አዲስ አበባ፡- የግብር ንቅናቄ በሀገር ደረጃ ከተጀመረ ወዲህ በከተማ እና በክፍለ ከተማ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ ከንግዱ ማኅበረሰብ ወይም ከግብር ከፋዩ ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የተዘረጋው ስርዓት በከተማዋ የሚሰበሰበው ገቢ እየጨመረ እንዲመጣ እያስቻለ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የእቅዱ 93 ነጥብ 88 በመቶ ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ፡፡
የቢሮው የታክስ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ግርማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሠራተኛው ተነሳኝነት እና የተሰጣቸው ስልጠና፣ከግብር ከፋዮች ጋር የተደረጉ ውይይቶች እና ተቀራርቦ መሥራት የተቻለበት ሁኔታ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የተሻለ ገቢ እንዲገኝ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
‹‹ሁለት ሺ ወጣቶች ቀጥረን በግብር ላይ ትምህርት እየሰጡ ናቸው›› ያሉት አቶ ዮሴፍ፣ ወጣቶቹ የንግዱ ማህበረሰብ ወደ ግብር ስርዓቱ እንዲገባ መሥራታቸው ሌላው ለገቢው መጨመር ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በግብር መረብ ውስጥ ያልተካተቱ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ሌሎችን ወደ ግብር መረቡ ለማስገባት እንደ ፖሊስ እና ደንብ ማስከበር ያሉ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ችግሩን በአብዛኛው ለመፍታት የሚሠራው በትምህርትና በምክር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነጋዴው በራሱ ወደ ግብር መረቡ ለመግባት ጥረት በማድረግ ህዝብንና መንግሥትን ማገዝ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
አቶ ዮሴፍ ከከተማዋ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 25 ነጥብ 38 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰው፡፡ አፈፃፀሙም የእቅዱ 93 ነጥብ 88 በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ፤ ገቢው የተሰበሰበው ለመሰብሰብ በእቅድ ተይዞ ከነበረው 27 ነጥብ 04 ቢሊየን ውስጥ ሲሆን፣ ክንውኑ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመርካቶ ቁጥር ሁለት የታክስ ጉዳዮች ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ነጋሽ በበኩላቸው፤ ለሰው ኃይሉ በአመራር፣ በግብር አዋጅና በአቅም ግንባታ ላይ ያተኮሩ ወደ ሃያ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ጠቅሰው፣ ዓላማውም ግብር ከፋዩ የሚያነሳቸውን የአቅም ችግሮች መፍታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በመርካቶ ቁጥር ሁለት ብቻ ከ10ሺ284 መካከለኛ ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ለግብር ከፋዩ የንቅናቄ ሰነድ በማዘጋጀት እየተሠራ ነው፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ማለትም ከመሳለሚያ እህል በረንዳ አውቶቡስ ተራ አንዋር መስጊድ አካባቢና ተክለሃይማኖት በአብነት ሰባተኛ ዙሪያውን እና መሀል መርካቶ ባሉ ንግድ ቦታዎች የቀን ገቢ ግምት ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ፀጋዬ፣ አሁን ችግሩ 98 በመቶ መፈታቱንም አመልክተዋል፡፡
በክፍለ ከተማውም በዘጠኝ ወራት ውስጥ 967 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ 669 ሚሊዮን መሰብሰቡንና ይህም የዕቅዱ 70 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩ ዊሪቱ በገቢ ዙሪያ ነጋዴውን ሰብስበን በማነጋገር ግንዛቤ በመፍጠር መረጃን በመለየት የግብር ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ብሩ ገለጻ፤ነጋዴዎች በአክስዮን ተሰባስበው የሚያካሂዷቸው ግንባታዎች በአብዛኛው ተጠናቀው ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህም በአንድ አካባቢ በተለያዩ ዘርፎች ንግዱን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
አክሲዮኖቹ ለገበያ ማዕከልና ለተከራይ የፈጠሩት ዕድል ለገቢው ያደረገው አስተዋፅኦም ቀላል እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ አክሲዮኖች የሕንፃ ግብር እንደሚከፍሉ፣ በአክሲዮን ድርሻቸውም ግለሰቦችም እንዲሁ እንደሚከፍሉ እንዲሁም አከራይተው ሲሠሩም እንዲሁ የንግድ ግብር እንደሚከፍሉ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ከ430 ሺ በላይ ግብር ከፋይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ