አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ ክልል በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ያለው የወንድማማችነት ግንኙነት እንዲጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክሮ እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡
የሀረሪ እና ኦሮሞ ህዝቦችን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር የኦሮሞ እና የሐረሪ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በትናንትናው ዕለት በሐረር ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በሐረር ከተማ እየተካሄደ ባለው የህዝብ ለህዝብ ኮንፍረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ያለውን የወንድማማች ግንኙነት ማንም ሊያፈርሰው እንደማይችል፤ በአንድነት በመኖር፣ አብሮ በመልማትና በማደግ በህዝቦች ትስስር ውስጥ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመድፈን በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ለውጥ እና የፖለቲካ ነፃነት በመጠበቅ ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብና በሁሉም መስክ የለማች ሀገርን ለመፍጠር መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል
የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ የሀረሪ እና ኦሮሞ ህዝቦች ለዘመናት በፍቅርና በአንድነት የኖሩ መሆናቸውን፤ ሁለቱ ህዝቦች በተለያዩ ወቅቶች ለነጻነት እና ለማንነት የተደረጉ ትግሎች ላይ በጋራ ሲሳተፉ የቆዩ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
የኦሮሞና የሐረሪ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ታስቦ በመካሄድ ላይ ባለው የውይይት መድረክ ላይ የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሎቹ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል። በቅርቡ የኦሮሞና ቡኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የኦሮሞና አማራ እንዲሁም የኦሮሞና ሱማሌ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች በተለያዩ አካባቢዎች መካሄዳቸውም ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በአዲሱ ገረመው