አዲስ አበባ፡– አሁን በሥራ
ላይ ያለውን የጋራ
ገቢ ክፍፍል ሂደት
ግልፅ ማድረግ በክልሎችና
በፌዴራል መካከል ያለውን
ግንኙነት የሚያጠናክርና ለአንድነት
ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
።
የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ትናንት በሂልተን ሆቴል የጋራ ገቢ ክፍፍል ማሻሻያ ረቂቅ ቀመርን በተመለከተ ባካሄደው አውደ ጥናት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የረቂቅ አዋጁ ጥናት አማካሪ ዶክተር ሲሳይ ረጋሳ እንዳሉት፤ የጋራ ገቢና የበጀት ድጋፍ የመሳሰሉ የሀብት ፍሰቶችን በግልጸኝነትና በፍትሃዊነት ማሰራጨት ተባብሮና ተማምኖ ለመኖር ያስችላል።እንዲሁም የፌዴራል ሥርዓቱንም ከማጠናከር አንፃር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።አንዱ ክልል የተጎጅነት ስሜት የሚሰማውና ጥርጣሬ የሚያድርበት ከሆነ የግጭት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል የብዙ አፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዶክተር ሲሳይ ረጋሳ ገለፃ፤ በገቢ ክፍፍል ረገድ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ለሁሉም ባለድርሻ አካላትና ለህዝብ በሚገባ መልኩ በትምህርት ቤቶች ጭምር ማሳወቅ ተገቢ ነው።በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔርና የህዝብ ቁጥር ባለበት ሀገር የገቢ ክፍፍሉን በጥንቃቄና ግልፀኝነት በተሞላበት መልኩ መከፋፈል እንዳለበት አስታውቀዋል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የገቢ ክፍፍል መመሪያ ከፍተኛ ክፍተት የሚታይበት በመሆኑ የገቢ ክፍፍል መንገዱን በማሻሻል ያሉ ችግሮችን መቅረፍና በክልሎች መካከል፣ በክልሎችና በፌዴራል መካከል ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ እንዳሉት፤ የጋራ ገቢ ቀመር ሲወጣ በወቅቱ ያለውን ጊዜ ብቻ ያገናዘበ ነበር። በሂደት ግን በርካታ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች እየተስተዋሉ መጥተዋል።በተለይ ደግሞ ክልሎች በተለያየ ጊዜያት በቀመሩና በአስተዳደሩ ዙሪያ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።እንዲሁም የጥናት ተቋማት በሥራ ላይ ያለውን የገቢ ክፍፍል ቀመር በጥናታቸው ችግር እንዳለበት ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በክልሎች መካከል ያለውን የገቢ ክፍፍል ሂደትን አስተማማኝ ለማድረግና አለመተማመንን ለመቅረፍ በሥራ ላይ ያለው የገቢ ክፍፍል ቀመሩ መሻሻል አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ