ዶክተር ነጋሶ ለወይዘሮ አያኔ ተርፋሳ የእናታቸው አጎት ናቸው፡፡ በቅርቡ ከዚህ ዓለም የተሰናበቱት የቀድሞ የኢፌዴሪ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የህይወት ዘመን ቆይታቸውን አስመልክተው እንደሚናገሩት፤ በተለይ ቤተሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የነበራቸው አዎንታዊ ድርሻና ለትውልዱ አስቀምጠው ያለፉት ሕያው ተግባር አስተማሪ ነው፡፡
እንደ ወይዘሮ አያኔ ገለጻ፤ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጣም ተግባቢ፣ ሰውን በቶሎ መቅረብና መግባባት የሚችሉ፣ ዘመድ ጠያቂና በቤተሰባዊ ምክክሮች ላይ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ በማኅበራዊ አውድ ውስጥ በተለይ በቤተሰብ ዙሪያ ‹‹ሶለን›› የሚባል ማኅበር አቋቁመው ነበር፡፡ ማኅበሩ በየሦስት ወሩ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የሚገናኙበትና የሚጨዋወቱበት ስለ ማኅበራዊ ህይወት የሚያወጉበት፣ ‹‹ለማኀበረ ሰቡ ምን አስቀምጠን እንለፍ›› የሚል የረጅም ጊዜ እቅድም የሚያወሩበት ነው፡፡
ዶክተር ነጋሶ በአቋማቸው ጽኑ መሆና ቸውንና በትምህርታቸውና በሥራ ቸውም ከእሳቸው ስር ላሉ ሰዎች ትልቅተምሳሌት እንደነበሩ ወይዘሮ አያኔ ይናገ ራሉ፡፡ ‹‹የሚያምኑበትን ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉና የመርህ ሰው ነበሩ›› በማለትም ያስታውሷቸዋል፡፡ ዶክተር ነጋሶ የስራ ሰዓትን አክባሪ እንዲሁም ጎበዝና ጠንካራ ሰራተኛ እንደሆኑ በመጥቀስ፤ ይህም በሥራው ዓለም በኩል ያለውን ጥንካሬያቸውን እንደሚያጎላው ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ከተግባራቸው የተቀዳ ታታሪነት ማንም ሰው በየትኛውም ጊዜ መመስከር የሚችለው መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ወይዘሮ አያኔ አክለውም፤ ‹‹ምንም እንኳን እርሳቸው በስጋቸው ህልፈት ቢያጋጥማቸውም ሁሌም የሚወሱና በተምሳሌትነት መያዝ የሚችሉ ነገሮችን ትተው አልፈዋል›› በማለት ጠንካራ ሠራተኛ መሆን የሚቻልበትን መንገድ፣ ሰውን ማክበር፣ ዘመድ ጠያቂ መሆንን፣ ላመኑበት ነገር ሁሉ ወደ ኋላ ማለት እንደማያስፈልግ የሚያበረታቱ ሥራዎቻቸው ሁሌም ከትውልዱ ጋር እንደሚቆዩ ያብራራሉ፡፡
ከቤተሰብ ከፍ ሲልም እንደ አገር በተለይ አሁን ላይ ያሉ ወጣቶች ሰው ለዓላማው ቆራጥና ታታሪ ሰራተኛ መሆን እንዳለበት፤ ታሪክን ሳያበላሹ ለወገን አንድ ነገር ሰርቶ ማለፍንም ከዶክተር ነጋሶ መማር እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም ሰው ለግል ጥቅሙ ብቻ ሳይሆን ለራሱም ሆነ ለአገር ታሪክ ሰርቶ መልካም ስም እንዲኖረው በማድረግ መስራትን በጥልቀት በማየት ፈለጋቸውን መከተል አለባቸው ካሉ በኋላ ዶክተር ነጋሶ ለጊዜያዊ ጥቅም የማይበገሩ ሰው መሆናቸውንና ወጣቱን ትውልድም ከእነዚህ ታላላቅ ሥራዎቻቸው ትምህርት ሊወስድ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ይመክራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2011
በአዲሱ ገረመው