ገላን፡- በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በ10ሺ 500 ካሬ ሜትር ላይ የተገነባውና 12ሺ ቶን የኤሌክትሪክ ኬብል ማምረት የሚችለው ‹‹ዩሮ ኬብል›› ፋብሪካ የማምረት አቅሙን በሦስት እጥፍ ማሳደግ እንደሚያስችለው ተገለጸ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ የተገነባው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የኤ ሌክትሪክ ኬብል ማምረቻ ፋብሪካ በትናንትናው ዕለት ተመርቋል፡፡
የዩሮ ኬብል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፋብሪካ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ስአድ ኢብራሂም በፋብሪካ ምረቃው ስነስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው ከአስር ዓመት በፊት በኢትዮጵያና በቱርክ ባለሀብቶች ጥምረት ከውጭ የሚገባውን የኤሌክትሪክ ኬብል በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት አላማ አድርጎ የተገነባ ሲሆን፤ በ55 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ30 ሰራተኞች በግሎሪ የኤሌክትሮኒክስ እቃ አስመጭ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቅጥር ግቢ ውስጥ ስራውን ጀምሯል፡፡ በአንድ ፈረቃ በዓመት 12ሺ ቶን የኤሌክትሪክ ኬብል ሲያመርት የነበረ ሲሆን፤ በሦስት ፈረቃ በማምረት ምርቱን በሦስት እጥፍ ከፍ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ፋብሪካው ከአሁን በፊት በሀገር ውስጥ ተመርተው የማያውቁ እንደ አርምድ ኬብል (በመንገድ ላይ የሚቀበር ኬብል)፣ ዳታ ማስተላለፊያ ኬብል፣ የሳተላይት ኬብል፣ የእሳት አደጋን መቆጣጠር የሚችሉ ኬብሎችን እና ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ ኬብሎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ከተመሰረተ ጀምሮ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ግብር ለመንግስት ገቢ ማድረግ መቻሉን፤ አዲሱ የማስፋፊያ ፋብሪካ የፋብሪካውን ካፒታል ከ1ነጥብ 2ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያደርሰው፤ ለ200 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑንና ከ1ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረጉንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ፋብሪካው ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደሚያስችለው አክለዋል፡፡
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ማምረት ከሚችለው አቅሙ 20 በመቶውን ብቻ እያመረተ እንደሚገኝ የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ ለኬብል ማምረቻ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች አብዛኞቹ ከውጭ የሚገቡ በመሆኑ፤ ጥሬዕቃዎቹን በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ለማስቻል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባንኮች ብድር በማመቻቸት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በሶሎሞን በየነ