አዲስ አበባ፡- የቀድሞ አርበኞች ለአገሪቱ አንድነት ሲሉ የፈፀሟቸውን ታሪካዊ ገድሎችና የጀግንነት ተጋድሎዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋልና ትውልዱ እንዲማርባቸው ማድረግ ይገባል ተባለ።
78ኛው አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ‹‹እኔ ለሀገሬ›› በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የስብሰባ አዳራሽ በተዘጋጀ ሲፖዚየም ላይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ልጅ ዳንዔል ጆቴ እንዳሉት፤ አርበኞች ወራሪ ጣሊያን ለመመከት 1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ ባደረጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያን ከጠላት ነፃ አድርገው ደማቅ ጀብድ ፈፅመው ለትውልድ አኩሪ ታሪክ አስረክበዋል።
በወቅቱ የአገሪ መሪ በሌለበት፣ መንግሥታዊ አደረጃጀት በፈረሰበት፣ ስንቅና ትጥቅ እንደ ልብ በማይገኝበት፣ ጠላት እንደፈለገው ቦንብና ገዳይ መርዞችን ከላይ በሚረጭበት፣ ከታች ደግሞ በዘመናዊ መሳሪያ ወገን በሚረግፍበት፣ አብዛኛው የዜጎች መኖሪያ በእሳት በሚጋይበትና በዚያን ክፉ ቀን የአገር ፍቅር ያነደዳቸው አርበኞችን ኢትዮጵያን ከጠላት መክተው ነፃ ማድረጋቸውን አውስተዋል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች ታሪክን በቅጡ ካለመመርመር የመነጩ እና የአባቶችን ተጋድሎ ካለመዘከር የመነጨ ነው። በመሆኑ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ለኢትዮጵያ አንድነት መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ባቀረቡት ፁሁፍ፤ ጥንታዊ አርበኞች የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ፍዳ መክፈላቸውን አስገንዝበዋል። በተለይም ደግሞ ጣሊያን በአድዋ ላይ በ1988 ዓ.ም የገጠማትን ሽንፈት ዳግም ለመበቀል በ1928 ዓ.ም ከፍተኛ ዝግጅት አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ዳግም ወረራ ባደረገች ጊዜ ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር አውስተዋል።
በጦርነቱ ወቅት በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ በተለይም ውስጣዊ ችግሮች ለጠላት ምቹ ሁኔታ ፈጥረው ነበር። በዚህም የተነሳ ጦርነቱ ብዙ ዓመታት እንዲቆይና ጠላት መልካም ሁኔታ እንዲፈጠርለት ካስቻሉ ምክንያቶች አንዱ ሆኗል።
ይሁንና በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውኖች በነበራቸው ከፍተኛ ተጋድሎ የአገራቸውን ክብር አስጠብቀዋል። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድም የአባቶቹን ታሪክ በሚገባ ሊገነዘብና የታሪክ እርሾ አድርጎ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች የትናንት ጀግኖችና አርበኞች ለአገሪቱ አንድነት የከፈሉትን መስዋዕትና ያደረጉትን ተጋድሎ ካለመገንዘብና ለትውልድ በተፈለገው ደረጃ ባለመተላለፉ የመጣ ነው።
መሰል ችግሮች ቀድሞ የነበሩና ለጠላትም አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል። በመሆኑም ትውልዱ አባቶች በጀግንነት ያቆዩዋትን አገር በትጋት ሊጠብቅና ታሪክን ሊያጤን እንደሚገባ ብሎም ቀጣናውንና ወቅታዊ ሁኔታ እንዲገነዘብ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በክፍለዮሐንስ አንበርብር