አዲስ አበባ፡- ወጣቱ ከአርበኞች ድል አኩሪ ታሪክ በመማር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በመምረጥና በማስቀደም ለሀገራችን ልማትና ዕድገት አንድ ሆኖ መስራት እንዳለበት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አሳሰበ።ዛሬ 78ኛው የአርበኞች የድል በዓል እየተከበረ ነው።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የፋሽስት ጦር የጣሊያንን ህዝብ በማነቃነቅ ሀገራችንን ዳግም ለመውረር ሲመጣ አያት ቅድመ አያቶቻችን በዘር፣በቋንቋ እና በሃይማኖት ሳይለያዩ አምስት ዓመት በዱር በገደል ተዋግተው ሀገራችን ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ማድረግ ችለዋል።
ወጣቱም ከዚህ አኩሪ ታሪክ በመማር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በመምረጥና በማስቀደም ለሀገራችን ልማትና ዕድገት ልክ እንደ ቅድመ አያቶቻችን ሁሉ አንድ ሆነው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል ።ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ ጠላቶቿን በመመከት ዳር ድንበሯን፣ ክብርና ነፃነቷን፣ ባህሏንና እሴቶቿን በሙሉ አስጠብቃ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
የአርበኞች ድል በዓል በየዓመቱ የሚከበረው ሚያዝያ 27 መሆኑን የተናገሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት የደርግ የፖለቲካ አስተሳሰብ ኮሚኒስት ስለነበር ከንጉሱና ከምዕራባውያኑ ጋር የተያያዘውን ታሪክ በሙሉ ለመደምሰስ በማሰብ አርበኞች የገቡበትን ቀን መጋቢት 28 ይከበር እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል።አሁን ሚያዝያ 27 የአርበኞች በዓል ተብሎ የሚከበረው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ሀገራቸው ገብተው ሰንደቅ አላማችንን የሰቀሉበትና ሀገርም የተረጋጋበት ቀን በመሆኑ ነው ብለዋል።
የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የሥራ አመራር ምክር ቤት አባል አባት አርበኛ ሻምበል ዋኘው አባይ ኃይለማርያም ፤ እንዳሉት ጣሊያን በመሳሪያ ደርጅቶ የዓለም ህግን ጥሶ ይፋዊ ጦርነት አካሂዷል።የኢትዮጵያ ህዝብ አልገዛም በማለት ድፍን አምስት ዓመት በጦር፣ በጎራዴ፣በድንጋይና በዱላ በከፍተኛ ወኔ በመዋጋት የፋሽስት ወራሪን ዳግም ድል ማድረግ ችለዋል።ይህም ሁኔታ ለነጮች ሀፍረትን ያከናነበና የሽንፈትን ጽዋ የጠጡበት ሲሆን ለመላው የጥቁር ህዝቦች ደግሞ የዳግም ድል ሸማ ያጠለቁበት ቀን ነው።
«ወጣቱ ታሪክን ከመንከባከብ አንፃር ትልቅ ኃላፊነት አለበት» ያሉት አባት አርበኛ ሻምበል ዋኘው ሆኖም ግን መንግሥት ወጣቱን በሚገባው መልኩ ስለ ታሪኩ እንዲያውቅ እያስተማረው አይደለም ብለዋል።
የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የሥራ አመራር ምክር ቤት አባል አባት አርበኛ ዳኛቸው ተመስጌን፤ በበኩላቸው አርበኝነት በተሰራ ጀብዱ ላይ የሚከበር ድል ነው።ስለዚህ መንግሥት ለፖለቲካው ትኩረት እንደሚሰጠው ሁሉ ለሀገር ታሪክ፣ ሉአላዊነትና አንድነት በስፋት በማሳወቅ በትምህርት ፖሊስ በማካተት ጭምር ወጣቱን ማስተማር እንዳለበት ተናግረዋል። መንግሥት ወጣቱን ስለ ታሪኩ ሳይነግርና ሳያስተምር አዲሱን ትውልድ ተወቃሽ ማድረግ የለበትም ብለዋል ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ሞገስ ፀጋዬ