አዲስ አበባ:- በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የሚሰጡት የብሄራዊ ፈተናዎች ዝግጅት በመልካም ሁኔታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለፀ። የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሄር በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የ10ኛ ክፍል (የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት) እና የ12ኛ ክፍል (የዩኒቨርሲቲ መግቢያ) ብሔራዊ ፈተናዎች ከግንቦት 21 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ፤ የስምንተኛ ክፍል ደግሞ ከሰኔ አምስት እስከ ስምንት ቀን 2011 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣሉ።
በዘንድሮው ፈተናም 1 ሚሊዮን 277ሺህ 573 የ10ኛ እና 322ሺህ 317 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ከነዚህ ውስጥ 860ሺህ 201 የ10ኛ እና 251ሺህ 91 የ12ኛ ክፍል መደበኛ ተፈታኞች፤ ቀሪዎቹ ደግሞ የግል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ እያንዳንዱ ተፈታኝም ከወዲሁ ሙሉ ዝግጅት እንዲያደርግና በየማህበራዊ ሚዲያው በሀሰት ተባዝተው በሚሰራጩ መልሶች እንዳይታለልና የጥቅም ፈላጊ አጭበርባሪዎች ሰለባ እንዳይሆንም አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ተማሪው ፍፁም በሆነ የራስ መተማመን ስሜት እንዲሰራ፤ ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ አስፈላጊውድጋፍ እንዲደረግለት አሳስበዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ከፈተናውና ተፈታኞች ጋር በተያያዘም ኩረጃን በህግ የተከለከለ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርግና «የፈተና ደንብ ጥሰት» እንዳይፈጸም ህግ ማክበር እንዳለበትም አሳስ በዋል፡፡
ማንም ሲኮርጅም ሆነ ሲያስኮርጅ የተገኘ ተፈታኝ በምንም አይነት መንገድ ከህግ ተጠያቂነት አያመልጥም፤ «ለዚህ ደግሞ ከቴክኖሎጂ ጀምሮ አስፈላጊው የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ዝግጅት ተጠናቋል» ሲሉም አስረድተዋል። ከግንቦት 21 እስከ 23፣ 2011 ዓ.ም ድረስ የሚሰጠው የ10ኛ ክፍልም ሆነ ከግንቦት 26 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ባሟላ ሁኔታ ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግባቸው የቆየ መሆኑን የገለፁት አቶ አርዓያ ፈተናው በጥሩ ሁኔታ እንደሚጠናቀቅም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
«ዝግጅቱ በዚህ አላበቃም፤ በአሁኑ ሰአት ‘የንቅናቄ ሰነድ’ አዘጋጅተን የጨረስን በመሆኑ ከክልሎች ፀጥታ ሀይሎች ጀምሮ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የጋራ ውይይትና ምክክር» ይካሄዳል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከዚሁ ጎን ለጎንም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ማለትም ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ ፈታኝ መምህራን፣ መም ህራን ማህበር፣ ርዕሰ መምህራን፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ዞኖችና ወረዳዎች ድረስ ያሉ የአስተዳደር አካላት፣ የፀጥታ ኃይሎችና መላው ህብረተሰብ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል። ለተፈታኞችና ለፈተናው ደህንነት ሲባልም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 2ሺህ 886 የፈተና ጣቢያዎች የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ከ82ሺህ 785 በላይ ባለሙያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011