ባለፉት አመታት እየቀነሰ የመጣው ቡና በአለም ገበያ ያለው ዋጋ ዘንድሮም በቅርቡ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ማሽቆልቆሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ይህን ተከትሎም ከዘርፉ መገኘት ያለበት የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ሀገሪቱ የቡና የውጭ ምንዛሬ እቅዷን ማሳካት እንድትችል በቡና ግብይት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ዳሳ ዳኒሶ ‹‹በእርግጥም አለም አቀፍ የቡና ዋጋ በዚህ አመት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት ዋጋም ከ20 በመቶ በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡›› ሲሉ በመጥቀስ፤ ምክንያቶቹ ውጪያዊና ውስጣዊ ሊባሉ እንደሚችሉ ያመለክታሉ፡፡ ባለፉት 13 አመታት የቡና አለምአቀፍ ገበያ ዋጋ እየቀነሰ መምጣቱንና አሁን ያለው ዋጋም የዛሬ 13 አመትና ከዚያ በፊት ጋር ሲተያይ ይመሳሰላልም ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ቀርቧል፡፡ ገዢዎችም ተረጋግተው የሚገዙበትና ዋጋ የሚቀንሱበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ሁለተኛው ውጫዊ ምክንያት አለም አቀፍ የቡና ግብይቱ በጥቂት ከፍተኛ ቡና ቆዪዎችና ቡና ነጋዴዎች ተጽዕኖ ውስጥ መውደቁ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም አንድ ኪሎ ቡና ከአንድ ስኒ ቡና ዋጋ በታች እንዲሸጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
‹‹ ከውስጣዊ ምክንያቶች አንዱ በቡና ግብይት የተሰማሩ አካላት የስነ ምግባር ጉድለት ነው። በላኪዎች መካከል የገበያ ሽሚያ ተፈጥሯል፤ በዚህም ከገበያ ዋጋ በታች ዋጋ ዝቅ አድርጎ መሸጥ ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም በብቃት ተደራድረን የተሻለ ዋጋ የምናገኝበትን እድል አጥብቧል፡፡››ይላሉ፡፡
በቡና ዘርፍ ለአመታት በኃላፊነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቡናው ኢንቨስትመንት እየሰሩ የሚገኙትና የህብረት ስራ አባት በመባል የሚታወቁት አቶ ሀይሌ ገብሬ፣‹‹የቡናዋን ዋጋያሳነሰችው ራሷ ኢትዮጵያ ናት››ይላሉ፡፡ ስፔሻሊቲ ቡና ተብሎ ከአለም ቡና በተሻለ ዋጋ ላይ ይገኝ የነበረውን ቡና ሸቀጥ /ኮመዲቲ/ ያደረገችውም አገሪቱ መሆኗን ያስረዳሉ፡፡
ቡና ከቡና ተደበላልቆ እየተላከ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ቡና የድሮ ማዕረጉን እያጣ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡ ቡናው በመደበላለቁ የኢትዮጵያ ቡና መሆኑን ለማወቅ ገዥዎች መቸገራቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
አቶ ሀይሌ‹‹ለቡና ዋጋ መውደቅ አንዱ የአለም ሁኔታ ነው፡፡›› ሲሉ አቶ ዳሳ የጠቀሱትን ሃሳብ ተቀብለው፤ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ቡናዎች በብዛት እየተመረቱ መሆናቸውንና ገዥዎች የኢትዮጵያን ቡና ለቅመምነት ብቻ እየፈለጉት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡‹‹ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ቡና ደግሞ በርካሽ ዋጋ ነው የሚሸጠው፡፡ የአለም ቡና በብዛት ገበያ መግባትም ሌላው ችግር ነው፡፡›› ይላሉ፡፡
አቶ ዳሳ የላኪዎች የስነ ምግባር ችግር ብለው የጠቀሱትን የግብይት ችግር አቶ ሀይሌም ይጋሩታል፡፡ ‹‹ቡና ዛሬ የኤክስፖርት ሸቀጥ አይደለም፡፡ ለገቢ ሸቀጥ ማስመጫ እንደ እቃ በእቃ ንግድ /ባርተር ትሬዲንግ/ እንዲያገለግል እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡ ፡ እነዚህ ወገኖች የሚያተርፉት በሚልኩት ቡና እንዳልሆነም ጠቅሰው፤ከቡና በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ብረትና የመሳሰሉትን ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባትና በውድ በመሸጥ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡‹‹ይህ አደጋ ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ወደፊትም መቆም አትችልም፡፡›› ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹ንግድ መተማመን ይፈልጋል፤ ይሁንና በሀገሪቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ገዥዎች ቡና መግዛት አልቻሉም፤ይደርስልናል አይደርስልንም የሚለውም ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡›› ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡
አቶ ዳሳ መፍትሄዎቹን የአጭርና የረጅም በማለት ይጠቁማሉ፡፡ ከአጭር ጊዜ አኳያ ቀሪዎቹ ወራት በቡና ግብይት ታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለገበያ የሚቀርብበት እንደመሆኑ በእነዚህ ወራት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በማቅረብ እንዲሁም ጥሩ ዋጋ ፍለጋ በሚል ሰበብ ላኪዎች እጅ የሚገኘውን ቡና ወደ ገበያ በማቅረብ ለማካካስ ይሰራል፡፡
ባለፈው አመት የአለም የቡና ዋጋ በቀነሰበት ወቅት መጠን በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ለማሳካት በተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ የቡና ኤክስፖርት ታሪክ ትልቁ የሚባለውን 238ሺ ቶን ቡና መላኩን ጠቅሰው፤ ዘንድሮም ይህን ለማድረግ እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡
‹‹ገዥዎች ሀገር ውስጥ ክምችት ሲበዛ የገቡትን ኮንትራት ጭምር በተለያዩ ምክንያቶች ሀገር ውስጥ እንዲዘገይ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡››ያሉት አቶ ዳሳ፣‹‹ይህን ችግር ለመፍታት በእጃችን ያለውን ክምችት ለመላክ ታቅዶ እየተሰራ ነው ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡
አቶ ዳሳ እንዳሉት፤የግብይት ተዋንያኑን ስነምግባር አለመጠበቅ ችግር ለመፍታት ከብሄራዊ ባንክ ጋር በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጡ አካላትን በማስጠንቀቅ እንዲያስተካክሉ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን፣ይህን በወሳኝ መልኩ ለመከላከል ዝቅተኛ የኤክስፖርት መሸጫ ዋጋ እንዲወሰን ማድረግ የሚያስችል ልምድ ከሌሎች ሀገሮች መገኘቱንና የውሳኔ ሀሳብም ለመንግስት መቅረቡን ያመለክታሉ፡፡
አቶ ዳሳ፣በቡናው ግብይት ዘርፍ ተገቢ ያልሆነውን ተግባር ለማስቆም በአለም ቡና ዋጋ ተመጣጣኝ ነው ተብሎ የሚታሰብ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ መወሰን ለእዚህ ተግዳሮት መሸጋሪያ ነው ተብሎ መታሰቡንም አመልክተዋል፡፡ ይህም በየጊዜው የሚከለስና ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት እንደሚሆን በመግለጽ፡፡
እንደ አቶ ዳሳ ገለጻ፤የእሴት ሰንሰለትን ለመቀነስ፣ከረጅም ጊዜ አኳያ ዘላቂ የገበያ እድል የሚያስገኙ አማራጮችን በመቅረጽ ባለስልጣኑ እየሰራ ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ››የሚባል አለም አቀፍ የቡና ጥራት ውድድር ነው፡፡
አቶ ሀይሌ፣ ለሁሉም ነገር ሰላም ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ገዥዎች የኢትዮጵያን ቡና የሚፈልጉት ከታህሳስ እስከ ሚያዚያ ባሉት ወራት መሆኑን ያስረዳሉ፤ዘንድሮ በእነዚህ ወራት የኢትዮጵያ ሰላም አስተማማኝ ስላልነበረ ገዥዎች ወደ ኬንያና ታንዛኒያ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሀገሮች መሄዳቸውን ያመለክታሉ፡፡ የሰላም ማስፈኑ ስራ ላይ በትኩረት እንዲሰራም ያስገነዝባሉ፡፡
የቡና ገበያው በዱሮው መንገድ መፈጸም ይኖርበታል፤ የቡና ግብይት ገዥዎች በሚፈልጉት አይነት እንጂ እኛ በምንፈልገው መንገድ መሆን የለበትም፤ ሲሉም ያመለክታሉ፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶ፣ ተመክሮበትና በባለሙያ ተመርምሮ ስልጠና እየተዘጋጀ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡
አቶ ሀይሌ፤ መንግስት በቡና ገበያ ላይ ያወጣቸውን ህጎች እንደገና ማየትና መከለስ ይኖርበታል፡፡ አሁን አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታት በሚል የወጡ የቡና ግብይት ህጎች ኢትዮጵያን ሊያጠፏትም ይችላሉ። ኢትዮጵያ ቡና ከውጭ አስመጥታ ቆልታ እንድትልክ የወጣ ህግ ሀገሪቱን የልዩ ቡና ባለቤትነቷን ሊያሳጣት ይችላል፡፡ ሲሉ ስጋታቸውንም ያመለክታሉ፡፡
አክለውም፤‹‹በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ የሌሉትንና ያሉትን በዘርፉ ታዋቂ የሆኑ ባለሙያዎችን በመሰብሰብና አማካሪ በማድረግ በሳል ህግ ማውጣት ይገባል፡፡ የሩጫ ህጎች ለአደጋ ያጋልጣሉ፤ የበሰለና ዘመን የሚሻገር ህግ ያስፈልጋል፡፡ ››ብለዋል፡፡
አቶ ሀይሌ ‹‹ንግድ ገጽታ ነው፤ የቡና ፍላጎት እየሞላ ከመጣ አዳዲስ ፍላጎት ያለበትን ማሰስ ያስፈልጋል፡፡ ጥናት በማድረግ ምን ያህል አቅም እንዳለን አዳዲስ ፍላጎት የት ይገኛል የሚሉና ሌሎችን በማጥናት ገበያ ማፈላለግ ያስፈልጋል፡፡››ይላሉ፡፡
የቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው በ2011 በጀት አመት 300 ሺ 420- ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡ በዘጠኝ ወራትም 195 ሺ 574 ቶን ቡና በመላክ 706 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ታቅዷል፡፡በእነዚህ ወራት 151 ሺ 211 ቶን ቡና በመላክ 498 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል፡፡አፈጻጸሙም በመጠን 77 በመቶ ሲሆን በገቢ ደግሞ 70ነጥብ 8 በመቶ ነው፡፡
ለአለም ገበያ የሚቀርብ የቡና ግብይት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንደመሆኑ መንግስት በዚህ ላይ በትኩረት መስራት ይኖርበታል፡፡ የውጭ ምንዛሬውን ላልተፈለገ አላማ የሚያውሉና ግብይቱን የሚረብሹ ህገወጦችን መስመር ማስያዝም ተገቢ ነው፡፡ የቡና ክምችትም ጎጂ እንዳይሆን በጥንቃቄ መመራት ይኖርበታል፡፡ ተጨማሪ የገበያ አማራጮችን መፈለግም ትኩረትን ይሻል፡፡ እነዚህን ማድረግ ከተቻለ ከቡናው ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል፤ በእነዚህ ላይ ካልተሰራ ግን እንደ ሀገር አደጋ ይከተላል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2011
በኃይሉ ሣህለድንግል