አዲስ አበባ:- የአክሱምን ሐውልት ጥገናና እንክብካቤ የሚያከናውን የሥራ ተቋራጭ ድርጅት ለመቅጠር በዝግጅት ላይ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጠበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የጥገናውን ጥናት ካከናወኑት አማካሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሐውልቱን ጥገና ለሚያከናውነው ድርጅት ይፋዊ ጥያቄ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ከኢጣሊያ የተመለሰውን ሐውልት የተከለውና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለው ላታንዚ የተባለው ድርጅት የሐውልቱን ጥገና እንዲያከናውነው አማካሪ ድርጅቶቹ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
ባለስልጣኑ በዚህ ሳምንት ከአማካሪ ድርጅቶቹ ጋር ከሚያደርገው ውይይት በኋላም ላታንዚ ጥገናውን እንዲያከናውን ጥያቄ ለማቅረብ እቅድ ተይዟል። እንደርሳቸው ገለፃ፤ ለጥገናው የሚያስፈልገው በጀት ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ተብሎ በሚመደበው የካፒታል በጀት ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት ደረጃ በደረጃ ማግኘት እንደሚቻል ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አቅጣጫ ተሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም በቅርቡ ኢጣሊያ ለሐውልቱ ጥገናና እንክብካቤ ድጋፍ እንደምታደርግ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ቃል ገብተዋል።
ከአክሱም ሐውልቶች መካከል 24 ሜትር ርዝመት ያለውንና “ቁጥር ሦስት” በመባል የሚታወቀውን ሐውልት ለመጠገን የሚያስችለውና ኤም ኤች ኢንጂነሪንግና ስቱዲዮ ክሮቺ በተባሉ ድርጅቶች የተካሄደው ጥናት በሰኔ 2010 ዓ.ም ቢጠናቀቅም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ጥናቱን ለመገምገምና ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ ለመስጠት የወሰደው ጊዜ ስራው ቶሎ እንዳይጀመር ማድረጉንም ጠቁመዋል።
“ቁጥር ሁለት” በመባል የሚታወቀው ሐውልት ከኢጣሊያ ተመልሶ ሲተከል በሌሎቹ ሐውልቶች ላይ መነቃነቅና ንዝረት እንዳይፈጠር ተብሎ በገመድ የተወጠረው “ቁጥር ሦስት” ሐውልት ከቆመበት የመቃብር ስፍራ ጋር በመሆኑ አፈሩም በውሃ እየታጠበ በመምጣቱ በፕሮጀክቱ ጥገናና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
የአክሱም ሐውልቶች በ1972 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገበና በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ጎብኝዎች የሚያስተናግዱ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ሲሆኑ፤ አሁን አሁን በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ችግሮች ተደቅነውባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በአንተነህ ቸሬ