• የኅብረት ስምምነት ባልፀደቀበት ደንብና መመሪያ አውጥቷል-ሠራተኞች • የህብረት ስምምነቱ ባይፀድቅም የሰው ሀብት መመሪያ የማውጣትና ሥራ ላይ የማዋል ስልጣን አለን -ድርጅቱ
አዲስ አበባ፦ በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ድርጅቱ የኅብረት ስምምነት ባልፀደቀበት ደንብና መመሪያ አውጥቷል በማለት ቅሬታቸውን ገለፁ።
በድርጅቱ የባስ ካፒቴንና የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዳዊት ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ መሥሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ሀብት መመሪያዎችና ደንቦች ያልነበሩት በመሆኑ መተዳደሪያ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሂደት ላይ ይገኛል። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የመነሻ ሀሳቦች ወደ ድርጅቱ ሠራተኞች ወርደዋል። ሠራተኛውም በረቂቅ ሰነዱ ላይ ተወያይቶ ማዳበሪያ ሀሳቦችን ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በመውሰድ ማካተቱን ተናግረዋል።
“ድርጅቱ የኅብረት ስምምነት ባልፀደቀበትና ሠራተኛው ባልተስማማበት ሁኔታ የራሱን መመሪያና ደንብ አውጥቶ ‹በዚህ መተዳደሪያ ደንብ ትተዳደራላችሁ› መባሉ ተገቢ አይደለም›› የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ሠራተኛው ሲወያይ የነበረው የኅብረት ስምምነቱን ለማዳበር እንደነበር ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ውይይቱ አንድ ውሳኔ ላይ ደርሶ ሠራተኛው መስማማቱንና አለመስማማቱን በመግለፅ የፈረመውም ሆነ የተያዘ ቃለ ጉባኤ በሌለበት ድርጅቱ መመሪያና ደንብ በማውጣቱ ሠራተኛው ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል። በዚህም ሚያዝያ 16 ቀን 2011 ዓ.ም የተጠራው ስብሰባ ተበትኗል›› ብለዋል።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ፈለቀ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ አዋጅ በሚፈቅደው መሰረት ከምልመላ ጀምሮ እስከ ቅሬታ አቀራረብ ድረስ አጠቃላይ ሥራው የሚመራበትን የሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ እንዳወጣ ተናግረዋል። ሠራተኞቹ በስድስት ቡድኖች ተከፋፍለው የማህበሩ ምክትል ሰብሳቢ በተገኙበት መድረክ በተዘጋጁት ስድስት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ሠራተኞቹ ውይይት ማድረጋቸውንም አስረድተዋል።
እንደኃላፊው ገለፃ፣ በውይይቱ የተካተቱን ግብዓቶች በመጨመር ረቂቅ መመሪያው ለቦርዱ ቀርቧል። ቦርዱም መመሪያውን ከማፅደቁ በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ፣ የኦዲት፣ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት እንዲሁም የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በማቅረብ አስተያየት እንዲሰጡበት አድርጓል። ቦርዱ የተሰጠውን አስተያየት ጨምሮ ከሚመራቸው መሰል ተቋማት ጋር በጋራ በመወያየት ለአንድ ሳምንት የመናበቢያ ጊዜ በመስጠት ከፋይናንስና ከግዥ መመሪያ ውጭ ያሉትን አራት መመሪያዎች በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም አፅድቋል።
ድርጅቱ የህብረት ስምምነቱ ባይፀድቅም የሰው ሀብት መመሪያ የማውጣትና ሥራ ላይ የመዋል ስልጣን እንዳለው የገለፁት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ የህብረት ስምምነቱን ለማፅደቅም ሥራዎች መጀመራቸውንና ከሁለት ዓመታት በላይ እንደወሰደባቸው ጠቁመዋል። ይህ በመሆኑም በአንዳንድ ሠራተኞች ዘንድ በወር ውስጥ ሁለትና ሦስት ጊዜ መኪና የማጋጨት፣ በሥራ ሰዓት መኪናን የማቆምና ከመስመር የመውጣት፣ ትኬት የተሸጠበትን ገንዘብ ለግል ጥቅም የማዋል አጋጣሚዎች መፈጠራቸውንና አጠቃላይ ሥርዓት አልበኝነት መከሰቱን አስታውሰው፣ ቦርዱ ለዚሁ ችግር መፍትሔ ያለውን ፍትሀዊ የሆነ የሰው ሀብት አስተዳደር መመሪያ በማውጣትና ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት አምኖ መመሪያው ተግባራዊ እንደሆነ አብራርተዋል።
አመራሩን ሳይጨምር በድርጅቱ ውስጥ ካሉት አንድ ሺህ 881 ሠራተኞች መካከል የሠራተኛ ማህበር አባላት የሆኑት 388 ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውንና በአሁኑ ወቅት ቅሬታ እያነሱ ያሉት የማህበሩ አባላትም ሆኑ አባል ያልሆኑ ሠራተኞች የፀደቀውን ደንብና መመሪያ በተገቢው መንገድ አውቀውና ተረድተው እንዳልሆነም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
በፍሬህይወት አወቀ