አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከሀገር ሲወጡ እና ሊገቡ ሲሉ የተያዙ የተለያዩ አገር ገንዘቦች 182 ሚሊዮን ስድስት መቶ ሺ ብር በላይ የምንዛሪ ዋጋ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጽህ ፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ደገፉ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የ2011 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያሳየው የምንዛሪ ዋጋቸው 182 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የሆኑ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች መያዛቸውን ነው። ከገንዘቡ እስከአሁን እንደሚደረገው ሁሉ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እየተደረገ ይገኛል።
እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ የምንዛሪ ዋጋቸው 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሆኑ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በህገ ወጥ መልኩ ወደ አገር ሲገቡ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በተመሳሳይ የምንዛሪ ዋጋቸው ብር 174 ነጥብ ሦስት 3 ሚሊዮን ብር የሆኑ በህገ ወጥ መልኩ ከአገር ሊወጡ የነበሩ የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ አገራት የገንዘብ ኖቶች ተይዘዋል።
ወርቅ፣ የከበሩ ማዕድናት እና የገንዘብ ኖቶች በኮንትሮባንድነት ሲያዙ በማስረጃ ተደግፎ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እንደሚደረጉ የገለጹት አቶ ወንድወሰን፤ የገንዘብ ኖቶቹ ሳይመነዘሩ በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊው እንደጠቆሙት፣ በተለይ የጅግጅጋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እና የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ዋነኛ የህገወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ማዘዋወሪያ ቦታዎች ተብለው ተለይተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኩል የምንዛሪ ዋጋቸው 99 ሚሊዮን 706 ሺ ብር የሆኑ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል።
በመላ አገሪቷ በሚገኙ የጉምሩክ ጽህፈት ቤቶች ያለው ቁጥጥር መጠናከሩን የገለጹት አቶ ወንድወሰን፤ በተለይ ደግሞ የውጭ አገራት ገንዘብ ኖቶች ዝውውር ቁጥጥሩ በሁለቱ ጣቢያዎች ከፍተኛ እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል። በአጠቃላይ የ94 ነባር እና አዳዲስ ኬላዎች የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመግታት በሚያስችል አግባብ አዲስ አደረጃጀት እንደተዘጋጀላቸው ጠቁመዋል።
እንደ ጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ግምታዊ ዋጋቸው 885 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ ንብረቶች ወደ አገር ሊገቡ እና ከአገር ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። የኮንትሮባንድ የመከላከል ሥራን በተገቢው ሁኔታ ለማስቀጠል የፌዴራል ፖሊስ ኃይል በጉምሩክ ደንብ መሠረት ተቋቁሞ ከ94ቱ በ44 ኬላዎች 660 የፖሊስ ኃይል ተመድበው እየሰሩ ይገኛል።በተቀሩት ደግሞ የመደበኛ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26/2011
ጌትነት ተስፋማርያም