አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከሚሰጠው ትምህርት፣ ስልጠና፣ የምክር አገልግሎትና ምርምር በተጨማሪ እየሰጠ ያለውን የማኅበረሰብ አገልግሎት ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገለፀ።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዓለማየሁ አበበ ትናንት የሲቪል ሰርቪስ ኤፍ ኤም 100 ነጥብ 5 ሥርጭት የጀመረበትን ሦስተኛ ዓመት በዓል አስመልክተው ባደረጉት ንግግር እንዳብራሩት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙበት አካባቢ ማኅበረሰብ ተፈላጊነታቸውን ማሳየትና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያው ላሉት የየካና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎች ወረዳዎች ድረስ በመውረድ ድጋፍና ዕገዛ እያደረገ መሆኑን ዶክተር አለማየሁ ጠቅሰው፣በቀጣይም የተጀመረውን ድጋፍና እገዛ ጠቅላላ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አባላት ኃላፊነት በመውሰድ አገልግሎቱን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ሞገስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ሦስት ዓመታት የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡የዝግጅቱ ዋነኛ ዓላማ የተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፁ ማድረግ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተማሪዎችና ሠራተኞች ስለማኅበረሰብ አገልግሎት ያላቸው ግንዛቤ እየዳበረ እንዲመጣ ማስቻልም ነው።
በቦሌና የካ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች የባለሙያ ስልጠና የማግኘት ችግር እንደነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ዩኒቨርሲቲው ባለው የሥልጠናና የማማከር ዘርፍ አማካይነት ይህንን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቅሰዋል። እስካሁንም ለዕድሮችና ሌሎች አደረጃጀቶች የተለያዩ ሥልጠናዎች መሰጠቱን አቶ ወንድሙ አስታውሰዋል ።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በኢንጅነሪንግ ኮሌጁ አማካይነት ዲዛይኖችን፣መጋዘኖችን እና የተለያዩ ህንፃዎች ባሉት ኢንጅነሮች አማካይነት በነፃ እየሰራ መሆኑን።
ገንዘብ እያሰባሰበ በአካባቢው ላሉ ዐቅመ ደካሞች ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም የደም ልገሳ አገልግሎት በሰራተኞቹ በመስጠትና ማኅበረሰቡንም ለዚሁ ተግባር እየቀሰቀሰ እንደሆነ አቶ ወንድሙ ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ“ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” በሚል የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ የደም መለገስ እንደሚከናወንና ለአራት ቀናት የሚቆይ የመፃህፍት ሽያጭ ዐውደ ርዕይ እንደሚኖር ታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ