– ከ670 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል
– 400 አፈናቃዮች በቁጥጥር ሥር ውለዋል
አዲስ አበባ፡- ህግና ስርዓትን ማስከበርና በህግ የሚጠየቅን አካል እንዲጠየቅ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ። የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተሰራው ሥራ 800 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ተጣርቷል፤ 400 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ከ670 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 5ኛ ልዩ ስብሰባ ትናንት ሲካሄድ፣በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ የተመለከተው የሱፐርቪዥን ቡድን ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፣ ቡድኑ ያቀረበው ሪፖርት፤ ሚዛናዊ፣ የተፈናቃዮችን ድምጽ ያሰማና ሁኔታቸውን ያሳየ መሆኑንም ጠቁመዋል። ያልታዩ አካባቢዎች በቀጣይ እንደሚታዩም አመልክተዋል። ዓለም ያስደመመ ለውጥ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታ ውሰው፤ በአንጻሩ፤ አንገት የሚያስደፋ መፈናቀል፣ ሞትና ግጭት መኖሩ አሳፋሪ መሆኑን በማንሳት ድርጊቱን ኮንነዋል። ዜጎች ወጥተው የሚገቡበት ሰላማዊ ማዕቀፍ ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።
በለውጥ ወቅት አገር ሲመራ በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥማሉ ያሉት አቶ ደመቀ፤ ችግሩን ማስተካከል የሚያስችል፣ የህዝብ ተጠ ቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሥራ በመስራት ለውጡ ጥልቀት እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል። ህዝቡን ከመፈናቀልና መሰል ስጋት አላቅቆ ወደ ለውጥ ግስጋሴ የማስገባት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት። የችግሩን ባህሪና ስፋት የሚመጥን ሥራ እንደሚሰራ፣ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል፤ የተፈናቃዮች ቁጥር የማጥራት ሥራ መቀጠሉን በመጠቆም፤ ተጠያቂ መሆን የሚገ ባቸው ሰዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተሰራው ሥራ 800 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ማለቁንና 400 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ተናግረዋል።ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ ያለመስጠት የፖለቲካ አመለካከት ችግር እንዳለም አንስተዋል።
‹‹እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ እያስታመምን አንቀጥልም፣ አመራሮችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ባግባቡ ሊወጡ ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል። ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ስር ማዋል ካልተቻለ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው መመለስ አዳጋች ነው ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል። በአንዳንድ አመራሮች ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎች እንደሚነሱና አመራሮችም መጠየቅ እንዳለባቸው አንስተዋል።
ከአልሚ ምግብና ሌሎች ከሰብዓዊ ድጋፍ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ላይም ችግሩን የሚመጥን ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መከፈቱንም ነው የጠቆሙት።
ክረምት ከመግባቱና የተፈናቃይ ዜጎች ህይወት ለአደጋና ስጋት እንዳይጋለጥ ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራው በፍጥነት እን ደሚሰራም ገልጸዋል። ከጦር መሳሪያ ጋር ተያይዞ ልቅ ነገር ስለሚታይ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ሀብትና ንብረት የወደመባቸው ዜጎችን መረጃ በመያዝ ከባንኮችና ከብድር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የጤና አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን በመጠቆምም፤ ጉዳት የደረሰባቸው 215 ጤና ኬላና 12 ጤና ጣቢያዎች የማሻሻያ ሥራዎች እንዲሰሩ መለየታቸውንም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች ለማቅረብና የሙያ ድጋፍ ለመስጠት ትኩረት መደረጉንና የተጀመረው እርቀ ሰላም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ወይዘሮ ሙፈሪሃት ገልጸዋል። ጊዜያዊና ዘላቂነትን ያጣመረ መፍትሄ ይተገ በራል፣ በአገር አቀፍም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ይሰራል ብለዋል።
ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፤ ከ2009 ዓ.ም አንስቶ ሳያቋርጥ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ቢገኝም የተጓደሉ ነገሮች መኖራቸውን አንስተዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የተፈናቃዮች ቁጥር በመጨመሩ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ተናግረዋል። የመንገዶች መዘጋት እርዳታ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ገድቦ እንደነበርም አስታውቀዋል። የአልሚ ምግብና የግብአት አቅርቦት ችግር መኖሩንና ክልሎች የሚችሉትን ያለማድረግ ችግር እንዳለም አንስተዋል። ለመልሶ ማቋቋም ሥራው ከ670 እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ባለፉት ሁለት ወራት ትግበራ በሦስት ዙር ሊመለሱ ይችላሉ ተብለው ከተለዩ ተፈናቃዮች 760ሺ ገደማ (ሰባት መቶ ስልሳ ሺ) ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው፤ በዜጎች መፈናቀል ምክንያት ትምህርት ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩን በመጠቆም፤ የትምህርትና የአልባሳት ቁሳቁስ በማቅረብ ባሉበት ቦታ ትምህርታቸውን እንዲ ከታተሉ የተደረገ ወቅታዊ መፍትሄ እንዳለ ጠቁመዋል። ችግሩ ሙሉ ለሙሉ የሚፈታው ለተፈናቃዮች እልባት ተሰጥቶ ወደ አካባቢያቸው መመለስ ሲችሉ፣ የወደሙ ትምህርት ቤቶች ሲጠገኑና መምህራንም ሲመለሱ መሆኑን ነው ያነሱት። ችግሩ የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያስከትልም አንስተዋል። የከፍ ተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እያቀረቡ ያሉት የቦታ ቅያሪ ጥያቄ ችግሩን ስለሚያባብሰው ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረው፤ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ተማሪዎች ተመልሰው ትምህር ታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የሱፐር ቪዥን ቡድኑ በሪፖርቱ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሱ፣ህይወት ያጠፉ አካል ያጎደሉና ንብረት ያወደሙ በአፋጣኝ ሊጠየቁ ይገባል ሲል አመልክቷል።ዘላቂ ሰላምን በማረ ጋገጥ ዜጎች በየቀዬአቸው ያለስጋት የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠርም ይገባል። ጉዳዩ ተፈናቃይ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል የተለየና የተቀናጀ ዕቅድ እንዲወጣና እንዲተገበርም አሳስበዋል።
የሱፐር ቪዥን ቡድኑ 24 አባላትን ያቀፈና ቋሚ ኮሚቴዎች የተወከሉበት ነው። ጥናቱ በትግራይ፣ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተካሄደ ሲሆን፤ መረጃው በ13 ዞኖች ውስጥ ወካይ የሆኑ 12 ወረዳዎች ውስጥ በተጠለሉ 27 ተፈናቃይ ዜጎች የተጠለሉባቸው የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች በመስክ ምልከታና በውይይት መሰብሰቡ ተጠ ቁሟል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
በዘላለም ግዛው