አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ካለው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ችግሮች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸው ተገለጸ።
ዓለም አቀፉን የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀንን አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በብሉስካይ ሆቴል በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለጸው፤ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ካለው የኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት ችግሮች እየጨመሩ መጥተዋል። በሀገሪቱ ከሚገኘው አጠቃላይ የንብረት መጠን 4ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው በሥራ ደህንነት እጦት ሳቢያ የሚወድም ነው።
በዕለቱ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል አሰ ሪዎች ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ሞገስ ዳዊት እንደተናገሩት፤ ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል በአሰሪዎች በኩል የቅድመ ግንዛቤ ሥራዎች ሊካሄዱ ይገባል።
እስካሁን ባለው ተሞክሮ በርካታ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ኢንሹራንስ የመግባት ልምድን ያዳበሩ ናቸው። ይህ ብቻ መሆኑ ደግሞ የሥራ ጊዜ ያለአግባብ እንዲባክን፣ምርትና ምርታማነት እንዲቀዛቀዝና ንብረትና ዕውቀት እንዲበዘበዝ ምክንያት ይሆናል።
እንዲህ ዓይነቱን የሙያ ደህንነትና ጤንነት ችግሮች ፈር ለማስያዝ አሰሪ ኮንፌዴሬሽኖች ለሠራተኞቻቸው ግንዛቤ ሊሰጡና የሥራ ቦታዎችን ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ዳዊት ገልፀው፤ በሀገሪቱ በየዓመቱ ከ100ሺ ሠራተኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ለሙያ ደህንነት ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት መንግሥት ችግሩን በ35 በመቶ ለመቀነስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቡድን መሪ አቶ መስፍን ኃይሌ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ጊዜ በፌዴራልና በክልል ከተሞች በሙያ ጤንነትና ተቆጣጣሪዎች የሚካሄድ አገልግሎት በአግባቡ መደራጀቱን አስታውቀዋል።
በዚህ ሂደት 12 የግሉ ዘርፍ የሙያ ደህንነትና አማካሪዎች በተሳትፎ እየሰሩ እንደሚገኝና 4ሺ373 በድርጅት ደረጃ የተቋቋሙ የሙያ ደህንነት ኮሚቴዎች በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥም በየዓመቱም በአማካይ 40ሺ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በየዓመቱ ሚያዚያ 25 ቀን ዓለምአቀፉ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቀን ዘንድሮ በዓለም 15ኛ ጊዜ በኢትዮጵያን ደግሞ 14ተኛ ጊዜ «የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅና የነገው የሥራ ዕድል» በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በመልካምሥራ አፈ ወርቅ