አዲስ አበባ:- የኢትዮ-ኤርትራ የህዝብ ለህዝብ ብሎም የመንግስታቱን ግንኙነት ለማጠናከርና ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከቀድሞ በላቀ ደረጃ የክልሉ መንግስት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በተያዘው ዓመት የተጀመረው ዳግም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ህወሓት ለግንባሩ ኢህአዴግ ባቀረበው ጥያቄና ባሳረፈው ውሳኔ መሠረት የተከናወነ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
መንግስትም ሃሳቡን ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረጉ የሁለቱ ሕዝቦች ዳግም ለመገናኘትና በርካታ ትሩፋትም ለማግኘት ችለዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ከቀድሞ ጀምሮ ግንኙነቱን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን በመግለጽ፤ በሰላም ሂደቱ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር የተለየ አቋም እንዳለው በማድረግ የሚሰራጩ ወሬዎች ትክክል እንዳልሆኑና ተቀባይነት እንደሌላቸውም አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ሕገ፡መንግሥቱንና የፌዴራል ስርዓቱን በመጠበቅ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወትም አያይዘው ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ተግባራትም ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
ዶክተር ደብረጽዮን፤ የክልሉ መንግስት የታችኛውን መዋቅር ዳግም የማደራጀት ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል። በክልሉ ያለውን ስራ አጥነት ለመፍታት፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት በክልሉ የታችኛውን የመንግስት መዋቅር ዳግም የማደራጀት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
የክልሉ ሰላም ይበልጥ እንዲጠናከር ከመስራት አልፎ ለመልካም አስተዳደር ችግሮችና ለልማት ስራዎች እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ለመፍታት የተለየ ትኩረት የተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላም ኢንቨስትመንቱን ከማጠናከር ጀምሮ ለሌሎች ክልሎችና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ምሳሌ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
የቀበሌ መዋቅሩን የማጠናከርና አደረጃጀቱን የማስተካከል፣ የግብርና ስራውን የማጠናከር፣ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ከተለያዩ ክልሎች ለተፈናቀሉት የመስሪያ ቦታና የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በሀፍቱ ገብረእግዚአብሔር