ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡ 30 ሰዓት ገደማ ነው፡፡ በስልጤ ዞን አካባቢ ከባድ ዝናብ እየጣለ ነበር፡፡ በዞኑ የቅበት ከተማ ቀጠር ቀበሌ ነዋሪና የሦስት ልጆች አባት አቶ ሁሴን ሱንቀሞ ለአራስ ባለቤታቸው አጥሚት በማዘጋጀት ላይ ሳሉ ከውጪ በኩል ከባድ ድምጽ ሰሙ፡፡ የዝናብ ነጎድጓድ ድምጽ ስለመሰላቸው ትኩረት አልሰጡም፡፡
ድምጹ ግን የነጎድጓድ ሳይሆን ጎርፍ ትላልቅ ድንጋዮችን እያንከባለለ ወደ ቤታቸው የሚመጣ ድምጽ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ በቤታቸው በር ክፍተት የጎርፍ ውሃ ወደ ቤታቸው መግባት ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ጎርፉ እያንከባለለ ያመጣው ትልቅ ድንጋይ የቤቱን በር ሙሉ በሙሉ በመስበሩ ጎርፉ ያለከልካይ ወደ ቤት ገባ፡፡
ውሃው ቤቱን እየሞላ ሲመጣ የአምስት፣ የሦስትና የአንድ ወር ህጻናት ልጆችንና ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ውጪ ሊወጡ ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡ መላው ቤተሰባቸውን ይዘው በቤታቸው ውስጥ ባለው ቆጥ ላይ ወጡ ፡፡ የጎርፉ ሀይል እጅግ ከባድ በመሆኑ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ውሃው ቤቱን ሞልቶ እነሱ የተቀመጡበት ቆጥ ድረስ ማጥለቅለቁን ቀጠለ ያሉን አቶ ሁሴን ናቸው፡፡
ውሃው ቤት ሞልቶ ግድግዳውን ጥሶ ሲወጣ ውሃው መላውን ቤተሰብ ይዞ ወጣ፡ ፡ ጎርፉ ረጅም ርቀት ከወሰዳቸው በኋላ አቶ ሁሴንና ባለቤታቸው ዛፍ በመያዝ መትረፍ የቻሉ ሲሆን የአምስት፣ የሦስት ዓመትና የአራስ ቤት ጨቅላ ህጻኑን ግን ጎርፉ ይዟቸው እንደሄደ ነገሩን፡፡
‹‹ የሁለቱ ሬሳ ተገኝቷል፤ የአንዱን ሬሳ ግን ማግኘት አልተቻለም፡፡›› የሚሉት አቶ ሁሴን፤ ጎርፉ ቤት ውስጥ የነበረውን እህል፣ ከብትና የቤት ውስጥ መገልገያዎች ከነቤቱ አፍርሶ የወሰዳቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ አደጋው ከደረሰበት ዕለት ጀምሮ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም መላው የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
አሁንም ቢሆን አካባቢው አስፈሪ ነው የሚሉት አቶ ሁሴን፤ እንደርሳቸው ሁሉ በሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ላይም ተመሳሳይ አደጋ ሊከሰት ይችላል፡ ፡ በመሆኑም የጎርፉን መምጫ መንገድ ለይቶ ማስተካከል ወይም ቅያሪ ቦታ ሰጥቶ ህዝቡ አካባቢውን ለቆ እንዲነሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡
በዞኑ በ7 ቀበሌዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ከእነዚህም ውስጥ በ5ቱ ቀበሌዎች ከባድ ጉዳት ማስከተሉን የሚናገሩት የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱዋሪስ ጀማል ጎርፉ የስድስት ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ይናገራሉ፡፡ ከሟቾች መካከል ሦስቱ የአቶ ሁሴን ሱንቀሞ ልጆች ሲሆኑ፤ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ በባጃጅ ተሳፍረው በመንገድ በመሄድ ላይ ሳሉ በደራሽ ጎርፍ መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ከአምስት ሺ 615 በላይ ዜጎች በጎርፉ ምክንያት መፈናቀላቸውንና 637 ቤቶች በጎርፉ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተናገሩት አቶ አብዱዋሪስ ፤ 342 ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል በውኃ ተጥለቅልቋል ብለዋል።
የችግሩ ሰለባዎችን ለመርዳት የዞኑ መንግስት ከአካባቢው ህብረተሰብና ከክልሉና ከፌዴራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጋር በመሆን ተጎጂዎችን የመንከ ባከብና ችግሩን እንዲቋቋሙ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ የዞኑ አስተዳደር አንድ ሚሊየን ብር በመደገፍ በጉዳቱ ምክንያት ቤት አልባ የሆኑትን አንድ ላይ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡ የአልባሳት፣ የህክምናና የምግብ ድጋፍም እየቀረበላቸው ነው፡፡
እንደ አቶ አብዱዋሪስ ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም በዞኑ በሌሎች አካባቢዎች እንጂ አሁን ጎርፍ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተከስቶ አያውቅም፡፡ የአደጋ ባለሙያዎች ባከሄዱት የአደጋውን መንስኤ የማጣራት ስራ የዘነበውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ጎርፉ የተፈጥሮ መንገዱን ለቆ በመውጣት ሰው ወዳለባቸው አካባቢዎች በመፍሰሱ እና በቅበት ከተማ ውስጥ የሚገኙ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ጎርፉን ማስተላለፍ ባለመቻላቸው አደጋው ሊከሰት መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አራት ስካቫተሮችን በማስገባት ጎርፉ ጥሶ የወጣባቸውን ክፍተቶች የመድፈን ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ በቅበት ከተማ ውስጥ የሚገኙ ቱቦዎቹ እንዲስተካከሉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የማሳወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ ውሃውን ማስተላለፍ የሚችሉ ቱቦዎችን ለመተካት ባለስልጣኑ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል፡፡
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደሚሉት፤ ከስልጤ ዞን በተጨማሪ በሀላባ ዞን የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከ10ሺህ ሄክታር በላይ የለማ መሬት የወደመ ሲሆን፤ ከ3ሺ በላይ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
በዞኖቹ ለጎርፉ መከሰት ምክንያት የሆኑትን የጎርፍ መተላለያ መንገዶችን የመድፈን ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማስተባበርና በመንግስት ድጋፍ ለሁለቱም ዞኖች የጎርፍ ተፈናቃዮች ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አማን ማብራሪያ፤ ክረምት እየመጣ ስለሆነ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች በመለየት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በክልሉ ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል ስልጤ፣ ሀላባ፣ ሀዲያና ጉራጌ ዞኖችና የሀዋሳ ከተማ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡ ፡
በአካባቢዎቹ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ተፋሰሶችን የማስተካከል ስራዎች እየተሰራ ነው፡፡ በተለይም የክልሉ መንግስት ከዞን መስተዳድሮች ጋር በመሆን ከከፍታ ቦታዎች የሚመጣው ጎርፍ ጉዳት እንዳያደርስ የማስቀልበስ ስራዎች እየተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም የተፋሰስ መተላለፊያዎችን በተገቢው በማጽዳት የሚመጣው ጎርፍ ጉዳት እንዳያደርስ እየተሰራም ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በመላኩ ኤሮሴ