አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት አሰጣጥ ጥራት ባለው መልኩ ለማስኬድ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ለዘርፉ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆን እንቅፋት መፍጠሩ ተገለፀ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግንባታና የግዥ መጓተቶች እንዲሁም የውሃ እጥረቶች እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም፤ በቴክ ኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉ ውጤታማ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም ለዘርፉ የሚመደበው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለመቅዳትና ለማስፋፋት አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ባለው የበጀት ሁኔታ በተቻለ አቅም ጥራት ያለው ሰልጣኝ ለማፍራት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የግንባታ መጓተቶች በመኖራቸው በታሰበው ልክ እየተሰራ አይደለም፡፡ በየተቋማቱ የውሃ አቅርቦትን ለማዳረስ የተሰሩት ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም፡፡ በሌላ በኩል በየተቋማቱ የኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዱዋሳ አብዱላሂ፤ አገሪቱ ለያዘችው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ለዘርፉ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተቻለ አቅም ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲወጡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ጥራት ያለው ቴክኒክና ሙያ ሰልጣኝ ለማፍ ራት የአሰልጣኞች ብቃት ማደግ አለበት የሚሉት ዶክተር አብዱዋሳ፤ ከየተቋማቱ የሚወጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መፈተሽ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቶች ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚካሄዱና አዳዲስ የሚገነቡ ተቋማት ግንባታ መጓተቶች፣ የላቦራቶሪ እቃዎችና አጋዥ መጽሐፍት እጥረት የተፈጠረው በግዥ መጓተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በየተቋማቱ የሚታዩ የግዥ ክፍተቶች ለመ ፍታት መመሪዎች እየተዘጋጁ መሆኑን በመጥቀስ፤ የኦዲት ክፍተቶችን ለመቅረፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አመራር ማጠናከር፣ የህግ ክፍተቶችን መቅረፍና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቦርድ አመራር ውስጥ የዞን አስተዳዳሪ ወይም የከተማ ከንቲባ እንዲካተት መደረጉን የገለፁት ዶክተር ሳሙኤል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የዞን አመራሮች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታዎች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመ ራሮች አስተዳደራዊ ነፃነታቸው መከበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
መርድ ክፍሉ