አዲስ አበባ:- በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን ከመፍረስና ከመጥፋት አደጋ የሚታደግ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ በቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ መንገሻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ጥንታዊ ቤቶቹ ለተለያየ አገልግሎት እየዋሉ አደጋ እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ቤቶች በደርግ ዘመነ መንግስት በአዋጅ 47/67 የተወረሱ በመሆናቸው በመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ሥር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ በዚህም የማፍረስ የማከራየትና የማደስ መብት እንዳለው ይታመናል፡፡ በቅርስነታቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይመለከታ ቸዋል፡፡ ችግሩን ለመከላከልም 440 ቤቶች በቅርስነት ስለመመዝገባቸው ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በዚህም ለእድሳት እንኳ ከቅርስ አንፃር ታይቶ ፈቃድ ማግኘት ቢገባም ይህ እየሆነ ግን አይደለም፡፡
እንደ አቶ ወርቁ ገለፃ ለሁለት ጊዜ የቅርስ ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን ከተመዘገቡት ቤቶች በላይ የታሪክ ዋጋ ያላቸው ቅርሶች ግን አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑ ይታያል፡፡ ከተመዘገቡት ውስጥም ሦስቱ የመፍረስ አደጋ አጋጥሟቸዋል፡፡ ችግሩም ከግንዛቤ እጥረትና ለግል ጥቅም ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡ ብዛት ያለው ቅርስ ምን ይሠራል? የሚል የተሳሳተ አመለካከት መኖሩንም የጠቆሙት አቶ ወርቁ እያንዳንዱ ቤት የተለያየ ታሪክ እንዳለውና የቁጥሩ ብዛትም የአገሪቱን የታሪክ ባለፀጋነት የሚያሳይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል፡፡ ቤቶቹ በቅርስነት ሲመዘገቡም አራት መመዘኛ መስፈርቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ከ50 ዓመት በላይ ማስቆጠሩ የቤቱ ጥንታዊ የኪነ-ሕንፃ ጥበብና ሥልጣኔን ማሳየቱ የተሠሩበት ግብዓት የቤቱ ባለቤትና ለአገሪቱ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለትውልድ ከሚያስተላልፉት ጠቀሜታ ጋር ተዳምሮ በቅርስነት ለመመዝገብ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህም ለጉብኝት እንዲበቁና ትምህርት እንዲሰጡ ይደረ ጋል፡ ፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ አካላት ጋር ለመሥራት ቢሞከርም ከአደጋ ግን ሊድኑ አለመቻላቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ አቶ ወርቁ ከዚህ ቀደም በ2010 ዓ.ም ቁጥር አንድና ሦስት የራስ አበበ አረጋይ ቤቶች መፍረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህም አንደኛው የሪል እስቴት ባለቤት በሆኑ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት ነው የፈረሱት፡፡ ቢሮው ቤቶቹ መፍረስ የለባቸውም በሚል ጉዳዩን በሕግ አስይዞታል፡፡
ሆኖም ጉዳዩ በሂደት ላይ እንዳለ በዘንድሮ 2011 ዓ.ም ከወር በፊት ደግሞ የራስ ካሣ ኃይሉ 92 ዓመት ያስቆጠረ የልጃቸው ልጅ ቤት የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር (ታርጋ) በሌለው ዶዘር ሲፈርስ ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ የቤቱ ግማሽ ክፍል ከፈረሰ በኋላ በመደረሱም ተጠግኖ ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ውሳኔ አርፏል፡፡ ከችግሮቹ በመነሳትም ሁለት አንኳር ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል አንዱ ሲሆን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ደግሞ ሌላኛው ነው፡፡ ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ሕጋዊ አሠራር እንዲኖር ማስቻል ላይ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የቤቶቹን ደህንነት የሚያረጋግጡ ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ለተለያየ አገልግሎት እየዋሉ የሚገኙትን ቤቶች ከቅርስ ጋር የተያያዘ ለተፈቀዱ አገልግሎቶች እንደሚውሉም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
ፍዮሪ ተወልደ