ሀገር የምትፀናው በምክንያት በሚመራ ትውልድ አብሮነትና ፍቅር፤ አንድነትን በሚያጠናክረው በበጎ አስተሳሰብ በተቀረፀ ዜጋ ነው።ጉዳዮችን ከስሜት ይልቅ በስሌት መርምሮ እውነታውን በማረጋገጥ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ ከስህተት ያድናል።
ከጥቂት ወራት በፊት በደሴ ከተማ የተከሰተ ነው።አንዲት ታዳጊ ሕፃን ተገድላ ትገኛለች።የሟቿ እናት «ልጄን የገደለው የእንጀራ አባቷ (ባለቤቴ) ነው» ብላ በፖሊስ ታስይዛለች። የአካባቢው ነዋሪ ወንጀሉን የፈፀመው ግለሰብ በፍርድ ቤት ተጣርቶ የሚወሰንበትን ቅጣት ከመጠበቅ ይልቅ «ወንጀለኛውን አቅርቡልን ዕርምጃ እኛው እንውሰድ!» በማለት በፖሊስ እጅ ያለውን ተጠርጣሪ አሳለፈው እንዲሰጡ አደባባይ ወጥቶ ይጠይቃል። ፖሊስም ለተሰበሰበው ህዝብ ጉዳዩ በህግ እንደሚታይ ገልጾና ህዝቡን አረጋግቶ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ያደርጋል።
የምርመራው ውጤት ሲጠናቀቅ የወንጀሉ ፈፃሚ የተጠረጠረው ግለሰብ ሳይሆን የልጅቷ እናት ሆና ተገኘች።ወንጀሉ ተፈጸመ በተባለበት ወቅት ፖሊስ ተጠርጣሪውን ይዞ ከለላ ሳያደርግ ህዝቡ ቢያገኘው ኖሮ በግለሰብ ላይ ምን አይነት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልና ውጤቱም አሳዛኝ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።
ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜትን ማስቀደም ሊተመን የማይችል ጥፋትና ሊነገር የሚከብድ ውድመት ያስከትላል።ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ጉዳዮችን በጥልቀት ከመመርመር ይልቅ የሰማውን ሳያጣራ ለሌላው የማስተላለፍና ምክንያት አልባነቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፍቅርተ ማሞ በሰዲል ኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሥነ ልቦና ባለሙያ ናቸው።ዛሬ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚታየው ተገቢ ያልሆኑ ስህተቶች ወጣቱ ትውልድ የደረሰበትን ጉዳዮች ሳይመረምሩ መወሰኑና ከምክንያት መራቁ ማሳያ እንደሆነ ይጠቁማሉ።ጠዋት ላይ አንድ ጉዳይ ተነስቶ መልካምነት ይወራል።ሁሉም ተቀባብሎ የጉዳዩን ቅዱስነት ካንዱ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያደርሳል።ከሰዓት ላይ ይሄው ቅዱስ የተባለው ጉዳይ ወይም ግለሰብ ይረክሳል፤ይንቋሸሻል፣ይብጠለጠላል።ይህ በአንድ ዕለት የተፈጠረ የአንድን ጉዳይ ወይም ሰው ማወደስና ማንኳሰስ መነሻው ምክንያት አልባ የመሆኑ ማሳያ ነው።ስለሁኔታው ሳያውቁና በቂ ግንዛቤ ሳይኖር በ‹‹አሉባልታ›› መመራት ውጤቱ አስከፊ መሆኑን ይናገራሉ።
ወጣቶች ለሚያነሱት ሃሳብ ተገቢነት እርግጠኛ መሆን አለባቸው የሚሉት ወይዘሮ ፍቅርተ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስ ፈልጋቸውን ነገር መርጠውና ለይተው አለማቅረባቸው፣ በራስ መተማመን ላይ አለመስ ራታቸው፣ ጉዳዮችን በምክንያት እንዲቀበሉ ካልሆነም ያጡበትን ምክንያት እንዲያውቁ አለማድረጋቸው የወለደው ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።
ትውልድን ለማነፅና በጎ አመለካከቱን ለማስረፅ ወላጆች፣ትምህርት ቤቶችና መገናኛ ብዙኃን በኃላፊነት ስሜት ሊሠሩ እንደሚገባ ወይዘሮ ፍቅርተ ያስረዳሉ።ትውልዱ ሀገራዊ ስሜት በማላበስ ሀገሩን እንዲወድና ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።
የላይፍ ኤንድ ፒስ ኢንስቲትዩት የስነ ልቦና ባለሙያ አቶ ፍሬው ከፍያለው እንዳሉት አንድን የተደገፈ ጉዳይ በአጭር ጊዜ አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት ማጥላላት ለነገሮች ያለንን እይታ በትክክል ካለመገንዘብ የመነጨ መሆኑን ያስረዳሉ።ትውልድን ማነፅና ለበጎ ተግባር ማስተማር ምክንያታዊ ትውልድ ለማፍራት ወሳኙ መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ አህመድ ሙሀመድ ወጣቶች ከምክንያት ርቀው ጉዳዮችን በስሜት መመራታቸው የፈጠጠ እውነት መሆኑን ያስረዳል።አንድ ግለሰብ ከቤተሰቡ ከማህበረሰቡ ሰፍቶም ከሀገሩ የሚያገኘው ብዙ ነገር ቢኖርም በራሱ አመክንዮ ህይወትን የመረዳት አቅሙና ለነገሮች ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ከጅምላ የወጣ ሳይሆን ከግለሰቡ ሰብዕና የመነጨ መሆኑን ያስረዳል።
«የማህበረሰባችን ሰብዕና እንዲስተካከል አስቀድሞ የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብዕና መታነፅ ይገባዋል።» በማለት ሃሳቡን የሚያጠናክረው ጋዜጠኛ አህመድ፣ በምክንያት የሚያምን ዜጋ ለመፍጠርና አሁን የሚታየውን ችግር ለመቀነስ የሁሉም ማህበረሰብ ድርሻ የጎላ መሆኑን ይናገራል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ተገኝ ብሩ