አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በ26ኛው የፕሬስ ነጻነት ቀን ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙ የተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች ጠቆሙ።
ጋዜጠኞቹ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ መንግሥትን የሚተቹ ድረ ገጾችን በመዝጋትና የፕሬስ ነጻነትን የሚያፍኑ ህጎችን በማውጣት ስሟ ይነሳ ነበር። የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ የተደረገውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በውጭ ሀገራት የነበሩ ጋዜጠኞች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው፤ እስር ላይ የነበሩት መለቀቃቸው፤ የፕሬስ ነጻነት የሚያፍኑ ህጎች ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆኑና ተዘግተው የነበሩ ድረ ገጾች እንዲከፈቱ ማድረጓ በፕሬስ ነጻነት ደረጃ 40 ደረጃዎችን እንድታሻሽል ረድቷል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም አሁንም በርካታ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባታል። የሚዲያ ነጻነትን ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
የናሚቢያ ሚዲያ ትረስት ዋና ሊቀመንበርና ጋዜጠኛ ግዌን ሊስተር እንደምትለው፤ ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን በማፈን ስማቸው ከሚነሱ ሀገራት አንዷ ነበረች። ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን የፖለቲካ ለውጡን ተከትሎ የፕሬስ ነጻነት ላይም መሻሻሎች መታየት ጀምረዋል። የተዘጉ ድረገፆች እንዲከፈቱ መደረጋቸው መልካም ተግባር ነው። በዚህና በሌሎች ሥራዎች 40 ደረጃዎችን ልታሻሽል ችላለች። ባለፈው አንድ ዓመት የተሰሩ ሥራዎች ግን በቂ አይደለም። መንግሥት የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ተግባራት መቀጠል አለበት።
‹‹በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላም ጋዜጠኞች አይታሰሩም የሚል እምነት አለኝ ያለችው›› ጋዜጠኛ ግዌን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው የፕሬስ ነጻነትን ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን ተግባራት አጠ ናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላት ተናግራለች።
እንደ ጋዜጠኛ ግዌን ማብራሪያ፤ የፕሬስ ነጻነት ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ያለመናገር ነጻነትና ያለ ፕሬስ ነጻነት ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም። ጋዜጠኛው በነጻነት በመስራት ሙያውን የሚተገብርበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ህዝቡ በነጻነት መኖርና መናገር አይችልም። በመሆኑም የፕሬስ ነጻነቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከመንግሥት ባሻገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችና መላው ህብረተሰብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
የዩጋንዳ የሚዲያ ባለሙያዎች ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅና ጋዜጠኛ ጆን ናኩ በበኩሉ እንዳብራራው፤ አፋኝ ህጎችን በማውጣት ሚዲያዎችን ዝም የማሰኘት አቅም አለው። አፋኝ ህጎችን በማውጣት ሚዲያዎችን አፍ ማስያዝ ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለትንሽ ጊዜ ለመደበቅ ሊረዳ ይችል ይሆን እንጂ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ብልጽግና ፋይዳ አይኖረውም። ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከተፈለገ የፕሬስ ነጻነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳየው በጎ መሻሻል የሚደነቅ ነው። የፕሬስ ነጻነት ማረጋገጥ ግን በራሱ ግብ ሊሆን አይችልም። ነጻነት አተገባበር ዙሪያ መንግሥት ከሚዲያዎች ጋር በቅርበት መስራት አለበት።
ኢትዮጵያና ዩጋንዳን በመሳሰሉ ብዝሃነት ባሉባቸው ሀገራት የሚዲያዎች አዘጋገብ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል ያለው ጋዜጠኛ ጆን፤ በአንድ በኩል የሁሉም ማንነቶች በተገቢው የሚንጸባረቁበትን አውድ በመፍጠር በሌላ በኩል ሁሉንም ማንነቶች በሚያግባቡ የጋራ እሴቶች ላይ በትኩረት በመስራት የማይተካ ሚናቸውን ሊጫወቱ ይገባል ብሏል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ጋዜጠኛ አለመታሰሩና የሚዲያ ህጎችን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች መጀመራቸውን ሲሰማ መደሰቱን የተናገረው መቀመጫውን በዩኤስ ዋሽንግተን ያደረገውና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎችን በመለየት የሚታወቀው የስኖፕስ ዶት ኮም መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ጋዜጠኛ ዳቪድ ማይክልሰን ነው። የተወሰዱ እርምጃዎች ሀገሪቱ በሚዲያ ነጻነት የነበራትን ስም እንድታድስ እገዛ እያደረገላት ነው። ተጠናክረው መቀጠልም አለባቸው ብሏል።
ሚዲያው መንግሥትን በመቆጣጠር የመ ንግሥት ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መጎልበት የማይተካ ሚና ይጫወታል ያለው ዳቪድ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ሊያደርግ የሚችል ሚዲያ እንዲበቅል ሚዲያ፣ መንግሥትና መላው ህብረተሰብ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብሏል።
የሀሰት መረጃዎችንና የመረጃ ብክለትን ለመከላከል ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ህጎችን በማውጣት ላይ መሆናቸውን ያስታወሰው ዳቪድ፣ እነዚህ ህጎች የተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ለማፈን ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከነበረችበት በፕሬስ ነፃነት ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ ዘንድሮ 40 ደረጃዎችን ማሻሻሏ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
መላኩ ኤሮሴ