቀየሩንና መረጃ ለመስጠት የነበረው ፍላጎት በእጅጉ መቀነሱን ትናገራለች፡፡
የምያንማር መንግሥት ባለስልጣናት ከወታደራዊ ጉዳዮች ውጪ ባሉ አጀንዳዎች ላይ እንኳን ለጋዜጠኞች መረጃ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው በግልጽ እያሳዩ ነው፡፡ በዚህም የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ዛው ሃታይ የጋዜጠኞችን የስልክ ጥሪዎች እንደማያስተናግዱና በአስራ አምስት ቀናት አንድ ጊዜ ብቻ መግለጫ እንደሚሰጡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በ2018 የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Without Borders – RSF) የፕሬስ ነፃነት መለኪያ መሰረት ደቡብ ምሥራቅ እስያዊቷ አገር ምያንማር ከ180 አገራት መካከል 137ኛ ደረጃ የያዘች ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ስድስት ደረጃዎች ማሽቆልቆሏን ያሳያል፡፡
(የመረጃው ምንጮች፡- አልጀዚራ ፣ ሮይተርስ እና ኤቢሲ ኒውስ)
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በአንተነህ ቸሬ