አዲስ አበባ፡- በሕክምና ባለሙያዎች የተነሳው ቅሬታ በባለሙያዎቹና በመንግሥት መካከል ተግባቦት ባለመኖሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።በጤናው ዘርፍ ላይ የሚታየውን ተግዳሮት ለመቅረፍ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰሞኑን ከሕክምና ባለሙያዎች ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመላው አገሪቱ ከተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ውይይት በባለሙያዎችና በመንግሥት መካከል የተግባቦት ችግር እንዳለ ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ ላይ የሚታየውን ተግዳሮት ለመቅረፍ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፈው አንድ ዓመት የተተገበሩ የተቋማት ማሻሻያ ሥራዎች መረሳት እንደሌለባቸዉ አስገንዝበዋል::
በዘርፉ ከተሰሩት ስራዎች መካከልም የሕክምና ቱሪዝምን ለማበረታታት ስድስት የተለያዩ ተቋማትን የማደራጀት ሥራ መሰራቱንና ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል።
የመንግሥትና የግል ሽርክናን በማሳለጥ ስድስት የሕክምና አምራች ኢንዱስትሪዎች ተሰናድተዋል፤ 120 ሚሊዮን ዶላር ለመድሃኒት መግዣያ መመደቡንና ወደ 4ሺ200 የሚሆኑ መኖሪያዎች በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ በ340 የጤና ተቋማት ውስጥ መገንባታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ አገሪቱ የ20 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ነበረባት፤ ከ12 እስከ 13 ዓመታት ያልተከፈለ ዕዳ አለባት። በመሆኑም መንግሥት የአገሪቱን ስብራት የማስተካከል ሥራ ላይ ስለነበር ባለሙያዎቹ ይህን ችግር አለመረዳታቸውን አንስተዋል።
“ባለሙያዎች መንግሥት የሕክምናው ዘርፍ ላይ የሰራውን ሥራ ማወቅ አለባቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጨረታ የሚገዛ የሕክምና ዕቃ ብዙ ወራት ይወስድ የነበረው ወደ 15 ቀን ዝቅ መደረጉን ተናግረዋል። 30 ቢሊዮን ብር የነበረው የሕክምና በጀት ወደ 130 ቢሊዮን ብር ከፍ ተደርጓል። እንዲሁም ከወጪ መጋራት በተጨማሪ ይከፍሉት የነበረው 500 ሺ ብር ሙሉ በሙሉ መነሳቱን አስታውቀዋል።
እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ክፍያ ታክስ ስለማይሆን መንግሥት በዓመት 70 ሚሊዮን ብር እንደሚያጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሁለት ቦታ መሥራትን አስመልክቶ ከተሳታፊዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ልምድ ያላቸውን ሐኪሞችን ማስቀረትም ስለማይቻል ሁለት ቦታ መሥራት እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለሕክምናው ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ያሉት ተሳታፊዎች ባለሥልጣናት ሲታመሙ ውጭ አገር ሄደው መታከማቸውን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል። “የአገሪቱን ሕክምና ስለማይተማመኑበት ነው ውጭ አገር የሚሄዱት” ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም በቀጣይ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና ተቋም ይገነባል። የጤና ፖሊሲውም ይሻሻላል፤ እስካሁን በተላላፊ በሽታዎች ላይ የነበረው ፖሊሲ ተሻሽሎ የማይተላለፉ በሽታዎችንም እንደሚያካትት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባለሙያዎቹ ባስተ ላለፉት መልዕክትም ሕክምና የተለየ ሙያ ነው። በኩርፊያና በቁጣ የሚሰራ አይደለም። በቀጣይ እንደ ወታደር ሕክምና የጀግና ማዕረግ እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል። ይሁን እንጂ የዚህ ክቡር ሙያ ባለቤቶች በአክቲቪስት እንዳይጠለፉና የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳትሆኑ ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ