ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ለኢት ዮጵያ ከወደ ጀርመን የመጣ የብዙ ዎችን ልብ የሠበረ መርዶ ተስተጋባ፡፡ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሶለን ባጋጠማቸው የጤና እክል ሳቢያ ሕክምና ለማድረግ ካቀኑበት ጀርመን አገር ሕይወታቸው የማለፉ ዜና ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና በቅርብ ለሚያውቋቸው ብቻሳይሆን ብዙዎችን አስደንጋጭ ዱብ ዕዳ ነበር፡፡ አገራቸውን ለትውልዱ መፃዒ ተስፋ የምትመች ለማድረግና እንደምትሆንም ታላቅ ተስፋን ሰንቀው በዓላማቸው ፀንተው ሲሠሩ የቆዩት ዶክተር ነጋሶ የሚያምኗትን ኢትዮጵያን ትተው ዳግም ላይመለሱ አሸለቡ፡፡ ስርዓተ ቀብራቸው በተፈፀመበት በትናንት ናው ዕለትም ምንም እንኳ ለአገራቸው ቅን አሳቢ ዶክተር ነጋሶን ሊመልስና ያበረከቱትን ሁሉ ሊተካ የሚችል ተመጣጣኝ ድርጊት ባይገኝም ሕዝቡ ግን በነቂስ ወጥቶ ለመጨረሻ ጊዜ በእንባ ሸኝቷቸዋል፡፡
ጎህ ሲቀድ አስከሬናቸው ከነበረበት አያት ሆስፒታል ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሲያቀና የሰፈሩ ነዋሪዎች እጃቸውን ከአፋቸው ጭነው ከዓይናቸው የሚወርደውን መንታ የእንባ ዘለላ እያበሱ መቀበላቸውን ለተመለከተ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ሕይወታቸውም የተካኑ እንደሆነ ለመገመት አያዳግተውም፡፡ ከመኖሪያ ቤታቸው በማርሽ ባንድ ታጅቦ የቀብር ሥነሥርዓት ሽኝት መርሐ ግብር በሚካ ሄድበት የሚሌኒየም አዳራሽ ሲያቀናም፤ አስከሬኑ በሚያልፍበት መንገድ ሁሉ የፀጥታ ኃይሎች በልዩ ወታደራዊ ሥርዓት ሕዝቡም የመተላለፊያ መንገዶቹን ጥግ እየያዘ ያሳልፍ ነበር፡፡ በስፍ ራው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮ ንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል፡፡
ሃይማኖታዊሥነሥርዓቶችም የተካሄዱ ሲሆን የሕይወት ታሪካቸውም ተነቧል፡፡ ጳጉሜ ሦስት ቀን 1935 ዓ.ም በቀድሞ ወለጋ ክፍለ አገር ቄለም አውራጃ በሰዮ ወረዳ በደምቢዶሎ ከተማ ከአባታቸው ከቄስ ጊዳዳ ሶለን እና ከእናታቸው ወይዘሮ ዲንሴ ሾሊ ወደ ምድር እንደተቀላቀሉ የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ያትታል፡፡ አባታቸውም ዓይነስውርነታቸው በወቅቱ ከነበሩ ችግሮችና ከምንም ራዕያቸው ሳያግዳቸው በልቦናቸው ብሩህነት ታግዘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስ የሃይማኖት አባት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ነጋሶም በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በትምህርታቸው ውጤታማ የመሆናቸው ምስጢር አባታቸው እንደሆኑ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ዶክተር ነጋሶ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ደምቢዶሎ በሚገኘው በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የቤተል ትምህርት ቤት ገብተው አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ቢጀምሩም፤ ወላጅ አባታቸው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ወደ ሚዛን ተፈሪ በመዛወራቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚሁ ቦታ ቀጥለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቀድሞ መጠሪያው በናዝሬት በአሁኑ አዳማ ከተማ በሚገኘው የናዝሬት ባብል አካዳሚ አጠናቀ ዋል፡፡
በመቀጠልም በቀድሞ ስያሜው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ መጠሪያው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የተፈተኑትን ፈተና በአንደኝነት በማለፍ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በዚህም በ1963 ዓ.ም በታሪክ ትምህርት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ሰፍሯል፡፡ በዚህ መልኩ በትምህርታቸው በጥሩ ውጤት እያጠናቀቁ የጨረሱት ዶክተር ነጋሶ፤ ወደ ሥራ ዓለም በመሰማራት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ወለጋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የላ አደራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በመሆን እንዳገለገሉ በታሪካቸው ተገልጧል፡፡ በወቅቱም የቤተክርስቲያኒቱ ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ጉዲና ቱምሳ የነበራቸውን ዕምቅ አቅም በማየታቸው በቤተክርስቲያኒቱ በኩል ነፃ የትምህርት ዕድል ተመቻችቶላቸው ወደ ጀርመን አቅንተዋል፡ ፡
በዛም በፍራንክፈርት ኤም ማይን ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ሰብ ትምህርት በኤቲኖሎጂ ጥናት ዘርፍ እስከ ዶክትሬት (ፒኤችዲ) ድረስ ተምረዋል፡፡ የፖለቲካ ሕይወትም ገና በወጣትነት ዘመ ናቸው ‹‹ሀ›› ብሎ እንደጀመረ የሕይወት ታሪካቸው ያወሳል፡፡ በወቅቱ ይኖሩበት በነበረው ሚዛን ተፈሪ የነበሩ አስተዳዳሪዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች መጨቆናቸውና ኢፍትሃዊነት መን ገሱ ውስጣቸውን ሠላም የነሳቸው ዶክተር ነጋሶ፤ የተለያዩ ጥያቄዎች ይፈጥርባቸዋል፡፡ የመጀመሪያ ፖለቲካዊ ሕይወታቸውም በይፋ የተጀመረው በትውልድ ስፍራው ደምቢዶሎ ለእረፍት በሄዱበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ ለፓርላማ ምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩት ግለሰብ ለእስር በመዳረጋቸው ዶክተር ነጋሶ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን የ‹‹ይፈቱን›› ሠላማዊ ሰልፍ ይወጣሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ይኸው የፖለ ቲካ እንቅስቃሴያቸው ከፍ እያለ መሄዱ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ተነቧል፡፡ በተለይም በ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆንና ፊት ለፊት በመጋፈጥ የተጎጂዎችን ድምጽ ማሰማት ጀመሩ፡፡
በተለያዩ ወቅት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም እንቅስቃሴያቸው እያደገ ሲሄድ ለሕዝብ መታገል እንዲሁም መሞት ክብር እንደሆነ በማመን ለለውጥ በዕምነት ለመታገል መነሳታቸውን ይገልጹ ነበር፡፡ በዚህም ለትምህርት ወደ ጀርመን ባቀኑበት ወቅት ሳይቀር በተለያዩ አደረጃጀቶችና ንቅናቄዎች በመሳተፍ ታግለዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋው ባህሉና ወጉ ተጠብቆ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነትና በእኩልነት እንዲኖር ከፍተኛ ትግል አድርገዋል፡፡ ጥናትና ምርምሮችን አድርገዋል፤ መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ዶክተር ነጋሶ በ1983 ዓ.ም በአገሪቱ በነበረው የስርዓት ለውጥ ሕዝባቸውን ለማገልገል የቅንጦት ሕይወታቸው ሳያሳሳቸው ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው በሕይወት ታሪካቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አጽዳቂ ጉባዔ አመራር፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ እንዲሁም በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በተለያዩ ሕዝባዊና መንግሥታ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል፡፡ ከሕገመንግሥቱ መጽደቅ በኋላም የኢፌዴሪ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት በመሆን ለሰባት ዓመታት ሕዝባቸውንና አገራቸውን በትጋት፣በሀቀኝነትና በታማኝነት ማገልገላቸውም እንዲሁ ተገልጿል፡፡ በቆይታቸውም ሲሳተፉበት የነበረው ፓርቲ ከአቋማቸው ጋር ተጣጥሞ ባላገኙት ወቅትም ልዩነታቸውን በግልጽ በማስቀመጥ በቆራጥነትና በመርህ የቤተመንግስት ኑሮ ሳያጓጓቸው ብሎም ቀጥሎ ሊፈጠርባቸው የሚችለውን ችግር ለመጋፈጥ ወስነው በመውጣት በሌላ መልኩ ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡
ከዚያም በ1997 ዓ.ም በተወለዱበት ደምቢዶሎ ከተማ በግል በመወዳደር አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመግባት ለአምስት ዓመታት አገልግ ለዋል፡፡ በመቀጠልም የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ በተሰኘው ተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ በመደራጀት ያላቸውን የፖለቲካ ዕምነት ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ዶክተር ነጋሶ አንድነት ከመነጣጠል በተሻለ እንደሚጠቅም ከመስበክ ባለፈ ለኢትዮጵያ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋቸውን በተለያዩ መድረኮችም ያንፀባርቁ ነበር፡፡ በዓላማ ጽናታቸውም ከፕሬዚዳንትነታቸው ከለቀቁ በኋላ ብዙ ችግሮች እንዳሳለፉም በሕይወት ታሪካቸው ተዳሷል፡፡ የግል ቤትም ሆነ ተሽከርካሪ ያልነበራቸው በመሆኑም ጣሪያው በሚያፈስ ቤትና በእግራቸው ተጉዘው ከሕዝብም ጋር ተሰልፈው መጓጓዛቸው ለግል ጥቅማቸው ያልተንበረከኩ መሆናቸውን ዓይነተኛ ማሳያም ይሆናል፡፡ በቅርቡም ኦዴፓ በወሰደው እርምጃ ክፍያ በመፈጸም እንዲሁም የሕክምና ወጪዎችን ሸፍኖላቸዋል፡፡
ዶክተር ነጋሶ ከ50 ዓመታት በላይ በዘለቀው የፖለቲካ ሕይወታቸው ላመኑበት ዓላማ ባለማወላወል ፀንተው የቆሙ በሀቀኝነትና ያለአድልዎ አገራቸውን ያገለገሉ ምስጉን እንደነበሩም ታሪካቸው አውስቷል፡ ፡ዶክተር ነጋሶ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የተለያዩ መሰናክሎችን አልፈው ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለማድረግ የበቁ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ፡፡ ባለትዳር፣ የአንድ ወንድና የሁለት ሴት ልጆችም አባት እንደነበሩም በሕይወት ታሪካቸው ተዳሷል፡፡ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በሽኝቱ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1983 ዓ.ም ከዶክተር ነጋሶ ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰዋል:: አንጋፋ ፖለቲከኛና የታሪክ ሰው ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል፡፡ ከግል ጥቅም ይልቅ ለሕዝብ መኖርን ያስተማሩና አገራቸውን በታማኝነት ብቻ ሳይሆን ምሳሌ ሆነው ማለፋቸውንም አውስተዋል፡፡ በቀጣይም የእርሳቸውን ተምሳሌትነት በመከተል ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የትዳር አጋራቸው ረሬጊና አበልትና ልጃቸው አቶ ኢብሳ ነጋሶ በተመሳሳይ ይህንኑ ሃሳብ በመጋራት ትውልዱ ከእርሳቸው ሊማራቸው የሚገባ በርካታ ቁምነገሮች እንዳሉ ምንም እንኳ ‹‹ስሞት እንዳታለቅሱ›› ቢሉም እንባ እየተናነቃቸው ገልፀዋል፡፡ ዶክተር ነጋሱ በምድር የነበራቸው ቆይታ ቢያበቃም መርሐቸው ግን ሕያው ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት፡፡ በቅርብ የሚያውቁቸው ወዳጃቸውና አብሮ አደጋቸው አቶ ሌንጮ ለታ፤ ባደረጉት ንግግር ለሕዝብ ራሳቸውን የሰጡ ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡ ፡ በወጣትነት ዘመናቸውም ብዙዎችን በፍቅር የማንበርከክ ኃይል እንደነበራቸው በማስታወስ፤ በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ሕይወታቸው መልካም ግንኙነትን መፍጠር የሚችሉ የአቋም ሰው እንደነበሩ የኋሊት አስታውሰው ዘክረዋል፡ ፡
በመሆኑም ከኀዘን ይልቅ ሠርተው ያለፉትን ተግባር በማሰብ ደስ መሰኘት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ሌንጮ፤ ጠመዝማዛው የነጋሶ መንገድ አበቃ ሲሉም አክለዋል። ሌላኛው ያነጋገርናቸው የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ዲሌቦ፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ዶክተር ነጋሶን እንደሚያውቋቸው ተናግረዋል፡፡ ትልቅና መንፈሳዊ ደፋርም ናቸው፡፡ ለሰው ልጆች አንድነት እኩልነት እንዲሁም ለእውነት የቆሙ መሆናቸው የታላቅነታቸው ማረጋገጫ እንደ ሚሆኑም ነው የተናገሩት፡፡ በዚህ ዘመን ያለው ትውልድም ኢትዮጵያዊነትና ለአንድነት ለአገር ልማት መተባበር እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከሚሊኒየም አዳራሽ ወደ አስከሬን ማረፊያው መካነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብርም አምርቷል። በስፍራውም የሃይ ማኖት አባቶች ዕውቅ ሰዎች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አባቶች ሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ተካሂዷል፡፡ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው የአበባ ጉንጉኖችን አኑረዋል፡ ፡ ዶክተር ነጋሶ በምድር የነበራቸውን ቆይታ ጨርሰው ቢያርፉም በአገሪቱ የነበራቸው ብሩህ የመፃዒ ዕድል ተስፋ ግን ሕያው ሆኖ ለዘላለም እንዲኖር ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ መልዕክቶች በስፍራው ካሉ የ ሃይማኖት አባቶች ተላልፏል፡፡ በመጨ ረሻም ስንብት ከተደረገ በኋላ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶ ግብዓተ መሬታቸው ተፈፅሟል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2011
ፍዮሪ ተወልደ