– ሦስት የባህላዊ የህክምና መድኃኒቶች በቀጣዩ ዓመት ለገበያ ይቀርባሉ
አዲስ አበባ፡- በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ የተለያዩ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው ተገለፀ። ባህላዊ የህክምና መድኃኒቶች ላይ ሲደረግ የቆየው ምርምርና ቅመማ ስራ ተጠናቆ በቀጣዩ ዓመት ለገበያ ማቅረብ እንደሚጀመር ታውቋል።
የተለያዩ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበትና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየሁለት አመቱ የሚያካሂደው አራተኛው ሀገር አቀፍ የጤና ጉባኤ ትናንት በይፋ በተጀመረበት ወቅት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደተናገሩት፤ የጤናውን ዘርፍ በጥናትና ምርምር መደገፍ እጅጉን አስፈላጊ ነው።ይህ እንደመሆኑም በዘርፉ የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ይበልጥ ማጎልበት የግድ ይላል።
«ባህላዊ የህክምና መድኃኒቶች ብዙ የምናወራባቸው ግን ምንም ያልሰራንባቸው ናቸው፤ ኢትዮጵያም ይህን የጥንት ሀብት አልተጠቀመችበትም» ያሉት ዶክተር አሚር፤ በዚህ ዓመት ሶስት ባህላዊ የህክምና መድኃኒቶች ለገበያ ለማቅረብ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የእነዚህ መድኃ ኒቶች የምርምርና ቅመማ ስራ ዘጠና በመቶ መጠናቀቁን አመልክተዋል። መድኃኒቶቹም በሚቀጥለው ዓመት ወደ ገበያው በመግባት ጥቅም ላይ እንደሚውሉም ገልፀዋል፡፡
በአራተኛው ሀገር አቀፍ የጤና ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ ምርምሮችም ዘርፉን በጥናትና ምርምር ለማስደገፍ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ያመላከቱት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ለሁለተኛው የአገሪቱ የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚጠቅሙና እየተከለሰ ለሚገኘው የጤና ፖሊሲ በግብዓትነት የሚያገለግሉ ግኝቶች እንደሚመላከቱበትም አብራርተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች በአይነትም በጥራትም መሻሻል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገለፃ፤መንግስት ለተለያዩ ዘርፎች ውጤታማነት በተለይ ለምርምር ስራዎች ተገቢውን ትኩረትና አስፈላጊውን በጀት መድቧል። በርካታ ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ተፈጥረዋል። የባለሙያዎች ቁጥር ጎልብቷል።ይሁንና አሁንም ቢሆን ጤናውን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች በበቂ መልኩ እየተከናወኑ አይደለም።
የሚከናወኑ ጥናቶችም ቢሆን ከችግር ፈቺነታቸው በተለይ ለህትመት በቅተው ተደራሽ የሚሆኑበት አግባብ ደካማ መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤በቀጣይ መሰል ችግሮች መታረምና የምርምር መድረኮችም መጠናከር እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም በጤናው ዘርፍ ምርምርና ጥናቱን የሚሰሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሰራራቸውን መፈተሽ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ፕሮፌሰሩ፤«ተቋማቱ የምርምርና ጥናት አካሄድና የትኩረት አቅጣጫቸውን ስለመከለስ ሊያስቡ ይገባልም»ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በበኩላቸው፤በዚህ ጉባኤ የሚቀርቡ ምርምሮች በተለይ ለፖሊሲ አውጪ አካላት ግብዓት ሆነውም ለጤና ዘርፍ ውጤታማነት እንደሚያገልግሉ አመላክተዋል።
«በተቀናጀ የመረጃ ሽግግር የህብረተሰብ ጤና ለማሻሻል›› በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ጉባኤ፤ ከሚቀርቡ የምርምሮች ውጤቶች መካከል፤ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፣በምግብና ስነ- ምግብ፣በዘመናዊ መድሃኒት የተለመዱ በሽታዎች፣በስርዓተ ጤና፣ በባህላዊ መድሃኒት እንዲሁም ጥራት ያለው የጤና መረጃ አጠቃቀምን የሚዳስሱት ይጠቀሳሉ፡፡
ከ200 መቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የምርምር ፅሁፎች በሚቀርቡበት በዚህ ጉባኤ፤ ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪ አካላት፣ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ500 መቶ በላይ ተሳታፊዎች እንደተገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
ታምራት ተስፋዬ