. በ2012 ዓ.ም ከታክስ ማሻሻያው ከ20 እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ይጠበቃል::
አዲስ አበባ፦ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ መሰብሰብ ባለመቻሉ በተጨማሪ እሴት ታክስ፣ በኤክሳይዝ ታክስ እና በተርን ኦቨር ታክስ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑን ገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ። የኢ᎐ፌ᎐ዴ᎐ሪ ገንዘብ ሚኒስቴር የአንድ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ላይ በትናንትናው እለት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት፤ በሀገራችን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ መሰብሰብ አልተቻለም።
በመሆኑም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የገቢውን መጠን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ያገኘው ጉዳይ የፖሊሲ ጉዳይ ነው። ገቢ ከታክስ ፖሊሲው ጋር ትልቅ ቁርኝት እንዳለው ጠቅሰውም፤ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያ ሀሳቦች ላይ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። በተለይ የታክስ መሰረቱን ለማስፋት የኤክሳይዝ ፖሊሲዎችን በአዲስ መንገድ ለማሻሻል፤ የተጨማሪ እሴት ታክሱን ለማስተካከል እና የቁርጥ ግብር አሠራርን ማሻሻያ ለማድረግ በትኩረት መሠራቱን ገልፀዋል።
የኤክሳይዝ ታክስ፣ የተርን ኦቨር ታክስ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ላይ ማሻሻያ ተሠርቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁንና በቅርቡ ለምክር ቤቱ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል። በ2012 ዓ.ም ከታክስ ማሻሻያው ከ20 እስከ 30 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ገቢ ይጠበቃል ብለዋል። የቁርጥ ግብር አሠራር ማሻሻያን በተመለከተ ችግሩ በክልሎች በተለየ መልኩ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ በርካታ ክልሎች ላይ ገቢ ከመሰብሰብና ከመልካም አስተዳደር አኳያ ችግሮች በስፋት መስተዋላቸውን ተናግረዋል።
ከክልሎች ጋር በጉዳዩ ላይ በመነጋገር የቁርጥ ግብሩን የሚያሻሸል ሰነድ ተዘጋጅቶ መላኩንና ክልሎቹ ሰነዱን ተግባራዊ ያደርጉታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል። እንደ ዶከተር እዮብ ገለፀ፤ ኢኮኖሚው ሊያመነጭ የሚገባውን ገቢ አለማመንጨቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የማክሮ ኢኮሚኖሚ ሚዛን መዛባት ለማስተካከል ያግዛል። ለፈለግናቸው የኢንቨስትመንት ጉዳዮች፤ በተለይ በትምህርትና በግብርና ላይ አተኩሮ መሥራት እንዲቻል ተጨማሪ ጉልበት ይሆናል።
ዶክተር እዮብ በሌላ በኩል፤ የአገሪቱ የልማት ፍላጎት ብዙ ቢሆንም ገቢው ግን ውስን በመሆኑ ባለፈው አንድ ዓመት ከልማት አጋሮች በተለይም ከቻይና እና ከአውሮፓ ህብረት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል። ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች ለማግኘት ታቅዶ አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መገኘቱንና ሁለት ነጥብ 86 ቢሊዮን ብሩ ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት መግባቱን ገልፀዋል።
የብድር አከፋፈሉ ላይ መሻሻሎች መኖራቸውንና በዘጠኝ ወሩ 14 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ ስምንት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የውጭ ብድር ተከፍሏል። አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት የፋይናንስ ሥርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ ወጪ ያደርጉ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር እዮብ፤ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ቸግሩ የከፋ ነው ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ በማድረግ በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የክፍያ ሥርዓት ተዘርግቷል።
ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦትጪ እቃዎች ሆነው ዋጋቸው ጨመረም አልጨመረም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ ዕቃዎች ላይ፤ እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤንነት የሚጎዱና ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ ዕቃዎችን አጠቃቀም ለመቀነስ ሲባል የተጣለ ታክስ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በዳንኤል ዘነበ