የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የስንብት ሥነሥርዓት ከትናንት በስቲያ በሚሌኒየም አዳራሽ በተፈፀመበት ወቅት አብሮ አደጎቻቸውና የትግል ጓዶቻቸው ፕሬዚዳንቱ የነበራቸውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስብዕና ገልፀዋል።
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ዋና ፀሀፊና አብሮ አደግ አስራት ጣሴ
እኔና ዶክተር ነጋሶ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው በ1958 ዓ.ም ስድስት ኪሎ በሚገኘው በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ በልኡል በእደ ማርያም የመሰናዶ ትምህርት ቤት ነው። በወቅቱ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስራ አንደኛ ክፍልን ካጠናቀቁ ተማሪዎች በውጤታቸው ከፍተኛ የሆኑትን መርጦ ለመምህርነት ሙያ የሚያዘጋጅ ፕሮግራም ነበር።እኔ ከአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነጋሶ ደግሞ ከአዳማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጥቶ ተገናኘን።
እንደ ልዩ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ በአንድ መኝታ ቤት በአንድ ተደራራቢ አልጋ ላይ ተመደብን ነጋሶ ከላይ እኔ ከታች ደረሰን።በመጀመሪያው ቀን የአልጋው ብሎን ባለመጥበቁ ነጋሶ ከላይ እኔ ላይ ወደቀ ፡፡ በወቅቱ እኔ ባልጎዳም ነጋሶ ራሰ በራ ስለነበር ሽማግሌው ወደቀ ተባለ።
የሁለታችንም ምርጫ የታሪክ ትምህርት መከታተል በመሆኑ አንድ ክፍል ተመድበን በአመቱም ዩኒቨርሲቲ ገብተን ለአራት አመታት በአንድ ክፍል ተምረን ትምህርታችንን ጨረስን። በልኡል በእደማርያምና በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በጥሩ ጓደኝነት ላይ የተመሰረተ
ግንኙነት ነበረን። ዶክተር ነጋሶ ወደ አዳማ የሄደው ከደምቢ ዶሎ በመሆኑ ጭምር በወቅቱ አዲስ አበባ ከምትሰጠው የከተሜነት ባህሪ ጋር እንዲላመድ ያደረግኩት እኔ ነኝ። እኔ በቅድሚያ የሰንጋ ተራ ከዛም የአራት ኪሎ ልጅ ስለነበርኩ በእነዚህ ሁለት አካባቢዎች ያዳበርኩትን ባህሪ የቻለውን ያህል እንዲወስድ አድርጌያለሁ።
ደጃች ውቤ ሰፈር ዳንስ ቤቶችን መጎብኘት ጀመርን ፤ መጠጥም ቢሆን ከባለ ኬሻው ቢራ ፊሊተር ጠላ እስከ ጠጅ ድረስ እንቀማምስ ነበር።ነጋሶ እኔ ባላስተምረውም ሲጋራ ማጨስ ጀመረ። የጉርምስና እድሜያችንን ጣፋጭ ለማድረግ ቁጥብ አልነበርንም፡፡ ዶክተር ነጋሶ በአስተዳደጉም ሆነ በባህሪው ለስላሳና የተረጋጋ ሰው ነበር።የፖለቲካ ፍላጎት ፍቅር የዲ ኤን ኤው አካል ስለነበር በተለያየ የፖለቲካ ዘርፍ ይንቀሳቀስ ነበር።
በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቀስቃሴ ንቁ ተሳትፎ ነበረው።በሜጫና ቱለማ ውስጥም ይንቀሳቀስ እንደነበር ይነግረኝ ነበር።በወቅቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ግራ ዘመም ስለነበር የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ማኦይዝም መፅሀፍ በትጋት ያነብ ስለነበር በየሴሉ በመደራጀት የፖለቲካ አክቲቪዝም ባህሪውን በጣም እያነቃቃው እያዳበረውና እያሳደገው ነበር።
ነጋሶ በአብዛኛው የተረጋጋ ሰው ቢሆንም መቆጣትም መጣላትም የሚችል ነው።በተለይም በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ አብረን ስንንቀሳቀስ ያሳይ የነበረው የቁጣ ሁኔታ አንዳንዴ አስገራሚ ነው።እልህም ይቀላቀልበታል፤ ከእኔም ጋር ቢሆን አልፎ አልፎ መፋጠጣችን አልቀረም።ነጋሶ ከቁጣ የመመለስ አቅሙም በጣም ጥሩ ነበር ተገቢ ሆኖ ካገኘውም ይቅርታ ለመጠየቅ ችግር የሌለበት የይቅርታ ሰው ነው።
ለምሳሌ ባደባባይ በህገ መንግስቱ ላይ ህዝቡ ተወያይቷል ማለቴ ስህተት ስለሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ታላቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ ይህም ምን አይነት የይቅርታ ሰው እንደሆነ ይገልፃል።በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ወቅት በተለያዩ የተማሪዎች ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፎች በንቃት ይሳተፍ ነበር፡፡በወቅቱ በተደጋጋሚ የመታሰር በፖሊስ ቆመጥ የመደብደብ ገጠመኞቹ ብዙ ነበሩ።
በወቅቱ ዝምባቡቤ ነፃ ትወጣ ዘንድ በእንግሊዝ ኤምባሲ ይደረግ በነበረውና በሌሎችም ተቃውሞዎች በንቃት ይሳተፍ ነበር።ነጋሶ የኤዱኬሽን ፋክልቲው አባልም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ምክር ቤት አባል በመሆን ተመርጦ አገልግሏል። ከሌሎች ቋንቋ ተራማጅ ተማሪዎች ጋር በመሆን በየፋክልቲውና በየካምፓሱ ተበታትኖ የነበረውን የተማሪዎች ማህበር (ዩዠዋ) ወደ አንድ እንዲመጣ ንቁ ተሳትፎ አድርጎ አሻራውንም አሳርፏል።እያስጠራኝ ብዙ እናወራ ነበር ፤የልኡል በእደማርያም የቀድሞ ተማሪዎች እንድንመሰርት ያነሳሳን ነበር። ዶክተር ነጋሶ በአንድ ወቅት የአንድነት ፓርቲን ሲቀላቀል እኔ የብሄር እንቁላልን ሰብሬ ወጥቻለሁ ብሎም ነበር።
ያን ሁሉ ፈተና አልፎ ነፃነት ዴሞክራሲ ሲመጣ ብዙ ተስፋ ሲገኝ ቢሞትም የታገለላቸው ውጤት አምጥተዋል።ጨካኝ እና አምባገነን መሪዎች ዶክተር ነጋሶን በመርህ ሲለያቸው እንዳጉላሉትና እንደጎዱት ሁሉ ሞቱንም ርካሽ፣ የማይረባና እርባና ቢስ ሊያደርጉት የነበራቸው ተስፋ ከሽፏል። ዛሬ እነሱ በህይወት እያሉ ያላዩትን ክብር እሱ በሞቱ አግኝቷል።
አቶ ሌንጮ ለታ
የቀድሞ የኦነግ ሊቀመንበርና አብሮ አደግ
አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ አብረን ነው የተማርነው፤ብዙ የሚያመሳስሉን ነገሮች ነበሩ ፤ የሁለታችንም አባቶቻችን በሃይማኖት ይሳደዱ ነበር የእነሱ ፅናት ለእሱም ተላልፎ ለአላማው ፅናት ሰጥቶታል። ሁለታችንም ስንወለድ በአካባቢያችን ድርቅ ስለነበር ብዙ እኩዮች የሉንም ፡፡ የሁለታችንም ታናናሾች በቁመት ይበልጡን ነበር።
የነጋሶ መንገድ ጠመዝማዛ ነበር፤ በእግሩ ደምቢዶሎ ጉዞ ጀምሮ በጫማ ጃንሆይ ስር ይገኛል ፡፡ አንዴ በኦነግ አንዴ በተቃዋሚ አንዴ በኢህአዴግ ጎራ ይገኛል ፡፡ ያ የነጋሶ መንገድ አሁን አበቃ። የእኛም መንገድ ከዚህ በኋላ ብዙ የሚረዝም አይደለም ። በመሆኑም እኛም ልክ እንደሱ እየታገልን የልባችንን እየተናገርን ብናልፍ ይሻላል ፡፡ስለሞቱ አናስብ ስላሳለፈው ጊዜ እናስብ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ
ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር የተዋወቅነው የዛሬ 28 አመት በ1983 ዓ.ም የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ ሴኔጋል የተላከውን ቡድን መርተው ሴኔጋል ነበር። ከዛን ጊዜ ጀምሬ እንዳየኋቸው መልካም ስነምግባር ያላቸው አገርን ማገልገል ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ በቀላሉ ከሰው ጋር የሚግባቡ ቀናና ሰዎችን ለማዳመጥ የማይሰለቹ የፈጣሪያቸውን ቃላትና ትምህርት በአግባቡ የተከተሉ ናቸው። ባጠቃለይም አንጋፋው የታሪክ ምሁርና ፖለቲከኛው ዶክተር ነጋሶ ለእምነትና ለህሊና መኖርን ያሳዩ ናቸው ። የግል ጥቅም ሀብት ለእሳቸው ምንም እንዳልነበር በኑሯቸው አሳይተዋል።
ችግር ሳይበግራቸው ከህዝብ በመወገንም ተቀባይነትን ማግኘት ችለዋል። በህይወት እስካለሁ ለሀገሬ የምችለውን አደርጋለሁ ብለው በገቡት ቃል መሰረት ኢትዮጵያን በታማኝነት ብቻ ሳይሆን በምሳሌነትም ማገልገል የቻሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ