አዲስ አበባ፤- ዜጎችን በማንገላታት፣ በማፈናቀል እና የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀም የተጠረጠሩ 420 አፈናቃዮች አለመያዛቸውን የሠላም ሚኒስቴር አስታውቋል።
በየደረጃው በማፈናቀል ተግባር ላይ የተሳተፉ የፖለቲካና የፀጥታ ሀይል አባላትም በክልሎችና በከፍተኛ አመራሩ ትብብር ማነስ በህግ ጥላ ስር ለማዋል መቸገሩንም አስታውቋል። የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፤ ትናንት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀረቡ እንዳስታወቁት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 4 ሺ 43 መዝገቦች ላይ ምርመራ ተደርጎ በ2 ሺ 276ቱ ላይ አቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰርት ተልኳል።
ከማፈናቀል ጋር በተያያዘ እስካሁን ክስ የተመሰረተው በ4 መቶ 68 ላይ ብቻ ነው። ከእነዚህም 420ዎቹን አፈናቃዮች በህግ ጥላ ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። ሚኒስትሯ፤ እንዳሉት አፈናቃዮችን ወደ ፍትህ አደባባይ ለማቅረብ በየደረጃው ከሚገኙ የፖለቲካና የፀጥታ አመራሮች ላይ የሚታይ የቁርጠኝነት ማነስ ችግር አለ። በተለይም በማፈናቀል ተግባሩ የተሳተፉ የተለያዩ አመራሮች ተጠያቂነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ሲጥሩ ይታያል።
ዜጎች ከተፈናቀሉ በኋላም ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ጉዳት ያደረሱም አሉ። ዜጎች እንዲፈናቀሉና ከተፈናቀሉም በኋላ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ በማድረግም መረጋጋት እንዳይፈጠር እየሠሩ ነው። የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ከተመለሱና ሠላም ከወረደ እራቁታቸውን ስለሚቀሩ መፈናቀሉና ግጭቱ እንዲቀጥል የሚሠሩ አካላት መኖራቸውንም አመላክተዋል። በአገሪቱ ህገ ወጥ የገንዘብ፣ የሰው፣ የኮንትሮባንድ፣ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎች ተሳስረው እየተከናወኑ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ያነሱት ሚኒስትሯ ከወንጀለኞቹ ጋር በትብብር የሚሰራ አመራር አለ ብለዋል።
ይህን አመራር በተቀናጀ መንገድ መጠየቅ ጀምረናል። በማስታረቅ ብቻ ሰላም ማምጣት አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል። ሚኒስትሯ፤ እንዳገለፁት በአገሪቱ ከማንነትና ከወሰን ጋር በተየያዘ ሊፈጠሩ የነበሩ ከፍተኛ ግጭቶች እንዲከሽፉ ተደርገዋል። በአገሪቱ ያለው የግጭት ድግግሞሽም ቀንሷል። በመንግሥት፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በእናቶች፣ በኪነጥበብና በስፖርት ቤተሰብ የተቀናጀ ሥራ ከፍተኛ ግጭቶች እየቀነሱ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።
የግጭቶች ድግግሞሽና ትላልቆቹ ግጭቶች እየቀነሱ የመጡ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች ግን አሁንም አነስተኛ ግጭቶች ይታያሉ። ትንሽ ግጭት ሲፈጠር ከሰማይ መዓት እንደወረደ በማስመሰል ተደራጅተው በማህበራዊ ሚዲያ አንዱን በሌላው ላይ በመቀስቀስ አገሪቱ በቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ የሚሠሩ አካላትም አሉ። ይህን የሚያደርጉ አካላት ዛሬ የሚቆሰቁሱት እሳት ነገ ለእነሱም እንደሚተርፍ አውቀው ከዕኩይ ተግባራቸው መቆጠብ ይገባቸዋል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
በየደረጃው በማፈናቀል ተግባር ላይ የተሳተፉ የፖለቲካና የፀጥታ ሀይል አባላትን በክልሎችና በከፍተኛ አመራሩ ትብብር ማነስ በህግ ጥላ ስር ለማዋል አስቸጋሪ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ዜጎችን በማፈናቀል ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ አካላትን በተለያየ ደረጃ ላይ ባሉ አመራሮች ትብብርና ቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም በተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ነፃ አውጭዎች በመቆጠር በህግ ጥላ ስር ለማዋል መቸገራቸውንም ተናግረዋል።
ይህን ችግር ለመፍታትም ጥርሳችን ነክሰን ወገባችን አጥብቀን እንሠራለን ብለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የዜጎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጻረሩ አካላት በምንም መመዘኛ ትክክል አይደሉም። መንግሥትም ህግ የማስከበር ሀላፊነቱን መወጣትና አጥፊዎችንም መጠየቅ ይገባዋል። ለተፈናቃዮች የሚደረገውም ድጋፍ ተጠናከሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ