አዲስ አበባ:- ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈ ለበትና ፋሺስት ድል የተደረገበት 78ኛው የድል በዓል በትናንትናው እለት አራት ኪሎ በሚገኘው በአራት ኪሎ አደባባይ በተከበረበት ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እንደገለፁት፣ ፋሽስት ኢጣሊያ ድል የተመታበትሚያዚያ 27 ለአገራችን ትልቅ ትርጉም ያለው ብቻ ሳይሆን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ክስተትም ነው፡፡ ይህ በኩራት የምናከብረው በዓል በአባቶ ቻችንና እናቶቻችን ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው ያሉት ክብርት ፕሬዚዳንቷ ድሉ ሉአላዊነታችንን ከማስከበሩም በላይ የቂም ቋጠሮን ሁሉ የፈታ ታላቅ ገድል መሆኑንም ገልፀዋል። እንደ ክብርት ሳህለ ወርቅ ገለፃ የፋሺስት ጦር እስከ አፍንጫው ድረስ ታጥቆ ቢመጣም ኢትዮጵያን መቆጣጠርና የኢትዮጵያውያንን የአገር ፍቅርና ወኔ ማንበርከክ አልቻለም፤ በተቃራኒው አባቶቻችንና እናቶቻችን እንዳያንሰራራ አድርገው የመቱት በመሆኑ አስፈላጊውን ትምህርት በመ ውሰድ ወደሰላማዊ መንገድ ለመመለስ ተገዷል።
እኛ ኢትዮጵያውያን አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ሉአላዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ የተረዳን ህዝቦች በመሆናችን በምንም አይነት መንገድና በምንም ዓይነት ሁኔታ አገራችንን ለድርድር አናቀርብም ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል። ልዩነት ቢኖረን እንኳን አገራችን ኢትዮጵያን የምናይበት መንገድ ምን ጊዜም አንድ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ይህ አሁንም ሆነ ወደፊት የማይናወጥ አቋም መሆኑንም አስገንዝበዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ የአባቶቻችን ጀግንነት አሁንም በከፍተኛ ደረጃ መደገም እንዳለበት የገለፁ ሲሆን፣ ይህም እንደነሱ ጦርነቱ ከፋሺስቶች ጦር ጋር ሳይሆን ከድህነት ከመውጣት፣ ከእርስ በእርስ ግጭትና ንትርክ ከመፅዳት፣ ፈጥኖ ከመልማትና ከመበልፀግ ጋር መሆኑንና ይህንንም ሁላችንምልብ ልንለው፤ በተለይም ወጣቱ ከልቡ ሊያስብበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በበኩላቸው እንደገለፁት፣ ይህ ሚያዚያ 27 የምናከብረው የድል ቀን አሁን ላለን ነፃነት ያበቃን ነው፤ በመሆኑም ታሪካዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበልን ልናከብረው ይገባናል፤ አሁን ያለውን ለውጥም ሁላችንም በህብረት፣ በአንድነት ሆነን ማስቀጠል ይጠበቅብናል፤ ይህን ለውጥ የሚቃወምና ለማኮላሸት የሚጥር ካለ በአባቶቻችን መስዋ እትነት እንደመቀለድ ነው የሚሆነው ሲሉም የተጀመረው ለውጥ መቆም እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የከተማው የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ይህ የምናከብረው በዓል የድል በዓል እንጂ የነፃነት በዓል አለመሆኑን አስታውሰው ይህም በልመና፣ እጅ በመንሳት፣ በመለማመጥና በማጎብደድ የመጣ ሳይሆን በከፍተኛ የእናትና አባቶቻችን መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን አስታውሰዋል፡ ፡
አርበኞቻችን ለአንድም ቀን እንኳን ለፋሺስት ጣሊያን እውቅና ሳይሰጡ እንደተናነቁ፤ ሚያዚያ 27 ባንዲራ ሲሰቅል ያን ለታውኑ ያስወረዱ ጀግኖች መሆናቸውን የገለፁት ተወካዩ አሁን ያለችን አገር የአርበኞቻችን ደም የፈሰሰባትና አጥንት የተከሰከሰበት መሆኗን አውቀን እርስ በርስ ከመጋጨት ይልቅ ልንንከባከባት፣ ልናለ ማትና በጋራ ልንጠቀምባት እንደሚገባም ገልፀዋል። የአባት አርበኛ የሆኑት የሀምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ በሰጡት አስተያየት ይህ በዓል ዝም ብሎ በዓል እንዳልሆነ ሁሉም ሰው በተለይም ወጣቱ ሊገነዘብ እንደሚገባና አሁን ያለው ጦርነት እንደ አባቶቻችን ከፋሺስቶች ጋር ሳይሆን ከድህነት፣ ኋላ ቀርነት፣ እርስ በርስ ግጭት እና ጥላቻ ጋር በመሆኑ ይህንኑ በማወቅና እነዚህን ከሀገራችን ለማስወገድ ስለሆነ ሁሉም በዚህ ላይ መረባረበ ይገባዋል በማለት አሳስበዋል።ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ይህ ዓይነቱ ታሪክና ታሪካዊ ቀን ልዩ ትኩረትን ሊያገኝ፣ ልዩ ቦታና ክብር ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በ78ኛው የድል በዓል ላይ የተለያዩ አገር ወታደራዊ አታሼዎች፣ አምባሳደሮች፣ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረ ገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ የተለያዩ የህብረ ተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ቡድኖች ልዩ ልዩ ትርኢቶችን በማሳየት፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርጎ በማውለብለብና በፌዴራል ፖሊስ ማርሽ በመታጀብ የኢትዮጵያን ህዝብ መዝሙር በመዘመር ተጠናቋል፡፡ ጣሊያን የአድዋን ድል ለመበቀል በ19 28ዓ.ም ኢትዮጵያን ብትወርም ጀግኖች አርበኞች ለአምስት ዓመታት ባደረጉት መራር ትግል በ1933 ዓ.ም ዳግም ሽንፈትን ተከናንባ ከኢትዮጵያ መውጣቷ የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
ግርማ መንግሥቴ