ነገ ብሄራዊ የኀዘን ቀን ሆኖ ይውላል
. ዛሬ የቀብራቸው ስነስርዓት ይፈፀማል
አዲስ አበባ:- የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ስለእውነት በሀገር ወዳድነት የሰሩ፣ ሀቀኛ እንዲሁም ለግል ጥቅማቸው የማይሮጡ እና ሰው አክባሪ እንደነበሩ የቅርብ ጓደኞቻቸው፣ የስራ ባልደረቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ገለጹ። የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ የሚፈጸም ሲሆን ነገ ደግሞ ብሄራዊ የኀዘን ቀን ሆኖ እንዲውል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አውጇል።
በኦሮሚያ ክልላዊ ብሄራዊ መንግስት የኦሮሚያ ህንጻዎች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ ጫንያለው እንደገለጹት፤ ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአምስት አመታት አብረው ሰርተዋል። በዚሁ ጊዜ የሚያውቋቸው ሰውን ሰብአዊ ፍጡር ስለሆነ ብቻ በሰውነቱ ሁሉንም በእኩል አይን የሚያዩ እንዲሁም ሀገር ወዳድና ለወገን ተቆርቋሪ መሆናቸውን ታዝበዋል። እንዲሁም የተሰጣቸውን የስራ ኃላፊነት በቆራጥነትና በታማኝነት የሚወጡ፣ ፈሪአ እግዚአብሄር ያደረባቸው፣ ሰው መካሪና አስተማሪም እንደነበሩ መስክረዋል።
በእርሳቸው ህልፈተ ህይወት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጹት አቶ አለሙ፤ ለትውልድና ለህዝብ የማስተላልፋቸውና የማካፍላቸው ስራዎች አሉኝ እያሉ ያጫውቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል። እነዚህን ስራዎቻቸውን ለትውልድ ሳያስተላልፉ በድንገት ለህክምና በሄዱበት ህይወታቸው ማለፉ አሳዝኗቸዋል። ኢትዮጵያም ትልቅ ምሁር፣ የሀገር ባለውለታና አለኝታ የሆኑ ሰው በማጣቷ ኀዘኑ ድርብ ድርብርብ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን የማውቃቸው ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ታጋዮች ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቱፋ ቶላ ፤ ዶክተር ነጋሶ በጣም የዋህ፣ ቅን፣ ላመኑበት ወደ ኋላ የማይሉ፣ ለክብራቸውና ለስልጣናቸው የማይጨነቁ እንዲሁም ለህዝብ ክብርና ጥቅም ብቻ የሚጨነቁ ሰው እንደነበሩ ገልጸዋል።
ከፕሬዚዳንትነት በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣ ናቸውን የለቀቁት ህግ መንግስቱ በተለይም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በዋናነት ሲንቀሳቀሱ በወቅቱ ተቀባይነት በማጣታቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ የሚታየው የለውጥ ጭላንጭል እንዲመጣም ሲታገሉ የነበሩ ሰው
መሆናቸውን መስክረዋል ።
የኦሮሚያ ህንጻ ስራዎች አስተዳደር የኦፕሬሽን ሲስተምና ቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ በበኩላቸው ከ1985 ዓ.ም እስከ ህልፈተ ህይወታቸው በተለያዩ ጉዳዮች መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መንገድ ይገናኙ እንደነበር ገልጸው፤ አቶ አሰፋ እንዳሉት፤ ዶክተር ነጋሶ ለህዝብ ጥቅም ሲሉ እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ከሙስና እራስን አጽድቶ መኖር እንደሚቻል ያሳዩ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህንንም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተግባር አሳይተዋል።
የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ትንሽ ወንድም አቶ ኤልሲኢ ጊዳዳ እንደተናገሩት፤ ዶክተር ነጋሶ ወንድሞቹንና እህቶቹን ወዳጅ ቤተሰብ አክባሪና ታዛዥ ነበሩ። በቤተሰቡ ውስጥም ሲያድጉ ከልጆች መካከል በእናትና
በአባታቸው በጣም ተወዳጅ ልጅ ነበሩ። አዋቂ ሆነውም ወደ ኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ አገር ወዳድ ናቸው። በዚች አገር ውስጥ እውነተኛ ሰላም፣ ፍትህና ዲሞክራሲ እንዲኖር የታገሉ ናቸው። በአጠቃላይ በማንኛውም ነገር ላይ ሁሉም ሰው እኩል መብት እንዲኖረውና ተጠቃሚ እንዲሆን ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
የዶክተር ነጋሶ ትልቅ እህታቸው ሲስተር ፅሀይቱ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ ለእርሳቸው እንደ ታላቅ እህት ያከብሯቸውና ይታዘዟቸው እንደነበር ይናገራሉ። “ስናድግ ትምህርት ቤት ስንሄድ ስንመጣ አብረን ነበር። ከትምህርት መልስም እድሜያችን ተቀራራቢ ስለሆነ ከሌሎች እህት ወንድሞቻችን በተለየ አብረን እንጫወት ነበር። እርሳቸውም ከቤተሰባችን በጣም ሰውን አክባሪና ወዳጅ ነበሩ። ቤተሰብም ሆነ ማንኛውም ሰው እንዲለወጥ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ፤ ቤተሰቡ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ከሶስት ወር አንድ ጊዜ ቤተሰቡ እየተገናኘ እንወያያለን። በውይይቱም ልጆች እንዲማሩና ጥሩ ደረጃ እንዲደርሱ ሁሌም በምክር ባላቸው አቅምም ድጋፍ እያደረጉ ነበር። በምንገናኝበትም ጊዜ ሰው በሰውነቱ እኩል እንደሆነ ሁሌም ሳያስተምሩ አልፈው አያውቁም ። በተጨማሪም ከቤተዘመድም ውጪ ማንኛውንም የተቸገረ ሰውና ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችን ካላቸው አካፍለው የሚሰጡ ሰው ነበሩ” ብለዋል።
በተያያዘ ዜናም የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ቀን ብሄራዊ የሃዘን ቀን እንዲሆን አውጇል። በዚሁ መሰረት ብሄራዊ የሀዘን ቀን ሆኖ የሚውለው ነገ ሚያዝያ 28/2011 መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታደሰ ጫፎ አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት የሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ ሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2011 በመላው የአገሪቱ ግዛቶች፣ በኢትዮጵያ መርከቦች እና በውጭ ሀገር በሚገኙ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ዝቅ ብሎ የሚውለበለብ ይሆናል።
የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስከሬን ከነበረበት ጀርመን ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል። በዕለቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለአስከሬኑ አቀባበል አድርገዋል።
በዛሬው እለትም በሚሌኒየም አዳራሽ የአስከሬናቸው የሽኝት ስነ ስርዓት የሚከናወን ሲሆን፤ ከሰዓት በኋላም የቀብር ስነ ስርዓታቸው የሚፈጸም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም
ሶሎሞን በየነ