አዲስ አበባ፡- ሙስናን በመከላከል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሆነ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዳልተወጡ ተገለፀ።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ትናንት በግዮን ሆቴል ከቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ (ቪኢኮድ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ኮሚሽነሩ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም እንደተናሩት፤ ሙስናን በመከላከሉ ረገድ የዴሞክራሲያዊ ተቋማቱም ሆኑ ኮሚሽኑ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ አለመወጣቸውን ተናግረዋል። እንደ ኮሚሽነሩ አቶ አየልኝ ገለፃ፤ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ዋና ዓላማቸው ዴሞክራሲን ማዳበር፤ ለዴሞክራሲ ፀር የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግርና ሌብነትን ማስወገድ ነው።
የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር፤ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የመስራትም ኃላፊነት አለባቸው። ይሁንና ይህን በመከታተልና በመቆጣጠሩም ሚናቸውን በአግባቡ ሲወጡ አይታዩም። “ልክ እንደዴሞክራሲ ተቋማት ሁሉ ኮሚሽኑም የሚጠበቅበትን፤ የሚገባውን እና የተቋቋመበትን ተልዕኮ በተሟላ መንገድ ፈፅሟል ማለት አይቻልም። ከዚህ በፊት የነበሩ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን መወጣት ባለመቻላቸው የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ጭምር አስገድደዋል” ብለዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ የሚገባው ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ጊዜው በግለሰብ ደረጃ ሳይቀር የሙስናን ወንጀል መታገልና ማስወገድ የሚጠይቅ ነው። የሙስናን ወንጀል መታገልና ማስወገድ በተወሰኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚጣል ሥራ ባለመሆኑም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል። ከለውጡ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውንም የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ኮሚሽኑ በዋናነት የማስተማርና የማስተባበር ሥራ በመሥራት ላይ እንዳለ ተናግረዋል። የህግ ማሻሻያና የማቋቋሚያ አዋጅ በማዘጋጀት፤ እንዲሁም ደንቡንም በመሥራት ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በቅርቡም የማሻሻያ ሥራውን ለሚመለከተው አካል በማቅረብና በማፀደቅ ተቋሙ በጠንካራ መሰረት ላይ ተደግፎ ለውጡን የሚያግዝ እንዲሆን የሚሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ከዕለቱ መድረክ የሚጠበቀውም በተለይ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትም ሆኑ ሲቪል ማህበረሰቡ የተደራጁበትን ዓላማ በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ ነው። በዚህም መግባባት ላይ እንደሚደረስም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። የቪኢኮድ ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ በበኩላቸው፤ የሙስና ምክንያት የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ለማስወገድ ጠንካራና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት መኖር እንዳለባቸው ገለፀዋል።
ሁሉም የበኩሉን ሚና ከመውጣቱም በላይ ሙስናን መሸከም የሚጠየፍ ዜጋ ለመፍጠርም መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል። ቪኢኮድም የበኩሉን ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በዕለቱ “መልካም አስተዳደር በማስፈንና ሙስናን በመዋጋት የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ሚና” በሚል ሐሳብ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት ዶክተር ጌታሁን ካሳ እንደገለፁት፤ ሙስና የስልጣኔ ደረጃ የማይወስነው የየትኛውም ማህበረሰብ ፈተና ነው።
የበለጠ የሚጎዳው ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ነው። ሙስና የህግ ልዕልናን፣ የማህበረሰብ እሴትን፤ እንዲሁም የምርጫ ሥርዓትም እንደሚያዳክም የተናገሩት ዶክተሩ፣ በተለይ በድሀ አገራት የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን እንደሚያመጣ ገልፀዋል። እርሳቸው መረጃዎችን ጠቅሰው እንዳብራሩት፤ በአፍሪካ የተሻለ ደረጃ ያላቸው ናምቢያ፣ ሞሪሺየስ፣ ቦትስዋና ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2017 ከ186 አገራት መካከል 107ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ዶክተር ጌታሁን የዓለም ባንክን ጥናት ጠቅሰው እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አምስት በመቶ አጠቃላይ አገራዊ ምርት በሙስና ይባክናል። ይህ በአፍሪካ ላይ ድህነትንና ሥራ አጥነትን አምጥቷል ብለዋል። በውይይቱ ላይም የፖለቲካ ድርጅቶች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በአስቴር ኤልያስ